Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባን የመጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሪ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ የውኃ እጥረት በመከሰቱ ውኃ በፈረቃ ለማድረስ የተገደደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ የንፁህ ውኃ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የገጠመውን ችግር ለመፍታት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ እንዲፈቅዱ ጠየቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጋር ባካሄዱት ውይይት፣ ለመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ የውጭ ምንዛሪ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡

የውይይቱ ማጠንጠኛ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተስተጓጎሉ በመሆናቸው፣ የውጭ ምንዛሪ በፍጥነት በሚቀርብበት መንገድ ላይ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከጀመራቸው የንፁህ ውኃ ፕሮጀክቶች መካከል የለገዳዲ ክፍል ሁለት ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በቀን 86 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውኃ ማመንጨት የሚያስችል በመሆኑ፣ ከ900 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበለት ይህ ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክት ተጠናቆ፣ የሚገኘውን ውኃ ወደ ሥርጭት ማስገባት የሚያስችሉ ዕቃዎችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጋጥሟል፡፡

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማጋጠሙና ይህ ችግር ሳይፈታ በመቆየቱ የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ነገር ግን የዋጋ ማስተካከያውን ጥያቄ ለማስተናገድ የግዥ መመርያው ባለመፍቀዱ የግንባታ ሒደቱ ተቋርጦ በድጋሚ ጨረታ እንዲወጣ ተወስኗል፤› ሲል የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ምክትል ከንቲባው ለዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ለድሬ የውኃ ግድብ ጥገና፣ እንዲሁም ለቦሌ አራብሳ ቤቶች ፕሮጀክት የፍሳሽ ማጣሪያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ እንዲለቀቅ ጠይቀዋል፡፡

መረጃዎች እንደጠቆሙት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ለቀረበው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ይህን ውይይት ከማድረጋቸው በፊት፣ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ጋር ነሐሴ 2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ውይይት አድርገው ነበር፡፡

በመጀመርያ ውይይታቸው ትኩረት የተደረገው ለኖርዝ አያት ፈንታ ጥልቅ ጉድጓድ ፕሮጀክት 22 ሚሊዮን ዶላርና አምስት ሚሊዮን ዩሮ ተጠይቆ፣ ነሐሴ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. የውጭ ምንዛሪ ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ለ700 ሺሕ ነዋሪዎች የሚበቃ 68 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውኃ ማመንጨት የሚያስችል ሲሆን፣ የሲቪል ሥራው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በ150 ሚሊዮን ብር ተከናውኗል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ በቀን ከ930 ሺሕ ሜትር ኪዩብ እስከ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ንፁህ ውኃ ያስፈልጋታል፡፡

ነገር ግን የከተማው አስተዳደር እያቀረበ የሚገኘው 525 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውኃ ብቻ ሲሆን፣ ይህም ቢሆን በኤሌክትሪክ መቆራረጥና በሌሎች የቴክኒክ ብልሽቶች ለነዋሪዎች በአግባብ እያደረሰ አለመሆኑን፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን አባተ (ኢንጂነር) በቅርቡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች በይፋ ወደ ፈረቃ አሠራር የተገባ በመሆኑ፣ በፈረቃ አሠራር ለኅብረተሰቡ ቢያንስ በሳምንት ሦስት ቀናት ውኃ ይደርሳል ተብሏል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች