Saturday, April 20, 2024

ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ማንነት ተደጋጋፊ ወይስ ተገዳዳሪ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ኢትዮጵያ አገራችን የየራሳችን አኩሪ ባህል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር፣ አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሐረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት አገር በመሆንዋ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፣ መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል ጥቅማችንን፣ መብታችንንና ነፃነታችንን በጋራና በተደጋጋፊነት ለማሳደግና አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይኼንን ሕገ መንግሥት በተወካዮቻቸው አማካይነት አፅድቀነዋል፡፡›› ከላይ የተገለጸው በ1987 ዓ.ም. ከፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የተወሰደና አገሪቱ ካለፉት 23 ዓመታት ጀምሮ የተመራችበት ሕገ መንግሥት መሠረታዊ ምሰሶ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የሕገ መንግሥቱ ዓላማ ወይም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እምነት ሆኖ ሳለ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ይኼንን እምነታቸውን አሟልተው ኖረውት አያውቁም ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እየዋዥቁ፣ የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ተወስኖ አግኝተውታል፡፡ የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባፀደቁት ሕገ መንግሥት ላይ፣ ‹‹መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅሞቻችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን እንቀበላለን፤›› ቢሉም፣ በተቃራኒው ወርሰው ባላረሙት የተዛባ ታሪክ መነሻ ቁርሾ ውስጥ ወድቀው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእርስ በርስ ግጭቶች ማዕበል እየተላጉ፣ እየተረጋጉና ዳግም እየተላጉ በሥጋት የተወጠረ ጉዞ ውስጥ ናቸው፡፡

በዚህ አስጨናቂ ሥጋት ውስጥ ሆነው በወርጋ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት የብሔር ማንነት የላቀ ትኩረት በማግኘቱ የጋራ ማንነት የሆነው ኢትዮጵያዊነት ደብዝዞ የግጭት ምክንያት እንደሆነ፣ ከዚህም አልፎ የመበታተንን ሥጋት መደቀኑን ተናግረው ነበር፡፡ ይኼንን ሥጋት መቀልበስና የደበዘዘውን የጋራ ማንነት ማጉላት ቀዳሚ የሥልጣን ቆይታቸው ተልዕኮ መሆኑን በይፋ ቢገልጹም፣ የእርስ በርስ ግጭቱ አሁንም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ምንም እንኳን አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ባትሆንም፣ ካለፉት አራት ዓመታት በተለይም ደግሞ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ አያሌ ብሔር ተኮር ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየፈነዱ ከመረጋጋት ይልቅ፣ ተቀጣጣይና ቀጣይ ባህርይን በመያዛቸው ከፍተኛ ሥጋት ተደቅኗል፡፡

በግጭቶቹ ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶችን የሚወክሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ልሂቃን ድርሻ ቢኖራቸውም፣ አገር የማስተዳደር ፖለቲካዊ ሥልጣንን በጨበጠው በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተቀሰቀሰው የውስጥ ትግል በሥልታዊ መንገድ ወደ ማኅበረሰቡ ወርዶ ሕዝባዊ ጉልበትን እየተላበሰ ወደ ግንባሩ የውስጥ ትግል መመለሱ፣ ግጭቶች ተቀጣጥለው እንዲቀጥሉና ፖለቲካዊ መፍትሔውም እንዲራዘም ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የኢሕአዴግ ምክር ቤትም፣ በአገሪቱ አፍጥጦ የወጣውን ይኼንን ችግር በመገንዘብ ፈጣን መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ስለመሆኑ በይፋ ገልጿል፡፡ ‹

‹የፌዴራል ሥርዓታችን ብሔራዊና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስማምቶ በመሄድ ረገድ የሚያጋጥሙ የአመለካከትም ሆነ መዋቅራዊ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባና ለዚህም ተከታታይ የለውጥ ዕርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ አስቀምጧል፤›› በማለት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫው ግልጽ አድርጓል፡፡

በዚህ ሳምንት ከመስከረም 23 ቀን 2011 ጀምሮ የሚካሄደውና ወሳኝ እንደሆነ የሚነገርለት የኢሕአዴግ ጉባዔ፣ ‹‹አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ለውጥ›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ መሆኑ የችግሩን ጥልቀት ድርጅቱ የተረዳው ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ማንነት ተደጋጋፊ? ወይስ ተገዳዳሪ?

በእንግሊዝ ኬል (Keele) የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና በኢትዮጵያና አካባቢ የሕግና የፖለቲካዊ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር)፣ ይኼንኑ ጉዳይ በተመለከተ ያደረጉትን ጥናትና ምርምር እንዲሁም ተገቢ ይሆናሉ ብለው ያመኑባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ባለፈው ሰሞን በአዲስ አበባ ተገኝተው አቅርበዋል፡፡

የጀርመን ዓለም አቀፍ ተቋም የሆነው ፍሬዲሪክ ስቱፍተንግ (FES) የአዲስ አበባ ቢሮ በማርዮት ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር)፣ ‹‹These Walls Will Fall: Medemer, Solidarity, Subsidiary at the Interstices of Ethnic Nationalism and Constitutional Patriotism›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት የምርምር ሥራቸው፣ በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔር ማንነት መካከል በአሁኑ ወቅት በግልጽ የወጡ መገዳደርን የተላበሱ የማንነት ፉክክሮች መነሻ፣ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤትና መፍትሔዎችን በግላቸው አመልክተዋል፡፡

የአገራዊ ማንነት (Nationalism) አመሠራረት በተለይ በአፍሪካ ከቅኝ ግዛት ጋር የሚተሳሰር ታሪካዊ ዳራ እንዳለው የገለጹት ምሁሩ፣ ናሽናሊዝም የቅኝ ገዥ የውጭ ወራሪዎችን ለማስወገድና የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልን ለማፋፋም ጉልህ ሚና እንደነበረው ያስረዳሉ፡፡ በዚህ የቅኝ ግዛት ወቅት የወራሪዎችን ጭቆና ለመታገል መሪዎች ማኅበረሰባቸውን ለትግል ማነሳሳትና የአይበገሬነት ስሜትን ለቅኝ ገዥዎች ለማሳየት የተጠቀሙበት መሆኑን፣ ለአመሠራረቱም አገራዊ ማንነትን የሚያጎለብቱ ታሪካዊ መዋቅሮች ጥቅም ላይ መዋላቸው፣ የአገራዊ ማንነት ፖለቲካንና ማኅበረሰቦችን ይረዱበት የነበረው አተያይ ይኼንኑ ማንነት ብቻ የሚያጎላ በመሆኑ ቅኝ የተገዙ አገሮች የፀና፣ በተግዳሮቶች ሳይናወጥ የሚሻገር፣ አልፋና ኦሜጋ የሆነ ማንነትን በወቅቱ የተላበሱ እንዲመስሉ ዕድል መፍጠሩን ያስረዳሉ፡፡

በዘመናዊው የፖለቲካ አመለካከት ግን ማንነት የማኅበረሰቦችን የፖለቲካ ወገንተኝነት ወይም አሠላለፍ የሚገልጽ ፖለቲካዊ ይዘት የገነነበት ባህርይ እንደሆነ፣ ይኼንንም ምሁራን በሁለት እንደሚከፍሉት ያመለክታሉ፡፡ የመጀመርያው አተያይ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የአንድ አገር አገራዊ እሴቶች፣ ልማዶችና ሥርዓቶች በሕገ መንግሥት ተጽፈው ሕጋዊ ማንነትን የሚፈጥሩበት (Constitutional Patriotism) እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ሁኔታ የኢትዮጵያ ማንነት አቀንቃኞችን እንደሚመስል ጠቅሰዋል፡፡

ሁለተኛው የማንነት አተያይ (አረዳድ) ደግሞ ከአገር በፊት የሚቀድመው ብሔራዊ ማንነት ነው፣ ከአገር በፊት ብሔር ነበር፣ አገር አገር የሚሆነው ብሔርን ካካተተ በኋላ መሆኑን በመግለጽ የብሔር ማንነት እንደሚመርጥ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ የማንነት አረዳድ የኢትዮጵያ የብሔር ማንነት አቀንቃኞች (Ethno-Nationalist) እንደሚወከሉ ገልጸዋል፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን የተገነባው አገራዊ ማንነት የተሻገሩ ትሩፋቶች፣ የቅኝ ግዛት ዘመን ካለፈ ከብዙ ዓመታት በኋላ የአፍሪካ አገሮች ራስ ምታት መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ በተለያዩ ብሔሮች የተዋቀሩ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ዘመን በኋላ የቀደመውን አገራዊ ማንነት በመጠቀም ማኅበረሰቦችን ማንቃትና ማንቀሳቀስ እንዳዳገታቸው፣ ወጥ የሆነ አገራዊ ማንነትን ማቀንቀንም ብሔርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ዝንባሌ፣ ባህርይና የውሳኔ አሰጣጥ ብሎም የብሔር ማንነት በተቃራኒው ተገዳዳሪ ኃይል ሆኖ ብቅ እንዲል ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ምሁሩ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያም ሁኔታ ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ የተናገሩት ምሁሩ፣ በብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ማንነት እንደ አዲስ ተዋቅሮ ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ትግበራ ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጋራ ማንነት ምሥረታና የብሔር ግንባታን የኢትዮጰያ ሕገ መንግሥት በእኩል ሁኔታ፣ ማለትም በፖለቲካ አመለካከትና በብሔር ተኮር አመለካከት የተከፈለ ሆኖ እንዲተገበር መፍቀዱን፣ ይህም አገራዊ የጋራ ማንነትና የክልል ወይም ብሔር ተኮር ማንነት ሁለት የማይታረቅና ተቀጣጣይ ጫፎች ሆነው የተከፋፈለ ማኅበረሰ እንዲፈጠር ማድረጉን ያወሳሉ፡፡ ይህም ባለፉት 23 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሙግት ርዕስ ሆኖ መዝለቁንና ዛሬ ደግሞ የበለጠ ተቀጣጥሎ የአገሪቱ ፖለቲካ ዋነኛ የስበት ማዕከል ሆኗል፡፡

የአገሪቱን ፖለቲካ የተቆጣጠረው የጋራ አገራዊ ማንነትና የብሔር ማንነት ጥያቄዎች ተደጋግፈው ከመሄድ ይልቅ ተገዳዳሪ፣ የሚጣረሱና ተቀጣጣይ የግጭት መንስዔዎች ወደ መሆን መሸጋገራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ የሁለት ተገዳዳሪ ማንነቶች መገለጫዎች በርከት ያሉ ቢሆንም፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ ግልጽ ተገዳዳሪ ማንነቶች ሆነው የሚታዩት ኢትዮጵያዊ ማንነትና የኦሮሞ ማንነት (ኦሮሙማ) መሆናቸውን በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ተገዳዳሪ ማንነቶች ጠንካራ ንድፈ ሐሳባዊና ታሪካዊ ዳራዎችን በመንተራስ የየራሳቸውን እውነት በተረጋጋ መሠረት ላይ የተከሉ መሆናቸውንም ያክላሉ፡፡

ኢትዮጵያዊነትና የኦሮሞ ማንነት ከመደጋገፍ ይልቅ ተገዳዳሪ የሆኑት፣ ኢትዮጵያዊነት ራሱን ከሁሉ የበላይ የሆነ አድርጎ በመቅረፁና ይኼንንም በተለያዩ ግዙፍ ታሪካዊ ዳራዎች በማስደገፍ፣ በፖለቲካ ላይ ብቸኛ የበላይ በመሆኑና በተቃራኒው ደግሞ ኦሮሙማ (ኦሮሞነት) ጨቋኝና የበላይ ነው ብሎ የተገነዘበውን ኢትዮጵያዊ ማንነት በመቃረን ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት ብቸኛ የበላይ ሆኖ ራሱን የሚገልጽ ስለመሆኑ ሦስት ማሳያዎችን አወል ቃሲም አሎ ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያዊ ማንነት ራሱን የሚገልጸው በኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኞች መሆኑንና ኢትዮጵያዊነት ነፃ (Liberal)፣ የሠለጠነ (Civilized)፣ የመከባበርና የእኩልነት ምልክትና የሞራል ልዕልና ያለው ቢሆንም፣ ጠባብ ብሔርተኛ ኃይሎች ሊፈታተኑ የሚሞክሩት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊነት ሌሎች ማንነቶች ራሳቸውን በአማራጭነት እንዳይገልጹ የመጫን ባህሪው ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው (Universal) አድርጎ ራሱን በመግለጽ፣ በሥልታዊ መንገድ ሌሎችን የሚያገል እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ለመሆን የዚህ ማንነት መገለጫ የሆነውን ቋንቋ መናገር፣ የኢትዮጵያዊነት ሞራል ደረጃዎችን በሚገባ መጠቀምን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ሁሉን አቃፊ መሆኑን የሚገልጽ ነገር ግን አግላይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊነት የእውነት መገለጫ፣ ከፖለቲካና ሥልጣን ገለልተኛ የሆነና ራሱን ችሎ የሚቆም እውነት እንደሆነ አድርጎ ራሱን የሚገልጽ ማንነት መሆኑን፣ በዚህም ውስጥ ሁሉንም እንደሚወክል የሚያምን መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊነት ብቸኛ የበላይ እንደሆነ የሚያምንና በሁሉም ተቀባይነት ያለው አድርጎ ራሱን የሚገልጽ ቢሆንም፣ ውስን የሆነ ብሔረሰብና ማንነትን እንደሚወክል የጠቀሱት ምሁሩ በአመዛኙ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል (የአማራና የትግራይ) ባህል፣ ትውፊት፣ ፊደልና የአኗኗር ዘይቤ በማስፋፋት ወካይ ማንነት (Ethiopinization) ማድረግ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል ኦሮሞነት የኢትዮጵያዊነት ተፅዕኖ ሰለባ፣ ማንነቱና ተደማጭነቱ ኢፍትሐዊ በሆነ ጥቃት የተነጠቀ አድርጎ የሚያምን፣ ይኼንንም ታሪካዊ ኢፍትሐዊነት በእንቢተኝነት ለመቀየር የተነሳ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ማኅበራዊና አገራዊ ድንበር አካል ቢሆንም፣ በተግባር ግን የኢትዮጵያ አካል የሆነ ነገር ግን እንደ በድን ተቆጥሬያለሁ፣ ድምፅ ያለው ድምፅ አልባ ሆኛለሁ ብሎ የሚያምን፣ የተጠቂነት ስሜት የተጫነው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የኦሮሙማ (የኦሮሞነት) ማዕከላዊ ችግር ኢትዮጵያዊነትን የማይቀበል ሆኖ፣ በራሱ ልሂቃን እየተገለጸ ያለ ማንነት ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ይህ የኦሮሙማ እንቅስቃሴ የኦሮሞ ፖለቲካን ወደፊት ማምጣት የቻለ እንደሆነ ነገር ግን በዚህ መንገድ ይቀጥላል? ወይስ በእኩልነትና ትብብር የሚያምን ትክክለኛ ማንነትና ማኅበረሰብን ዕውን ማድረግ ይችላል? በሚለው ላይ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ምሁሩ አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) በጥናታቸው ይገልጻሉ፡፡ ማንኛውም ትግል አዎንታዊ ለውጥና ነፃነትን እንዲቀናጅ ከተፈለገ በኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡ ፈጦ የመጣውን የኢትዮጵያዊነትና ኦሮሞነት መገዳደር የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሰቅዞ ሊይዝ የሚችል፣ ይህም የተከፋፈለና የማይስማማ ማኅበረሰብ የፖለቲካ ፍላጎቶች የሚንተከተኩበት ሆኖ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ፡፡ የዚህ ቀውስ መፍትሔ አቃፊ የሆነ ኅብረ ብሔራዊ ማንነት መገንባት ቢሆንም፣ ወደዚህ ለመድረስ አማራጭ መንገዱን ማጤን እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በእሳቸው አመለካከት አማራጭ መፍትሔ የሚሆነው ከጠንካራ የልዩነት ምሰሶዎች ይልቅ፣ እስከ ዛሬ ትኩረት ያላገኙ የላሉ የልዩነት ገመዶችን ማጥበቅ ተመራጭ ናቸው፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲስ ፍልስፍና የሆነው የመደመር መርህ ግልጽ የሆነ ትርጉምና ዝርዝር ማዕቀፍ ወጥቶለት መተግበር እንደሚችል ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል በመተዋወቅና በመግባባት ላይ የተመሠረተ ትብብራዊ አንድነት (Solidarity) መገንባት እንደሚያስፈልግ፣ የዚህ ዓላማ መሠረቱ መታረቅ ሳይሆን የማይታረቁ ፍላጎቶችን የያዘ ማኅበረሰብ መሆንን አምኖ ነገር ግን አንድ የሚያደርጉና የሚያስተሳስሩትን በማስቀደም፣ ተደጋግፎ መኖርን መለማመድ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም ያልተማከለ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ማስፈንን በምክረ ሐሳብነት አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -