Wednesday, April 17, 2024

የኢሕአዴግ ጉባዔ ቀይ መስመሮችና የወደፊት አቅጣጫዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከቅርብ  ዓመታት ወዲህ በተፈጠረ የፖለቲካ ቀውስ በአገሪቱና በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላይ ያንዣበበው የመበተን አደጋ በመስከን የመጥራት ምልክትን በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል የመደፍረስ ምልክትን እያሳየ በሚገኝበት ወቅት የግንባሩ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የኢሕአዴግ ጉባዔ ሰሞኑን ለ11ኛ ጊዜ በሐዋሳ ከተማ ለሦስት ቀናት ተካሂዶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ተከስቶ በነበረው የማኅበረሰቦች ግጭትና አሰቃቂ ግድያ ምክንያት  ከፍርኃት ውስጥ ሳትወጣ፣ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት እዚያ መክተማቸው አንፃራዊ መነቃቃትን ፈጥሮላታል፡፡ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ በአንፃራዊ መረጋጋት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዲችሉ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ይሁን እንጂ የኢሕአዴግ ጉባዔ በከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ውስጥ ሆኖ ነበር የተጠናቀቀው፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በከፍተኛ የደኅንነት ጥበቃ ውስጥ የጉባዔውን ቀናት ሲያሳልፉ፣ ሌሎች ጉባዔተኞች ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ለመግባት አራት ዙር ፍተሻዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ምንም ዓይነት የኤሌክትሮኒክ መገልገያ ቁሶች፣ የሞባይል ስልክን ጨምሮ የተሽከርካሪዎቻቸውን ቁልፍ ይዘው አዳራሹ የሚገኙበት ግቢ መግባት አይችሉም ነበር፡፡

የመጻፊያ ብዕር የያዘ ጉባዔተኛ የሚጽፍ መሆኑን፣ በጥበቃና በፍተሻ ላይ ለነበሩት አባላት በመጻፍ ማረጋገጥ ይጠበቅበት ነበር፡፡

ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ያረፉበት ኃይሌ ሪዞርት ሆቴል ላለፉት ቀናት ሌሎች ደንበኞችን ማስተናገድ ካለመቻሉም በላይ፣ ከሪዞርቱ አጠገብ የተንጣለለው የሐዋሳ ሐይቅ ዙሪያም በወታደሮች የተከበበ ነበር፡፡

የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲጀምር የነበረው ድባብ ከላይ የተገለጸውን ይመስል ነበር፡፡

የጉባዔው የመጀመርያ ቀን ሙሉ በሙሉ የጉባዔው መክፈቻ ቀን ሆኖ የግንባሩን ሊቀመንበር፣ የአጋርና ተፎካከሪ ፓርቲዎችን፣ እንዲሁም የውጭ መንግሥታትና ወዳጅ ፓርቲዎች ተወካዮች መልዕክቶቻቸውን ያስተላለፉበት ነበር፡፡

በተቀሩት ሁለት ቀናት ደግሞ አገሪቱ ያለፈችባቸው ያለፉት ሦስት ዓመታት የፖለቲካ ሁኔታዎችና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን የተመለከተ ውይይትና ግምገማ ከተደረጉ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን የያዙ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡

ያለፉት ዓመታት ፖለቲካዊ ክስተቶች ግምገማ

11ኛው ጉባዔ በ10ኛው የግንባሩ ጉባዔ የተቀመጡ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት አፈጻጸምና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን በትኩረትና ሰፊ ጊዜ በመስጠት መገምገሙን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡ የጉባዔው ቃል አቀባይ ሆነው የተመረጡት የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ይኼንኑ አረጋግጠዋል፡፡

በጉባዔው የመወያያ ሰነድ ሆነው ከቀረቡት መካከል አንዱ የሆነው የኢሕአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ሪፖርትም፣ ያለፉት ዓመታት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አመላክቷል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው ይህ ሰነድ በ10ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም የተዛነፈ መሆን በአገሪቱ ለተፈጠረው አለመረጋጋትና ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት መሆኑን ያስረዳል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ከምንጫቸው በማድረቅ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እጅግ ወሳኝ መሆኑ በ10ኛው ጉባዔ በግልጽ የተቀመጠ አቅጣጫ የነበረ ቢሆንም፣ በቁርጠኝነት ባለመፈጸሙ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ሙስናን ከምንጩ በማድረቅ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመምጣቱን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

በዚህም ምክንያት ለኢሕአዴግ ህልውና ፈተና መሆኑን አስረግጦ ይገልጻል፡፡ ችግሩ ሰፊና ጥልቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው የሚገኝ አመራር ከተለመደው አሠራርና አካሄድ ያልተላቀቀ በመሆኑ ጭምር የተፈጠረ እንደሆነም የሪፖርቱ ግምገማ ያስነገዝባል፡፡

‹‹የሪፎርም ሥራዎች ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ መሠረታዊ ለውጥ አላመጡም፡፡ የልማታዊ መንግሥት ተልዕኮን የሚመጥን የሲቪል ሰርቪስ አልተገነባም፡፡ የዕውቀት፣ የአመለካከትና የክህሎት ጉድለቶች በስፋት የሚታዩበት ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓት ሪፎርም ሥራ ተወስዶ ሲታይ ተመሳሳይ ችግር ሆኖ የሚታይበት ሆኖ በራሱ ባህርይ ሲመዘን የሕግ የበላይነትን ማስከበር የተሳነው፣ አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ድርጊቶችን ማስቀረት ያልቻለ፣ ወንጀል የመከላከል ሥራውም ደካማና ግጭቶችን በአግባቡ የመያዝ አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑ ታይቷል፤›› በማለት ችግሮቹን ያመለክታል፡፡

በኢሕአዴግ ውስጠ ዴሞክራሲ እንዲጠናከር በ10ኛው ጉባዔ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር የሚያስታውሰው ሪፖርቱ፣ አፈጻጸሙ በተቃራኒው በሚባል ደረጃ እንደነበር ያመለክታል፡፡

የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲያዊ ትግል የተዳከመበት ወቅት እንደነበር፣ የአመራር ነፃና ግልጽ ተሳትፎና የተሟሟቀ የሐሳብ ውይይት የጠፋበት፣ የሐሳብ ልዩነት ያለማስተናገድ፣ ሐሳቦችን ማፈን፣ ቂም መቋጠር፣ ሐሜትና አሉባልታ የተበራከተበት እንደነበር ሪፖርቱ ይገመግማል፡፡

በመርህ ላይ ያልተመሠረተ ትግል ማካሄድ፣ ይኼንን ተከትሎም የአመራሩ ጓዳዊ ግንኙነት በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑ፣ ከተግባር የተነጠሉ ግምገማዎች እየሰፉ በመምጣታቸው ምክንያት የግል ሐሳብን የማይደግፉ አመራሮች ማጥቃት፣ በመርህ አልባ ግንኙነት መጠቃቀም የተስተዋለባቸው ዓመታት እንደነበሩ ይጠቅሳል፡፡

የድርጅቱ ግምገማዎች፣ እንዲሁም ሒስና ግለ ሒስ ለግንባታ መሆናቸው ቀርቶ የማስፈራሪያና ማጥቂያ መንገድ እየሆኑ መምጣታቸውንም ይገልጻል፡፡

‹‹ስለሆነም ድርጅቱ በውስጡ ጠንካራ ዴሞክራሲ ሳይሰፍን ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሊገነባ አይችልም፤›› ሲል የችግሩን ጥልቀት አመላክቷል፡፡

የድርጅቱ አመራርና አባላት ለሚታገሉለት ዓላማ ስኬታማነት ለየትግል ምዕራፉ የሚመጥን የፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ብቃትና ሥነ ምግባር ሊኖራቸው የግድ ቢሆንም፣ የአመራሩና የአባላቱ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ብቃት ችግሮችን በመሠረታዊነት የሚፈታ አለመሆኑን፣ በዚህም ረገድ የግንባታ ሥራ አለመከናወኑን ያትታል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የድርጅት አመራር አባላትና አደረጃጀቶች ተልዕኳቸውን በብቃት ለመፈጸም ከሚችሉበት ቁመና ላይ አለመድረሳቸውን፣ በተለይም የሕዋስና የመሠረታዊ ድርጅቶች በእጅጉ የተዳከሙ መሆናቸውን ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡

የአባላት ምልመላ ሥራው ጥራት የሌለው፣ ከድርጅቱ ጥቅም ፈልጎ የሚመጣውን ሁሉ አሠራሩን ሳይከተሉ የመቀበል፣ በተጨማሪም ከምልመላው የጥራት ችግር ባሻገር አባላት ድርጅቱን በብዛት የሚለቁበት ሁኔታ መፈጠሩን ያብራራል፡፡

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወዲህ

በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ከሕዝቡ በተነሳ ቅሬታና ቁጣ ተገፍቶ ኢሕአዴግ በአዲስ ሁኔታ በጀመረው ጥልቅ ተሃድሶና የአመራር ለውጥ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ ያሳደሩ ለውጦች መመዝገባቸውን የኢሕአደግ 11ኛ ጉባዔ መገምገሙን ቃል አቀባዩ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገልጸዋል፡፡

በአመራር ለውጡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የድርጅቱን አመራር እንደገና በማደራጀት፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ፣ እንዲሁም የተለያዩ የለውጥ ተግባራት መፈጸም በመጀመራቸው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረበት ሁኔታ መታየት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግና መንግሥት አገሪቱ የገባችበትን አጣብቂኝ በጥሞና በመገምገም የወሰዱት ዕርምጃ ተጨባጭ ለውጦችን በማምጣት አገሪቱ ከአስከፊ ውድቀትና ሕዝቦችን ከመከፋፈል አደጋ በማውጣት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

የጉባዔው ቀይ መስመርና ቀይ አቅጣጫዎች

የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ ድርጅቱ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከተጀመረው ለውጥ ጋር በማቆራኘት ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡ ከውይይቱ በኋላም ዝርዝር ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

እነዚህም ትኩረት ሰጥቷቸው የሚተገበሩ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሲሆኑ፣ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ጉባዔው የድርጅቱ የማይታለፉ ቀይ መስመሮች ናቸው ያላቸውን አስታውቋል፡፡

ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶች ለቆመለት ዓላማ ታማኝና ዙሪያ መለስ መስዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ የሆኑ አባላትን ብቻ በማስቀረት አድርባይ አባላትን የማጥራት፣ አባላትን የመመልመልና የመገንባት ሥራ እንዲከናወን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

‹‹የመጨረሻው ዘመን ኢሕአዴግን ለመፍጠር የአባላት የእርስ በርስ ቅንጅት በመፍጠር፣ በማነሳሳትና በማዋሀድ የላቀ ድምር ውጤት የሚያስመዘግብ ብቃት ያለው የአመራር ስብስብ ለማምጣት ይሠራል፤›› በማለት የጉባዔው ቀጣይ አቅጣጫ ሰነድ ያስረዳል፡፡

ከላይ የተገለጸውን በተመለከተ በሥፍራው ለሚገኙ ጋዜጠኞች የጉባዔው ቃል አቀባይ አቶ ፍቃዱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያው መሠረት ቀይ መስመር ተብለው ከተለዩት መካከል አንዱ፣ የተደራጀ ሌብነትና ዘረፋን ኢሕአዴግ ከአሁን በኋላ እንደማይታገስና ይህም ቀይ መስመር ሆኖ ተለይቷል፡፡

ልግመኝነትና ውጤት አልባነት ሌላው በቀይ መስመርነት ተለይቶ የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ውጤት አልባነት፣ ውጤት የማያስመዘግብ አመራር፣ ውጤት የማያስመዘግብ ፓርቲ ወይም የፓርቲ መዋቅር ከዚህ በኋላ በኢሕአዴግ ውስጥ መቀጠል አይችልም፤›› ሲሉ የተቀመጠውን ቀይ መስመር ማለፍ የሚያስከትለውን ውጤት አብራርተዋል፡፡

ሕግና ሥርዓትን ማስከበርም የቀይ መስመሩ ሌላው ይዘት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚዘረዝረው ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ በፓርቲና በመንግሥት መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ትክክለኛም ሆነ የተሳሳቱ ውዥንብሮችን በማጥራት አንድነታቸውንና ልዩነታቸውን በሕግና በአሠራር ጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣ የአሠራር ግልጽነቶችን መፍጠርና መተግበር እንደሚገባ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም በአባል ድርጅቶች ውስጥና መሀል ያሉ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት ዴሞክራሲያዊ አንድነትን መፍጠር፣ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ያመለክታል፡፡

ከኢሕአዴግ ጉባዔ ጀምሮ ያሉ የግንባሩ ተቋማትና መዋቅሮች ከግለሰብ ተፅዕኖ ተላቀው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ ጠንካራ ሆነው ተልዕኳቸውን እንዲወጡም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫነት ተካቷል፡፡

የኢሕአዴግ ቀጣይ ምዕራፍ ርዕዮተ ዓለም የማምጣትና ልዕልና የማረጋገጥ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲከናወን ውሳኔው አሳልፏል፡፡

የእርስ በርስ ትግል፣ መወያየት፣ መከራከር፣ መተቻቸትና ግልጽ ድርጅታዊ መዋቅርና ምደባ የሚፈጥር የዳበረ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እንዲሰፍንም ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በአገሪቱ እየተነሱ ላሉ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች መሠረታዊና የማያዳግም ምላሽ ለመስጠት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ወደ ሙሉ ቁመናውና መግለጫው ማሸጋገር የሚያስችል ሥራ በቀጣይ ተጠናክሮ መከናወን እንዳለበት፣ ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ተአማኒነት ያለው፣ ፍትሐዊ በሆነ የመወዳደሪያ ሜዳ ላይ የሚከናወን፣ እውነተኛ ፉክክርና የሐሳብ ፍጭት የሚታይበት እንዲሆን ኢሕአዴግ የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫነት ተካቷል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊና ከግጭት የፀዳ ወይም ግጭት ቢፈጠር የሚፈታበት ሕጋዊ አካሄድን የተላበሰ እንዲሆን፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ አካላት አካታችና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሪፎርም ሥራዎች በጥናት ላይ በመመሥረት እንዲከናወኑ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ እውነተኛ ዳኝነት የሚገኝበት፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ከጉቦ የፀዳ የፍትሕ አገልግሎት የሚሰጥበት እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በመልካም አስተዳደር ረገድ ከአጭር ጊዜ አኳያ ሕዝቡን በየደረጃው ያስመረሩ ጉዳዮች ብዙ ካፒታልና የተለየ ቴክኖሎጂ የማይጠይቁ፣ ቅንነት ብቻ የሚጠይቁና በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉት ተለይተው እንዲተገበሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -