Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ከቻይና ከምታገኘው ጥቅል ብድር ውስጥ የዕርዳታ ምጣኔው ከፍ ተደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ከቻይና መንግሥት ከሚገኝ ጥቅል ኮንሴሽናል ብድር ውስጥ የዕርዳታ ምጣኔው ከፍ ተደረገላት፡፡ ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ አዲስ የኮንሴሽናል ብድር ሥሌት ተግባራዊ ማድረጓ ታውቋል፡፡

በዚህ መሠረት ቻይና ከዚህ ቀደም የምትሰጠው ኮንሴሽናል የብድር ድጋፍ ሥሌት 27 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ ሥሌት የኮንሴሽናል ብድር የድጋፍ ሥሌት 35 በመቶ ሆኗል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የኢትዮ ቻይና የልማት ትብብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ታደሰ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ቻይና የኮንሴሽናል ብድር የድጋፍ ምጣኔን ከ27 በመቶ ወደ 35 በመቶ ከፍ አድርጋለች፡፡ የውሳኔ ደብዳቤውም ለሚኒስቴሩ ደርሷል፡፡

ኮንሴሽናል ብድር ቀለል ያለ ወለድ የሚከፈልበት መሆኑን፣ በተራዘመ ጊዜ ተከፍሎ የሚያልቅና መጠነኛ ጫና ያለው የብድር ዓይነት ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ በዚህ ዓይነቱ ብድር ውስጥ በዕርዳታ መልክ የሚሰጥ የገንዘብ መጠን ይካትታል ብለዋል፡፡

አቶ ጥላሁን እንደገለጹት፣ በዚህ የብድር ዓይነት ውስጥ የዕርዳታ አሰጣጥ አሠራር አለ፡፡ በዚህ መሠረት ለሚመረጡ ፕሮጀክቶች 35 በመቶ የሚደርስ ዕርዳታ ይኖራል፡፡

‹‹ከገበያ (ኮሜርሻል) ብድር አንፃር ኮንሴሽናል ብድር የተሻለ ነው፡፡ ጠቀሜታውም የጎላ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹የቻይና መንግሥት ይህን ያደረገው የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ካስቀመጠው 35 በመቶ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ጥላሁን አክለው እንደገለጹት፣ ይህ ጥያቄ በኢትዮጵያና በሌሎች አፍሪካ አገሮች ሲቀርብ ስለነበር አሁን ምላሽ አግኝቷል፡፡

26 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ያለባት ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. በዝቅተኛ እርከን ላይ ከሚገኙ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት፣ ከልማት አጋሮች አሁንም ከፍተኛ ብድርና ዕርዳታ ትፈልጋለች፡፡

በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኘው ቻይና በዓለም ሁለተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ ናት፡፡

ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ከመሠረተቻቸው የሁለትዮሽ ትብብሮች ስምምነቶች ባሻገር፣ በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም አማካይነት ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጓ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያና የቻይና ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በግንቦት 2010 ዓ.ም. በቤጂንግ ከተካሄደው የ‹‹ቤልትና ሮድ›› ፎረም ጎን ለጎን የሁለቱ አገሮች መሪዎች ባካሄዱት የጎንዮሽ ውይይት፣ የኢትዮ ቻይና የልማት ትብብር ወደ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሸጋገሩ ተመልክቷል፡፡

ባለፉት 17 ዓመታት ቻይና ለአፍሪካ አገሮች 125 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታና ብድር መስጠቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ቻይና በቀጣዮቹ ዓመታት 60 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ አገሮች ለማቅረብ ዕቅድ መያዟ ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች