Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትኩረት የሚሻው የትራንስፖርት አገልግሎት

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት ያለበት ችግር እየተፈታ አይደለም፡፡ የትራንስፖርት እጥረቱ ዛሬም ተገልጋዮች የሚማረሩበት ነው፡፡ ዘርፉን ለማዘመን ተብሎ እየተወሰዱ ያሉ አንዳንድ ዕርምጃዎች መልካም ናቸው ቢባልም፣ ትግበራው ላይ የታዩ ስንክሳሮች የትራንስፖርት አገልግሎቱን የበለጠ እያወሳሰቡት ነው ማለት ይቻላል፡፡

መንግሥት የትራንስፖርት ችግሩን ለመቅረፍ የባንክ ብድር በማመቻቸት ከቀረጥ ነፃ የሆኑ  ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ማድረጉ እንደመልካም የታየ ቢሆንም፣ ተሽከርካሪዎቹ ከገቡ በኋላ መንግሥት ባስቀመጠው ታሪፍ አልሠራም ማለታቸው አነጋጋሪ ነበር፡፡ ይህም ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ የኅብረተሰቡና የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቃለል ወይም በተወሰነ ደረጃ ለማስተንፈስ ይረዳሉ ተብለው የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው፣ የመንግሥት ቀረጥ ቀርቶ እንዲገቡ የተደረጉት የሜትር ታክሲዎች እስካሁን ድረስ በታሰበው ልክ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ችግር የአገልግሎት ዋጋ ነው፡፡ የአገልግሎት ዋጋቸውን በሚመለከት የተፈጠረውን አለመግባባት ፈትቶ ሥራ ቢጀምሩ በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በተቻለ ነበር፡፡ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ተብሎ በየታክሲዎቹ ውስጥ የተገጠመው ዘመናዊ ኪሎ ሜትር መቁጠሪያና ዋጋ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ጌጥ ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የትራንስፖርት አገልግሎት አስተዳደሩ ችግር ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ሀብትን በአግባቡ ያለመጠቀም ነውም ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ ረገድ አንድ ውሳኔ ተሰጥቶ በአገር ገንዘብ የተገዙ ሜትር ታክሲዎች የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት ሳይችሉ ቀርተው በዘፈቀደ እየሠሩ ነው፡፡ የተፈለገውን ዓላማ ካላሳኩ ደግሞ ቀድሞውም በሚገባ እንዳልታሰበበት ያሳያል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከቀረጥ ነፃ ብድር አግኝተው የባንክ ብድር ከተመቻቸላቸው ሌላ በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉና በአሮጌ ታክሲ ገባ ወጣ የሚሉ ባለንብረቶች ዕድሉን እንዲያገኙ አለመደረጉና አሠራሩ ለተወሰኑ ብቻ ተሰጥቶ መቆሙ በራሱ የጠራ የአሠራር ሥርዓት የሌለ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በእርግጥ ለአሮጌ ታክሲ ባለቤቶች ይኼንን ዕድል እንዲያገኙ በማኅበር እንዲደራጁ ቢደረግም፣ ሳይሆን ቀርቷል ወይም ቁርጥ ያለ ውሳኔ ሳይሰጥበት በእንጥልጥል ላይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ለአንዱ ሰጥቶ ለሌላው መከልከል ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ጤናማ ውድድር እንዳይኖር በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦው ቀላል አይሆንም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን የተጀመሩና በመጀመር ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ ይህም የትራንስፖርት አገልግሎትን በአንድ የጥሪ ማዕከል በማድረግ በፈጣንና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ነው፡፡ አገልግሎቱ ዘመናዊና ወጪ ቆጣቢ ከመሆኑ ባሻገር ተጠቃሚዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ያለሥጋት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስችላል፡፡

እንዲህ ያለው አገልግሎት መጀመሩ ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም፡፡ በከተማይቱ ያሉ ነዋሪዎች ዋነኛ ችግር የሆነውን የትራንስፖርት አገልግሎት እንደዚህ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት፣ በመንግሥት በኩል ተገቢው ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡ በከተማይቱ በአሮጌ ታክሲዎች አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችም በተለይ ከፋይናንስ ተቋማት ተገቢው ድጋፍ እየተደረገላቸው የትራንስፖርት አገልግሎቱን ቢያጎለብቱ እሰየው ያስብላል፡፡

በዓለም ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ኡበር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ ይህ የትራንስፖርት አገልግሎት ማንኛውም ዜጋ ባለው ተሽከርካሪ፣ በመጠቀም የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚችልበትን አሠራር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያቀርባል፡፡ ይህ አገልግሎት የበርካቶችን የትራንስፖርት ችግር ከማቃለሉ ባሻገር ተገልጋዮች ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲከፍሉ በማድረግ በብዙዎቹ ተመራጭ ነው፡፡ ይህ የኡበር የትራንስፖርት አገልግሎትም ምንም እንኳን ወደ አገራችን ባይገባም፣ በተለያዩ አገሮች ዝናው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በአገራችንም ተመሳሳይ ሊባል በሚልችል መልኩ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ተቋማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ልክ እንደ ኡበር የግለሰብ የአሽከርካሪ ባለቤቶችን ሳይሆን በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ የንግድ ተሽከርካሪዎችን ይዘው ለትራንስፖርት ችግሩ መፍትሔ ለመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ዓለማችን እየዘመነች በምትሄበት በዚህ ወቅት እንደዚህ ዓይነቶቹ የትራንስፖርት አገልግሎቶች የበለጠ ተጠናክረው እንዲሄዱ የሚመለከተው አካል ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ እዚህ ጋር ከአገልግሎቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የሕግ ክፍተቶች ካሉም እነዛን ክፍተቶች ሞልቶ ይህን ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ማጠናከር አማራጭ የለውም፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር በሚሰቃዩበት በዚህ ወቅት፣ የትራንስፖርቱን ዘርፍ በማዘመን ሌሎች አገሮች ውስጥ የሚሠሩ ዘመናዊ ቢዝነስ ወደ አገራችን ማስገባታችን አማራጭ የለውም፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አዳዲስ የትራንስፖርት ዘርፎች ለተጠቃሚዎች ከሚሰጡት ጠቀሜታ በተጓዳኝ ለዜጎች የሥራ ዕድልም ስለሚፈጥሩ ይበሉ የሚያሰኝ ነው፡፡ ሆኖም በዘርፉ ያሉትንም አገልግሎት ሰጪዎች ችግር በመቅረፍ ወደዚህ ዘመናዊ ሥርዓት እንዲቀላቀሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ እንደዚህ ዓይነት አገልግሎቶች ለተጠቃሚዎች ደኅንነት ያላቸው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም ተጠቃሚዎች በተመዘገቡ አሽከርካሪዎች ስለሚንቀሳቀሱ በአሽከርካሪዎቹ የሚፈጸመው ወንጀል ይቀንሳል፡፡

ስለትራንስፖርት ጉዳይ ካነሳን ሌላው የምንጠቅሰው ነገር የታክሲ ስምሪትና የተጓዦች ደኅንነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጠበቅ ብሎ የነበረው ቁጥጥር ላልቷል፡፡ ተገልጋዮቹ ከታሪፍ በላይ ይጠይቃሉ፡፡ ከታሪፍ በላይ መጠየቃቸው ሳያንስ በአንድ ሚኒባስ ውስጥ 20 ተሳታፊዎች እንዲጓዙ መደረጉ ራሱ በዘርፉ ያለውን ችግር ያሳያል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን የተመለከቱ አሠራሮች እንደገና መፈተሽ አለባቸው፡፡

ሌላው ደግሞ የከተማ የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የአውቶቢሶችን ቁጥር ለማሳደግ ታስቦ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እነዚህ አውቶቢሶች ብቻ የሚጓዙበት መንገድ እንዲለይ ተደርጎ ይሠራል ተብሏል፡፡ ነገር ግን ይኼንን የተለየ መስመር ሥራ ማስጀመር አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ጀሞ ድረስ ለአውቶብሶች ተብሎ በቀለም የተለየው መንገድ ለታሰበለበት ዓላማ ማዋል አልተቻለም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሆኖ ሳለ ለአውቶብሶቹ የተሳናዳውን ቦታ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል የተደረገበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ አገልግሎቱ ካልተሰጠበት ለምንስ ተሠራ፡፡

ይኼን መስመር ለመለየት ግን ብዙ ተለፍቷል፡፡ አስፖልቱ ቀለም ጠጥቷል፡፡ በአጭሩ ወጪ ወጥቶበታል፡፡ አገልግሎቱ እንዴት እንደሚሰጥ አገልግሎቱን መስጠት ያለባቸው እነማን ናቸው የሚሉትንና በተለይ አሁን ላይ ብሶት እየፈጠሩ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ማጥራት ግድ ይላል፡፡ በአጠቃላይ የትራንስፖርት ሥርዓቱን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ መዲናችን የአፍሪካ ኅብረትና የተለያዩ የዲፕሎማት ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ዘመናዊና ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊኖራት ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት