Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊያልተፈታው የቀድሞ ሠራዊት ጥያቄ

ያልተፈታው የቀድሞ ሠራዊት ጥያቄ

ቀን:

የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት አመሠራረትና ታሪካዊ አመጣጥ ረዥም ዓመት ቢያስቆጥርም፣ በዘመናዊ ሠራዊትነት መደራጀት የጀመረው በ1927 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህ መልክ ከተደራጀ በኋላ የአገሩን ፀጥታና ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ በኮሪያና በኮንጎ ዓለም አቀፋዊ ግዳጁን በመወጣት ዝናን አትርፏል፡፡ ሕዝቡንም በሁለት ጊዜ ሽግግሮች በጥሩ ሥነ ምግባር ያላንዳች ግጭትና የመከፋፈል ስሜት ተረጋግቶና ተሳስቦ እንዲቆይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይዘነጋም፡፡

የሚያጋጥመውን ማኅበራዊ ችግር ለመወጣት ሲል ሲቪሎችንም ያካተተ ዕድር መሥርቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሠራዊቱ በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ሠራዊቱን በትኖታል፡፡ በመበተኑም የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊትና ሲቪል ሠራተኞች በሚል መጠሪያ ባቋቋመው የዕድሩ ገንዘብ ተጠቃሚ መሆን አልቻልም፡፡ ጡረታና ነፃ የሕክምና መብቶች ላይ ግን ተጠቃሚ የሆኑና ያልሆኑ መኖራቸው ዛሬም ድረስ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ኮሎኔል ጋረደው ነውጤ የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊትና ሲቪል ሠራተኞች መረዳጃ ዕድር ዋና ጸሐፊ ናቸው፡፡ እንደ ዋና ጸሐፊው ገለጻ፣ ዕድሩ የተመሠረተው በ1964 ዓ.ም. ነው፡፡ የዕድሩ ዋነኛ የገቢ ምንጩም ከአባላት ወይም ከዕድርተኛው በነፍስ ወከፍ በየወሩ የሚዋጣው ሁለት ብር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የሚሰበሰበውም ገንዘብ ተቀማጭ የሚሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ በዕድሩ ስም በተከፈተው የሒሳብ ደብተር ነው፡፡

- Advertisement -

ከእያንዳንዱ ዕድርተኛ ደመወዝ ላይ በየወሩ ከደመወዝ እየቆረጠ በዕድሩ ስም በተጠቀሰው ቅርንጫፍ የሚያስገባውም የመከላከያ ሚኒስቴር የምድር ጦር ሒሳብና ደመወዝ መምሪያ እንደነበር፣ በዚህ ዓይነት አካሄድ ዕድሩ ከተመሠረተበት ዕለት ጀምሮ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም. ድረስ በቅርንጫፍ ባንክ የተቀመጠው ገንዘብ ወደ ሰባት ሚሊዮን ብር እንደተጠጋ፣ ሠራዊቱ ቢበተንም የዕድሩ ህልውና ግን እስካሁን መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

መምሪያው የዕድሩን ገንዘብ እየሰበሰበ ባንክ የሚያስገባበትን ሰነድ ለዕድሩ እንዲያስረክብ ቢጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ዕድሩ መምሪያውን በልደታ መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሶ ነበር፡፡ የምድር ጦር የሕግ አገልግሎትም መምሪያውን ወክሎ ፍርድ ቤት መቆሙን ዋና ጸሐፊው ይናገራሉ፡፡  

የዕድሩ የክስ ጭብጥ ሠራዊቱ በመምሪያው ላይ ባለመብትም፣ ተጠቃሚም እንደነበር፣ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ስለተበተነ መምሪያው ሊያስተናግደው እንደማይችል፣ በዚህም የተነሳ የዕድሩን ገንዘብ ለማንቀሳቀስ የምችልበትን ሰነድ ልቀቅልኝ የሚል ነው፡፡ የመምሪያ የመከራከሪያ ጭብጥ ደግሞ ዕድሩ የተመሠረተውና መምሪያውም የዕድሩን ገንዘብ ማስተናገድ የጀመረው በንጉሡ ሥርዓት እንደነበር፣ ይህም ሥርዓት ፈርሶ በቦታው የደርግ ሥርዓት ሲተካ መምሪያው የያዘውን አገልግሎት እንደቀጠለ መቆየቱንና የደርግ ሥርዓት በኢሕአዴግ ሲተካ ግን ምን አዲስ ነገር ተገኘና ነው ሰነድ የመረካከብና ገንዘብ የማስለቀቅ ጥያቄ የተነሳው የሚል ነው፡፡

የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቱም በሁለቱም ወገኖች የቀረቡለትን ጭብጦች በሚገባ ከመረመረና ከተመለከተ በኋላ የቀድሞ ጦር ሠራዊትና ሲቪል ሠራተኛን የዕድር ገንዘብ በምንም ዓይነት የአሁኑ የመከላከያ ሠራዊት ሒሳብ መሆን ስለማይችል፣ የዕድሩ አባላት በባንክ ያለውን የዕድሩን ገንዘብ እንዲያንቀሳቅሱ ፈረደ፡፡ መምሪያው ገንዘቡ ለዕድሩ ሊለቀቅ አይገባም በሚል ለፍርድ አፈጻጸም የተቃውሞ ይግባኝ አቀረበ፡፡ የፍርድ አፈጻጸሙም የመጀመርያ ፍርድ ቤት የፈረደው የሕግ ስህተት ስለሌለበት ባንኩ ለዕድሩ ገንዘቡን እንዲለቅ በድጋሚ ፈረደ፣ የሕግ አገልግሎቱ እንደገና ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረበ፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም የቀረበለትን አቤቱታ ካየ በኋላ ገንዘቡ ታግዶ እንዲቀመጥ ሲል ፈረደ፡፡

‹‹ከዚህም በኋላ የታገደውን የዕድሩን ተቀማጭ ገንዘብ፣ የጡረታና ነፃ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብቶችንና የመኮንኖች ክበብን የሚመለከቱ ጥያቄዎች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊ አራት ጊዜ፣ ለአቶ  ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሁለት ጊዜ በተለያዩ ዓመታት በጽሑፍ አመልክተናል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሮቹ በተለያዩ ዓመታት ያቀረብናቸውን አቤቱታዎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው 11 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግልባጭ እንዲያውቁት አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ ያቀረቡት አቤቱታዎች ሁሉ ያለምንም መልስ የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ግን ጉዳዩን ከተከታተለ በኋላ የደረሰበትን ድምዳሜ ግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ለዕድሩ በጽሑፍ አሳውቋል፡፡ ጽሑፉም የሚለው ምድር ጦር ጡረታና ነፃ የሕክምና መብቶችን የከለከለው ሰው እንደሌለ፣ የሚፈልጉ በግንባር ቀርበው እንዲታከሙና ጡረታቸውንም እንዲጠይቁ የሚጠቁም ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ ጉዳዩን በመከታተልና በመመርመር ላይ መሆኑን ለዕድሩ እንዳሳወቀ አስረድተዋል፡፡

በተለይ የዕድሩን ገንዘብ በተመለከተ እስከ በላይ ፍርድ ቤት ማለትም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዛም ወደ ሰበር ሰሚ ለምን አላመለከታችሁም? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ኮሎኔል ጋረደው ሲመልሱ፣ ‹‹በፍርድ ቤት ፍትሕን ፍለጋ ብዙ ውጣ ውረድ ስለበዛብን እስቲ ጉዳዩን ወደ መልካም አስተዳደር ወስደን ውጤቱን እንየው በሚል እምነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ኮሎኔል ጋረደው፤ በቀድሞ ሕግ መሠረት ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገለ ዘላቂ ጡረታ ወዲያውኑ ወይም ዕድሜው ለጡረታ ሲደርስ ይከበርለታል፡፡ ከአሥር ዓመት ላነሰ አገልግሎት ለጡረታ የተቀመጠው ገንዘብ ይመለስለታል፡፡ አሁን ያለው የምድር ጦር ግን የቀድሞውን ሕግ በመሻር የ20 ዓመታት አገልግሎትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የአገልግሎት ዓመት የቀድሞውን ጦር አይመለከትም፡፡ ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ የምድር ጦር እኔ ስላላሠራኋችሁ ስለመብታችሁ ወደ ጡረታ ኤጀንሲ ለመጻፍ አልገደድም በማለቱ ብዙዎቹ ጡረታ አልባ ሆነዋል፡፡

ሠራዊቱ ለእናት አገሩ ሲል የቆሰለ፣ በከፍተኛ ውጣ ውረድ የደከመ አረጋዊ በመሆኑ ከፍሎ ለመታከም አቅም እንደሌለው ዋና ጸሐፊው ጠቁመው፣ በሠራዊቱ ደንብና መመርያ መሠረት ቢቻል በጦሩ ሆስፒታል ካልተቻለም በማንኛውም የመንግሥት ሕክምና ተቋም በነፃ የመታከም መብቱ እንዲከበርለት ጠይቀዋል፡፡ ምድር ጦር ደግሞ የጡረታ መብት ያላቸውና ደብተር የያዙ ሁሉ ቀርበው እየታከሙ ነው የሚል መልስ ቢሰጥም፣ ከ1987 ዓ.ም. በፊት ጡረታ የወጡ የሕክምና አገልግሎት እንደተነፈጋቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዋና ጸሐፊው እንደሚሉት፤ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢና ጨለለቃ ሕንፃ አጠገብ የነበረው የቀድሞ ጦር ሠራዊት መኮንኖች ክበብ የዕድሩ ይዞታ ነው፡፡ የማስፋፊያ ሥራም አከናውኖበታል፡፡ በስሙ የተመዘገበ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታም አለው፡፡ ይህ ሕንፃ ፈርሶ ቦታውም በሊዝ ተሸጦ ሌላ አዲስ ሕንፃ ተገንብቶበታል፡፡ ሽያጩ ለልማት በመሆኑ ዕድሩ እንደማይቃወም፣ ነገር ግን ምትክና ካሳ ሊከፈለው እንደሚገባ ጠይቋል፡፡

የዕድሩ ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ፣ ‹‹ባንክ የነበረውን ገንዘብ ዕድሩ አውጥቶ እንዲጠቀምበት ከዕገዳው በፊት በወቅቱ ለነበሩት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ እሳቸውም፣ ‹ገንዘቡን ከማውጣት ይልቅ ፕሮጀክት ቀርፃችሁ አምጡልን፡፡ ፕሮጀክቱን እኛ ተግባራዊ እናደርጋለን› የሚል መልስ ሰጥተውን ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ዕድሩ ለባለሙያ 7,000 ብር ከፍሎ ያስጠናውን ፕሮጀክት ፕሮፖዛል እንዳቀረበላቸው፣ ፕሮጀክቱም ያካተታቸው የመዝናኛ ክበብ፣ ክሊኒክና ቤተ መጻሕፍት እንደነበር፣ በመካከሉ ግን ሚኒስትር ዴኤታው ከቦታው እንደተነሱና ፕሮጀክቱም ተግባራዊ ሳይሆን እንደቀረ አስረድተዋል፡፡

በቀድሞው አዋጅ መሠረት እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ጡረታ የወጡት የቀድሞ ሠራዊት አባላት የጡረታ ካርዳቸውን እያሳዩ ተገቢውን ሕክምና እያገኙና እየተጠሩም ነበር፡፡ ከ1984 ዓ.ም. እስከ 1986 ዓ.ም. የጡረታ ዕድሜያቸው ደርሶ ጡረታ የወጡት የሠራዊቱ አባላትና የፊተኞቹም ወይም የቀድሞዎች ጭምር የጡረታ መብታቸው ቢጠበቅላቸውም ነፃ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብታቸው ግን ተነፍጓቸዋል፡፡ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ የወጡት ደግሞ የጡረታ አበልና ነፃ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብታቸው ተጠብቆላቸዋል፡፡

ባንክ ታግዶ የተቀመጠውን ገንዘብ፣ የጡረታና ነፃ የሕክምና መብቶችንና የመኮንኖች ክበብ በተመለከተ ያነጋገርናቸው በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የፍትሕ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ኪዱ ዓለሙ ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ እሳቸውም በዳይሬክቶሬቱ ውስጥ የተለያዩ ባለሙያዎች እንደተፈራረቁ፣ ጉዳዮቹ ለእሳቸውም አዲስ እንደሆኑባቸውና ምናልባትም ከእሳቸው በፊት በነበሩት አለቆቻቸው ጊዜ የተፈጸሙ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹በተረፈ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታግዶ ቆይቷል የተባለውን ገንዘብ በሕግ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ እስከመጨረሻው የፍትሕ አካል ማለትም እስከ ሰበር ድረስ በማቅረብ ዕልባት ቢያገኝ የተሻለ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ በተረፈ ተቋሙ ገንዘቡን አውጥቶ የሚጠቀምበት አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

የመኮንኖቹን ክበብ በተመለከተ ያላቸውን የግል አቋም ሲገልጹ፣ ቀደም ሲልም ሰዎች መጥተው ንጉሡ የሰጡን ነው ብለዋቸው እንደነበር፣ ንጉሡ እኮ የሰጧችሁ ለእናንተ ለግላችሁ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በየዘመኑ እየተፈራረቁ ለሚመጡና ለሚያገለግሉ መኮንኖች ሁሉ መሆኑ መታወቅ ይገባል በማለት እንደነገሩዋቸው ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ባለፉት ሁለት ሥርዓቶች የነበሩ መኮንኖች እንደተገለገሉበት ሁሉ በአሁኑም ሥርዓት ያሉት መኮንኖች እየተገለገሉበት እንደሚገኙና ወደፊትም ሊኖር በሚችለው ሥርዓት የሚገኙ መኮንኖችም እንደሚገለገሉበት መገንዘብ፣ ከዚህ አኳያ ክበቡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀብት ነው ብሎ ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል በማለት ተናግረዋል፡፡

የቀድሞውም ሆነ አሁን ያለው ማንኛውም ሠራዊት ጡረታ ቢወጣም ነፃ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብት ሊጠበቅላቸው ይገባል የሚል አቋም እንዳላቸው፣ ነገር ግን አገልግሎቱን ከየት ያግኝ የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ እንደሆነ ብርጋዴር ጄኔራል ኪዱ ገልጸዋል፡፡

‹‹በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ይታከም እንዳይባል የመሸከም አቅሙ ውስን መሆን እንደ አንድ ተግዳሮት ይታያል፡፡ መንግሥት ለዚህ ሆስፒታል የሚመድበው በጀት አሁን በአገልግሎት ላይ ያለውን ሠራዊት ታሳቢ ያደረገ ነው እንጂ፣ የቀድሞውን ጦር ሠራዊት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስለኝም›› ብለዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር ብቻ የሚተው ባለመሆኑም መንግሥት መፍትሔ ሊፈልግለት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ እምነት በየአካባቢያቸው በሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች እየቀረቡ እንዲታከሙ ወይም በጤና መድን ፈንድ ታቅፈው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ አማራጭ መፍትሔ ነው፡፡  

የጡረታ ጥያቄ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚኒስቴሩ እየቀረበና ወደ ዳይሬክቶሬቱም እየተገፋ ይመጣ ስለነበር እስኪ ሁኔታው ምን ይመስላል የሚለውን ለማጣራት ባደረጉት ጥረት በ1983 ዓ.ም. ለጡረታ የደረሱ የጡረታ መብታቸው እንደተከበረላቸው ለጡረታ ያልደረሱ ደግሞ በነበረው ሕግ መሠረት ድጎማ እንደተሰጣቸው፣ ይህንን የሰሙት በወሬ ደረጃ እንጂ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹የጡረታ ጊዜው ያልደረሰው በወቅቱ በነበረው የተሃድሶ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ተሰትቷቸዋል የሚል የሰማሁት ነገር አለ፡፡ ይህንን ሊያረጋግጥልኝ የሚችል ሕግና ሰነድ ግን አላገኘሁም፤›› ብለዋል፡፡  

ከመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ቀደም ሲል በሕግ ከተወሰነው የጡረታ መውጫ ዕድሜ በመድረስ፣ በጤና ጉድለት ወይም በሞት ካልሆነ በስተቀር ከ20 ዓመት ያነሰ አገልግሎት ፈፅሞ በሌሎች ምክንያቶች አገልግሎት ካቋረጠ የዘለቄታ ጡረታ አበል ማግኘት አይችልም ነበር፡፡ በተሻሻለው የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 907/2007 መሠረት ግን አዋጁ ከሚፃናበት ቀን አንስቶ ከአሥር መት ያላነሰ አገልግሎት ፈፅሞ በራሱ ፈቃድ ወይም በሌላ በማናቸውም ምክንያት ሥራ ካቋረጠ በሕግ የተወሰነው የጡረታ መውጫ ዕድሜ ሲደርስ የዘለቄታ ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ ልክ እንደሚከፈል ተደንግጓል፡፡

ይህም ሆኖ ግን የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጡረታ መውጫ ዕድሜ የሚወሰነው በመከላከያ ሚኒስቴር መተዳደሪያና ሕግ መሠረት መሆኑን ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የያዘውን ጉዳይ ከምን እንዳደረሰው ጠይቀን፣ የምርመራ ዳይሬክተር ጸሐፊ ወ/ሮ ወሰኔ ሺበሺ ጉዳዩ በባለሙያዎች እየታየና እየተጣራ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ ተጠናቅቆ ውጤቱ ለባለመብቶቹ እንደሚገለጽላቸው አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...