Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ቤታቸውን ራሳቸው እንዲገነቡ የሚያስችል ጥናት ተጀመረ

የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ቤታቸውን ራሳቸው እንዲገነቡ የሚያስችል ጥናት ተጀመረ

ቀን:

በ20/80 እና በ40/60 ቤቶች ግንባታ እየተፈተነ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሒደት ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በመውጣት፣ በአግባቡ እየቆጠቡ የሚገኙ ተመዝጋቢዎች የራሳቸውን ቤቶች እንዲገነቡ መሬት ማቅረብ የሚያስችል ጥናት ጀመረ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጀመራቸው አራት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የሆነውን 10/90 በብቃት ሲያጠናቅቅ፣ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራትም ቤቶቻቸውን እየገነቡ ነው፡፡  

ነገር ግን የ20/80 እና የ40/60 ቤቶች ፕሮግራሞች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ መጓዝ ባለመቻላቸው ለአስተዳደሩ ፈተና ከመሆናቸው ባሻገር፣ ተመዝግበው ለሚጠባበቁ ነዋሪዎች ሕልም ሆነዋል፡፡  

- Advertisement -

አስተዳደሩ ራሱን ከዚህ ችግር ለማውጣት አዲስ ጥናት የጀመረ ሲሆን፣ የጥናቱ ማጠንጠኛ ቤት እየሠራ ከማቅረብ ይልቅ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት ለነዋሪዎች ማቅረብ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

ጥናቱ እየተካሄደ የሚገኘው በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሥር በሚገኘው የኅብረት ሥራ ማደራጃ ኤጀንሲና በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ዜጎች አማራጭ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እንዲኖራቸው የሚያስችል ጥናት በጋራ እየተካሄደ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የጥናቱ የመጀመርያ ረቂቅ ተጠናቋል፡፡ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት አስተያየት እንዲሰጡበት ረቂቅ ጥናቱ መላኩ ታውቋል፡፡

ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ለሚመራው የከተማው አስተዳደር ካቢኔ ቀርቦ ሲፀድቅ በይፋ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ውስን ሀብት ነው ከሚለው አቋሙ በተጨማሪ፣ ለመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች መሬት ሸንሽኖ በማቅረብ የመኖሪያ ቤት ችግር አይፈታም የሚል አቋም ሲያራምድ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረት ኢሕአዴግ መራሹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ 13 ዓመታት ዘግይቶ በ1996 ዓ.ም. የመኖሪያ ቤት ግንባታ ውስጥ በስፋት ገብቷል፡፡

ነገር ግን በወቅቱ የተጀመሩ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ከምርጫ 97 ማግሥት በተከሰተው ቀውስ ሳቢያ በታቀደላቸው ጊዜ ውስጥ መካሄድ አልቻሉም ነበር፡፡

በዚያ ወቅት ከ400 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ ቢሆንም፣ እነዚህ ነዋሪዎች ባለፉት 15 ዓመታት ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት መሆን አልቻሉም፡፡

በነሐሴ 2005 ዓ.ም. በአራት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ቢመዘገቡም፣ በአጠቃላይ ባለፉት 15 ዓመታት ለነዋሪዎች የተላለፉት የመኖሪያ ቤቶች ግን 200 ሺሕ ያህል ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በ20/80 ቤቶች ፕሮግራም 94,114 ቤቶች፣ በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ደግሞ 38,240 ቤቶች፣ በድምሩ 132,354 ቤቶች በግንባታ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ቤቶችም ቢሆኑ በሚፈለገው ፍጥነት እየተገነቡ አይደሉም፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተካሄደው ምዝገባ 100 ማኅበራት የተቋቋሙ ሲሆን፣ ቦታ ተረክበው የራሳቸውን ቤት በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ሁለት ሺሕ ነባር የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲገኙ፣ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ሺሕ ቤቶችን በመገንባት ላይ መሆናቸው ይነገራል፡፡

ቀጣዩ የአስተዳደሩ ትኩረት በ20/80 እና በ40/60 የተመዘገቡ ነዋሪዎች በማኅበራት ተደራጅተው፣ የራሳቸውን ቤት ራሳቸው እንዲገነቡ ማመቻቸት ነው ተብሏል፡፡

አስተዳደሩ እነዚህን ቤቶች ካጠናቀቀ በኋላ ቀጣይ ትኩረቱን ተመዝጋቢዎች የራሳቸውን ቤት ራሳቸው እንዲሠሩ ቦታ ማቅረብ ላይ ይሆናል ተብሏል፡፡ ጥናቱ እየተካሄደ የሚገኘው በካቢኔው ይሁንታ ቢሆንም፣ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታው የሚወሰነውም በካቢኔው ይሆናል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...