Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተያዘው በጀት ዓመት የግብርና ምርቶች በገፍ መግባታቸው ይቀጥላል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በተያዘው በጀት ዓመት የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ብቻ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ዘይት፣ ስኳርና ስንዴ ከውጭ ለማስገባት ተዘጋጅታለች፡፡

 ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2011 በጀት ዓመት 400 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት፣ 7.7 ሚሊዮን ኩንታል ስኳርና 7.5 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማስገባት ታቅዷል፡፡

ከውጭ የሚገቡት እነዚህ ምርቶች በተለይም 40 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት፣ 643‚735 ኩንታል ስኳርና 621‚172 ኩንታል ስንዴ በተለያዩ መንገዶች በየወሩ ለኅብረተሰቡ ይቀርባሉ፡፡

እነዚህ በድጎማ ወደ አገር የሚገቡ የግብርና ምርቶች በ2010 በጀት ዓመትም በከፍተኛ መጠን ለኅብረተሰቡ ተከፋፍለዋል፡፡

በ2010 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 4.8 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር፣ 5.5 ሚሊዮን ኩንታል የዳቦ ስንዴና 407 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት ገብተዋል፡፡

መንግሥት ለእነዚህ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ ከመመደብ በተጨማሪ ከቀረጥ ነፃ ከመፍቀድ አልፎ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሽያጭ መካከል የሚፈጠሩ የዋጋ ልዩነቶችን በመደጎም በገፍ ወደ አገር በማስገባት ላይ ነው፡፡

በግብርና ላይ በተመሠረተ አገር እነዚህን ምርቶች ማስገባት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አገሪቱ እነዚህን ምርቶች እዚሁ ማምረት የሚያስችል ምቹ ከባቢ አላት፡፡ ንግድ ሚኒስቴር እነዚህ ምርቶች አገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ በመሆኑ በሒደት ከውጭ ማስገባት ይቆማል ብለዋል፡፡

‹‹ንግድ ሚኒስቴር ስትራቴጂ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ስትራቴጂው ተጠናቆ ተግባራዊ ሲደረግ እነዚህ ምርቶች በሰፊው አገር ውስጥ የሚመረቱበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤›› ሲሉ አቶ ወንድሙ መንግሥት እነዚህ ምርቶች ከውጭ ሳይሆን፣ አገር ውስጥ እንዲመረቱ እያመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የፓልም ዘይት እንዲያስመጡ ከፈቀደላቸው የግል አስመጪዎች ውስጥ የተወሰኑት ግዙፍ የዘይት ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

ስኳርን በሚመለከት ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የጀመራቸው፣ ነገር ግን ከዕቅድ በታች አፈጻጸም ያላቸው አሥር የስኳር ፕሮጀክቶች በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ምርት እንዲገቡ እንደሚደረግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርብ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ስንዴን በተመለከተ ዋነኛ አምራች የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ባሌና አርሲ ዞኖች ምርታማነታቸው እንዲጨምር፣ በሌሎች አካባቢዎችም የግሉ ዘርፍ በሰፊው ገብቶ የሚያለማበት መንገድ እየተመቻቸ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች