Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደኅንነትና በፀጥታ ተቋማት የሚያገለግሉ የፓርቲ አመራሮች ሊነሱ እንደሚችሉ ተጠቆመ

በደኅንነትና በፀጥታ ተቋማት የሚያገለግሉ የፓርቲ አመራሮች ሊነሱ እንደሚችሉ ተጠቆመ

ቀን:

ተቋማቱ ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆነው በድጋሚ ይዋቀራሉ

በብሔራዊ ደኅንነትና በሕግ አስከባሪ የፌዴራል ተቋማት ውስጥ በአመራርነትም ሆነ በአባልነት በማገልገል ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሊነሱ እንደሚችሉ የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የኢሕአዴግ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ በስፋት ተወያይቶ መግባባቱን፣ እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነትና ሕግ አስከባሪ የፀጥታ ተቋማት አደረጃጀት ከፖለቲካ የፀዳ ሆኖ በድጋሚ እንዲዋቀር መወሰኑን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር ያገኘው የ11ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ሪፖርትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሰነድም ይኼንኑ ያረጋግጣል፡፡

ሰነዱ ‹‹የ11ኛው ጉባዔ ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርዕስና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ማጠናከር በሚያትተው ንዑስ ሥር፣ ‹‹የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዱ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የአገር ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቁ የአገር ኩራትና መመኪያ ሆነው እንዲቀጥሉ ይሠራል፤›› ሲሉ ቀጣይ አቅጣጫ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ይኼንና ሌሎች በየዘርፉ የተቀመጡ ዝርዝር የቀጣይ ዓመታት አቅጣጫዎችን የያዘው ሰነድ በኢሕአዴግ ጉባዔ ዓርብ መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ፀድቋል፡፡

በተጠቀሱት ተቋማት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የፖለቲካ መስመራቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ከተቋማቱ መገለል የሚገባቸው መሆኑን፣ በተቋማቱ የተዋረድ እርከኖች የሚገኙ ደግሞ ከሙያቸው ወይም ከፖለቲካ አንዱን እንዲመርጡ በማድረግ ተቋማቱን በድጋሚ የማደራጀት ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ምክክር ተደርጎ መወሰኑን በጉባዔው የተሳተፉ ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በድጋሚ የሚዋቀሩት የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት ራሳቸውን የቻሉ ሙያዊ ተቋም እንዲሆኑና በሚኒስቴር ደረጃ እንደ አዲስ ለሚቋቋመው የሰላምና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ተቋማቱ ተጠሪ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ዘይኑ ጀማል ደኢሕዴንን በመወከል የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን ከሳምንት በፊት የተመረጡ ሲሆን፣ የእሳቸው ምክትል የሆኑት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ መላኩ ፈንታም በተመሳሳይ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን (ኦዴፓ) በመወከል የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ኦዴፓን በመወከል የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴን የተቀላቀሉ ሲሆን፣ በዚሁ ተቋም በምክትል ዳይሬክተርነት በማገልገል ላይ የሚገኙት የቀድሞው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አሰፋ አብዩ ደኢሕዴንን በመወከል የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ከእነዚህ የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት አመራሮች ውስጥ ሦስቱ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ ላይ ሲሳተፉ እንደነበሩም ሪፖርተር ማረጋገጥ ችሏል፡፡

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አደም መሐመድ፣ ተቋሙ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ እንዲሆን የሕግ ማሻሻል ሥራ መጀመሩንና በተቋሙ ውስጥ ለመቀጠል የፖለቲካ አባል አለመሆን መመዘኛ ሆኖ በማቋቋሚያ ሕጉ እንዲካተት የሚደረግ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ማንም ሰው የፖለቲካ አመለካከት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ በዚህ ተቋም ውስጥ መቀጠል አይቻልም፡፡ ይህ አዲስ ለሚመለመሉም ሆነ በነባር የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፤›› ሲሉ አስታውቀው ነበር፡፡

ክልከላው የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆንን ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲን በይፋ መደገፍና ቅስቀሳዎችን ማድረግና የፖለቲካ አመለካከትን በተመሳሳይ በይፋ ማንፀባረቅን አካቶ በሕግ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የሕግ ማሻሻያዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፀድቀው ተግባራዊ እንደሚደረጉም ጄኔራል አደም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ተቋማትን በድጋሚ ለማዋቀር የተረቀቀው አዋጅ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...