Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበወለጋ በኦነግ ስም የታጠቁ ቡድኖችን ትጥቅ ለማስፈታት በተጀመረው እንቅስቃሴ ጉዳት እየደረሰ ነው

በወለጋ በኦነግ ስም የታጠቁ ቡድኖችን ትጥቅ ለማስፈታት በተጀመረው እንቅስቃሴ ጉዳት እየደረሰ ነው

ቀን:

ትጥቅ ላለመፍታት ባሸመቁ ላይ በተወሰደ የኃይል ዕርምጃ በርካቶች መሞታቸውን እማኞች ገለጹ

በፀጥታ አስከባሪዎች ላይ በተሰነዘረ የቦምብ ጥቃትም የአካል ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል

የመከላከያ ሠራዊት በወለጋ አካባቢ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ስም የጦር መሣሪያ ታጥቀው የፖለቲካ ንቅናቄ የሚያደርጉ ቡድኖችን ትጥቅ ለማስፈታት የጀመረው እንቅስቃሴ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት ማድረሱና በአካባቢውም የግጭት ውጥረት መንገሡ ተሰማ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመከላከያ ሠራዊቱ ከቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በምዕራብና በምሥራቅ ወለጋ አካባቢዎች መሰማራት መጀመሩን የሚገልጹት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአካባቢው ምንጮች፣ ሠራዊቱ እንደሚሰማራ ቀደም ሲል መረጃ የነበራቸው የአካባቢው ወጣቶች ከቅዳሜ በፊት በነበሩት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፎችን በማድረግ ትጥቅ የማስፈታት ዓላማውን ሲቃወሙ እንደነበር ጠቁመዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ በአካባቢዎቹ እንዳይሰማሩ መንገዶችን በመዝጋት ድርጊት ላይ መሰማራታቸውን ምንጮች ገልጸው፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የተዘጉ መንገዶችን በመጥረግ መሰማራት ቢቀጥልም በአንዳንድ አካባቢዎች በጦር መሣሪያ የታጀበ ግጭት እንደገጠመውና በዚህ ምክንያትም የኃይል ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን ገልጸዋል።

የታጠቁት ወጣቶች ለኃይል ዕርምጃው የአፀፋ ምላሽ እየሰጡ በማፈግፈግ ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ፣ የተቀሩት ደግሞ ወደ ጫካ በመሸሽ እንደተሸሸጉ ይናገራሉ። መከላከያ ሠራዊት አባላት የአካባቢው አመራሮችንና ሽማግሌዎችን በማስተባበር ትጥቅ የማስፈታት ተልዕኳቸውን ቤት ለቤት በመዞር ለመፈጸም ጥረት እያደረጉ መሆኑን፣ ነገር ግን መሽገው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መንገድ በመዝጋትና ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር እየተሰወሩ መሆናቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ወለጋ አይራ ጉሊሶ በሚባል አካባቢ መንገድ በመዝጋት የሠራዊቱን እንቅስቃሴ ለመገደብ በሞከሩ ቡድኖች ላይ ሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በተወሰደ የኃይል ዕርምጃ፣ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል። በምዕራብ ወለጋ ቤጊ በተባለ አካባቢ በተወሰደ ዕርምጃ ጉዳት ባይደርስም የታጠቁት ቡድኖች መሸሻቸውን፣ በደምቢዶሎ አካባቢ በመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ በተሰነዘረ የቦምብ ጥቃት፣ በሦስት ወታደሮች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።

በቄለም ወለጋ፣ ሆሮ፣ ዋበራ በተባሉ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ መኖሩንና ነዋሪዎችም አካባቢዎቹን ለመልቀቅ መገደዳቸውን ምንጮች ገልጸዋል። የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በቤጊና በነቀምት የአካባቢውን ነዋሪዎችና ወጣቶች በመሰብሰብ ሲያነጋግሩና ሲያግባቡ እንደነበር ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በአካባቢው ስለተጀመረው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴና እስካሁን ስለደረሰው ጉዳት ማብራሪያ እንዲሰጡ ለመከላከያ ሚንስትሯ ወ/ሮ አይሻ መሐመድ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም የጉዳት መረጃ እንደሌላቸው፣ ወደ አስቸኳይ ሰብሰባ እየገቡ ስለሆነም ማብራሪያ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

ሪፖርተር የኦሮሚያ ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ለአቶ ሁሴን ፋይሶና የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ለአቶ ሌሊሳ ዋቆያ ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፣ ኃላፊዎቹ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ይሁን እንጂ አቶ ሁሴን በቀጣዮቹ ቀናት የተጠናቀረ መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ ማክሰኞ ማምሻውን ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ በምዕራብ ወለጋና በቄለም ወለጋ በኦነግ ስም በመታጠቅ ሕዝቡን ለችግር እየዳረገ ያለ አካል በአፋጣኝ ከዚህ ተግባር እንዲታቀብ አሳስበዋል፡፡

መንግሥት እስካሁን እንዲህ ዓይነቱን ተግባር በትዕግሥት ሲመለከት ነበር ያሉት አቶ ለማ፣ ከዚህ በኋላ ግን መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅና ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በወለጋ አካባቢ ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴውን ለማደናቀፍ የሚጥሩና ከጀርባ ሆነው ወጣቶችን የሚያሳስቱ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ፣ እንዲሁም መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንደሚቀጥልና ምንም ዓይነት ትዕግሥት እንደማይኖረው አስጠንቅቀዋል፡፡

ሪፖርተር በአካባቢው ማግባባት ሲያደርጉ ታይተዋል የተባሉትን የኦነግ ሊቀመንበር በስልክ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...