Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ማመላለሻ ባለንብረቶች በ15 ቀናት ውስጥ የታሪፍ ማሻሻያ ካልተደረገ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚመቱ አስጠነቀቁ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ነዳጅ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበር፣ መንግሥት በ15 ቀናት ውስጥ የታሪፍ ማሻሻያ ካላደረገ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚመታ አስጠነቀቀ፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበር፣ ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ስታዲዮም አካባቢ በሚገኘው ትራንስፖርት ባለሥልጣን አዳራሽ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግ ቢወተውትም፣ ተገቢው ምላሽ ባለማገኘቱ አባላቱ ለኪሳራ መዳረጋቸውን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

የማኅበሩ አባላት የታሪፍ ጭማሪ ካልተደረገ በቀር በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይችሉ፣ ሥራ ለማቆም እንደሚገደዱ በስብሰባው ወቅት አስታውቀዋል፡፡

ተሰብሳቢዎቹም ሆነ የማኅበሩ አመራሮች መንግሥት በ15 ቀናት ውስጥ የታሪፍ ማሻሻያ ካላደረገ ሥራ ለማቆም የተስማሙ ሲሆን፣ የማኅበሩ አባል የሆኑ የነዳጅ ትራንስፖርት ባለቤቶች ለስብሰባ ተሳታፊዎች በተዘጋጀው ሊስት ላይ ያኖሩት ፊርማ ከመሸኛ ደብዳቤ ጋር ተያይዞ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲቀርብ በጭብጨባ አፅድቀዋል፡፡

በዚህ መሠረት ማኅበሩ ደብዳቤውን ለማስገባት ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ ደብዳቤው ከገባበት ቀን ጀምሮ ታሳቢ በሚሆን 15 ቀናት ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠ የነዳጅ ባለንብረቶች ነዳጅ ከማጓጓዝ እንደሚቆጠቡ አስታውቋል፡፡  

በኢትዮጵያ የነዳጅ ትራንስፖርት ማጓጓዣ ታሪፍ በመንግሥት መመራት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ታሪፍ የሚተመነው የነዳጅና ቅባት፣ የባንክ ወለድ፣ የኢንሹራንስ (የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪ)፣ የጎማ፣ የመለዋወጫ፣ የደመወዝና ሌሎች ወጪዎች ላይ መጠነኛ ትርፍ በማከል ነው፡፡

ይህ የታሪፍ ሥሌት የፍሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማኅበር ተወካዮችና የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጋራ ሲያፀድቅ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

ማኅበሩ እንደሚገልጸው ይህ አሠራር ምንም የጎደለው ነገር ባይኖርም፣ ጊዜውን እየጠበቀ ታሪፍ መስተካከል ሲኖርበት ዛሬ ነገ እየተባለ ዓመታት በማስቆጠሩ ባለንብረቶች ለዕዳ ተዳርገዋል፡፡

‹‹ከሦስት ዓመታት በፊት ትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ የነዳጅ ማጓጓዣ ባለንብረት ተወካዮች በተገኙበት የታሪፍ ጥናት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተላልፏል እየተባለ ምንም ምላሽ ሳይገኝ ቀርቷል፤›› ሲል ማኅበሩ ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በላከው ደብዳቤ ገልጿል፡፡

ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በላከው ደብዳቤ ጨምሮ እንደገለጸው፣ ባለፉ ሦስት ዓመታት በውጭ ምንዛሪና በኢትዮጵያ ብር መካከል በተደረገው ተከታታይ የምንዛሪ ለውጥ ምክንያት የዕቃዎች ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጭማሪ አሳይቷል፡፡

‹‹ምንም እንኳን የነዳጅ ዋጋ ላይ የተደረገ የዋጋ ለውጥ ባይኖርም ከነዳጅ ውጪ ባሉ እንደ ጎማ፣ የባንክ ወለድ፣ ዘይትና ቅባት፣ ኢንሹራንስ (የተሽከርካሪና የነዳጅ)፣ የመለዋወጫና የጥገና ክፍያ፣ የባትሪ፣ የጂቡቲ መግቢያ፣ የሠራተኞች ደመወዝና አበል፣ የቢሮ ኪራይና ሌሎች ወጪዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ቀደም ሲል በነበረው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ከፍተኛ መሆኑን፣ ከሚመለከታቸው ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ ባዘጋጀነው ሰነድ አረጋግጠን፣ የታሪፍ ማስተካከያውን በመጠባበቅ ላይ ነበርን፤›› በማለት ማኅበሩ ለረዥም ጊዜ ታግሶ መቆየቱን በደብዳቤው አብራርቷል፡፡

ማኅበሩ እንደገለጸው በ2010 ዓ.ም. መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም በ15 በመቶ ዝቅ ሲያደርግ፣ መንግሥታዊና የግል ባንኮች የቁጠባና የብድር ወለድ መጠናቸውን ጨምረዋል፡፡

‹‹የተለያዩ መለዋወጫዎች መቶ በመቶ፣ ጎማ በ87 በመቶ፣ ደመወዝና አበል በ50 በመቶ፣ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በ43 በመቶ፣ የባንክ ወለድ በ28 በመቶና ኢንሹራንስ 25 በመቶ የጨመሩ ቢሆንም፣ በነዳጅ ማመላለሻ ታሪፍ ላይ ግን ለውጥ አልተደረገም፤›› በማለት ማኅበሩ የችግሩን ስፋት አስረድቷል፡፡

በዕቃና በአገልግሎት ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ባስከተለው ኪሳራ ምክንያት ብዙዎች የፍሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ ባለቤቶች ወርኃዊ የባንክ ክፍያ፣ ከላይ የተጠቀሱት ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የተከሰተውን የዋጋ ንረት መቋቋም አለመቻላቸውን ማኅበሩ ገልጿል፡፡

‹‹ከፊሎቹ ንብረታቸውን እስከመሸጥ የደረሱ ሲሆን፣ ቤት ንብረት የሌላቸው ደግሞ ተሽከሪዎቻቸውን በየጋራዥና በተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራ አስቀምጠው የሐራጅ ሽያጭ በመጠባቅ ላይ ይገኛሉ፤›› በማለት ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታውን አቅርቦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋ አሳመረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ ባለመገኘቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለመንግሥት ያቀርባል፡፡ ምላሽ ካልተገኘ ግን ሥራ ማቆምና ሰላማዊ ሠልፍ ማካሄድ ቀጣዮቹ ዕርምጃዎች ናቸው በማለት አስረድተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች