Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ በቡና ማሳዎች ላይ ለደረሰ ጉዳት ካሳ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፉት ሦስት ዓመታት ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት፣ ጉዳት ለደረሰባቸው የቡና ኢንቨስትመንት ባለቤቶች የሕግ ከለላና ካሳ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ጠየቀ፡፡

ማኅበሩ ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ገበያ ልማት ባለሥልጣን አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቡና እርሻዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ለመንግሥት አቤቱታ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

‹‹ለጉዳቱ መፍትሔ እንዲደረግ የተገለጸ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን በተጨባጭ ምላሽ አልተገኘም፤›› ሲሉ አቶ ግዛት ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ተቀስቅሶ በቆየው ደም አፍሳሽ ግጭትና የደቦ ፍርድ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱ በተጨማሪ፣ መጠኑ የማይታወቅ ከፍተኛ ንብረት መውደሙ ይታወቃል፡፡

በተለይ በኢንቨስትመንት ላይ ከደረሰው ጉዳት ውስጥ በቡና ማሳዎች ላይና በቡና በምርት ላይ የደረሰው ጉዳት ተጠቃሽ ነው፡፡

በተለይ በደቡብ፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ ክልሎች በርካታ የቡና ማሳዎች ተዘርፈዋል፣ ተጨፍጭፈዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ባዜን የእርሻና የኢንዱስትሪ ልማት፣ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ ብአኤካ ጄኔራል ቢዝነስና ኃይሌ ዓለም ንግድ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ባዜን የእርሻና የኢንዱስትሪ ልማት ኩባንያ ለኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር፣ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ኩባንያው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረበው አቤቱታ፣ በደረሰበት ዝርፊያና የንብረት ውድመት ኪሳራ እንደገጠመው ገልጿል፡፡

ኩባንያው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ጊቤ ቦሳ አካባቢ 538.4 ሔክታር መሬት የቡና ማሳ ባለቤት ነው፡፡ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ ቡና በማልማት ለዓለም ገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

ነገር ግን ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተደራጁ አካላት ለለቀማ የደረሰ ቡና እየተሸመጠጠ፣ የተለቀመ ቡና እየተዘረፈ በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቡና እንደተዘረፈበት ኩባንያው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ ይህንን አቤቱታ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ለኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ኃላፊዎች መዋቅሮች ቢያቀርብም ምላሽ እንዳልተሰጠው በመግለጽ በድጋሚ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አቤቱታውን ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ባቀረበው አቤቱታ መንግሥት የደረሰውን ጉዳት መጠን ገምግሞ ካሳ እንዲከፍለው፣ ካሳው ተፈጻሚ እስኪሆን ድረስ ከግል ባንኮች ከ19 በመቶ በላይ ወለድ የተበደረው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ወደ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲዛወርለት ጠይቋል፡፡

የቡና ማሳዎች የደረሰባቸው የጉዳት መጠን የተለያየ ቢሆንም፣ መንግሥት የደረሰባቸውን ጉዳት በማጤን ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ማኅበሩ ጠይቋል፡፡

የቡና አምራቶች በአገሪቱ የፀጥታ ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት በማሳቸው ላይ የሚደርስ ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ የሕግ ከለላ በሚሰጥበት ሁኔታ ላይ ከመንግሥት ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡

የቡናና ሻይ ገበያ ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ፣ የቡና አልሚዎች በአገሪቱ አለመረጋጋቶችና የፀጥታ ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ባለሙትና በሚያለሙት ቡና ላይ ችግር እየገጠማቸው፣ አልፎ አልፎም ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን መናገራቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ሳኒ እንዳሉት፣ ይህንን ችግር ለመፍታት የዞንና የወረዳ መዋቅሮች የጋራ ጥቅምን መሠረት በማድረግ ከአልሚዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአልሚዎች የሕግ ከለላ የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ ለማውጣት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች