Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማማከርና ምርምርን ለውጭ ምንዛሪ ምንጭነት

ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ የኤቢኤች ፓርትነርስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ተወልደው ባደጉበት ቢሾፍቱ ከተማ ነው፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኅብረተሰብ አቀፍ ሕክምና የመጀመርያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፐብሊክ ሔልዝ ላይ ሠርተዋል፡፡ በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካና በሌሎችም በርካታ አገሮች ውስጥ ልዩ ልዩ ሙያዊ ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ ዙሪያ የሚያከናውኑት ተግባራት በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ኤቢኤች አመሠራረት አጠር ያለ ማብራሪያ ቢሰጡን?

ዶ/ር ማርቆስ፡- ኤቢኤች ፓርትነርስ በኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት በሆኑ ሁለት ጓደኛሞች የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡ የድርጅቱ ዋና ዓላማም በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ያተኮረ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በመሠረቱ የማማከርና የሥልጠና ሥራ በጣም ውድ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ውድ የሆኑ ሰዎችን ክፍያ ከፍሎ፣ አቅርቦና አገልግሎት ሰጥቶ ገንዘብ መቀበልን ይጠይቃል፡፡ በዚህም የተነሳ ትንሽ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የኔትወርክ አቅም ይፈልጋል፡፡ ድርጅቱ የተመሠረተው በ250 ሺሕ ዶላር ወይም በ2.5 ሚሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል ሲሆን፣ በወቅቱ የነበረን ሞራል፣ የነበረን ኔትወርክና የነበረን ተነሳሽነት ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል፡፡ ድርጅቱም እንደተመሠረተ በአገር ውስጥ የሰዎችና የተቋማት አቅም ማነስ በስፋት በተንሠራፋበት ወቅት ነበር፡፡ እኛ ግን ኢንዱስትሪው ወይም ሥራው ምን እንደሚፈለግ በደንብ ስለምናውቅ የመጀመርያውን ሥራ ለማሳየት ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራት ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ማርቆስ፡- ከሦስት ሺሕ በላይ የሚጠጉ የምርምር ረዳቶችን በአጭር ጊዜ አሠልጥነን በሥራ ላይ እንዲሰማሩ አድርገናል፡፡ ሥልጠናውም ያተኮረው በኅብረተሰብ ጤና ላይ የፕሮግራሞችን ውጤታማነት ምዘናና ቁጥጥር ማድረግ ይገኝበታል፡፡ ከዚህም ሌላ ከ500 በላይ ኮንሰልታንቶችን የእኛ አሶሺየት ኮንሰልታንት እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ ይህም የተደረገው አወዳድረን፣ ውጤታቸውን አይተንና መርጠን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ኤችአይቪ ኤድስ በከፍተኛ ደረጃ በተሠራጨበት ዘመን የሥልጠና ማኑዋሎችን በማዘጋጀት፣ የአሠልጣኖች ሥልጠና በመስጠት ተባብረናል፡፡ እንዲሁም ከ5,300 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎችን በሥራ ላይ እንዳሉ ሥልጠና እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ ሥልጠናው በይበልጥ ያተኮረው በዋነኝነት በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ ሆኖ በእናቶች ጤና፣ በሥርዓተ ምግብና በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብርና አጋርነት ወይም በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ ዙሪያ ለመሥራት ያነሳሳችሁ ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር ማርቆስ፡- ዓላማችን ዕውቀትን ማመንጨት ወይም ማፍለቅ፣ ማሠራጨትና ተግባራዊ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን ከአጫጭር ሥልጠናዎች ወጥተን ረዣዥም ሥልጠናዎችን ለምን አንሠራም? የሚል ሐሳብ አዳብረን፡፡ ለተግባራዊነቱም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ ፈጥረን በትብብር መንቀሳቀስ ጀመረን፡፡ ትብብሩ ከተጀመረበት እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ ነዋሪ ለሆኑና ከ1,300 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር በድኅረ ምረቃ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ያገላበጥነው ሀብትና ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ኤቢኤች ፓርትነርስ አሉ ከሚባሉ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህም ሁኔታ በራሱ ትልቅ ግብና ውጤታማነት ነው፡፡ ማማከርና የምርምር አገልግሎት በመስጠታችንም የተነሳ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት ችለናል፡፡ ለዚህም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹ዘመናዊ፣ ቋሚና ታዋቂ የሆነ ደንበኛ› የሚል የዕውቅና ሰርተፊኬት ተችረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ ሥራ ጅማ ዩኒቨርሲቲን የመረጣችሁት በምን መልኩ ነው?

ዶ/ር ማርቆስ፡- ለፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትና ትስስር ሊጠናከር የሚችለው አንዱ ለአንዱ የሚጠቅምበት፣ ወይም አንዱ የሚጎድለውን ሌላው ሊሸፍንለት ወይም ማገዝ ወይም እርስ በርስ መደጋገፍ ሲቻሉ ነው፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በጣም ግዙፍ፣ ጠንካራና ስመ ጥር ነው፡፡ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በትምህርት ሚኒስቴርና በሌሎች እኩዮቹ ዩኒቨርሲቲዎች በተደረገ ውድድር አንደኛነትን የተቀዳጀ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ጥሩ ካሪኩለም፣ ሲስተምና ዝና አለው፡፡ ኤቢኤች ኩባንያ መሥራቶች ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ አሠራርን በደንብ ያውቃሉ፡፡ ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና ለመስጠት ምን እንደሚያስፈልግ? ወይም ደግሞ ምን መደረግ እንዳለበት? የሚጠቁም ልምድ አለን፡፡ ከዚህም ሌላ ለአጫጭር ሥልጠና ብለን የመሠረትነው ፋሲሊቲዎች አሉን፡፡ ከዚህም ሌላ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ያካበትነው የሥራ ልምድ አለን፡፡ ይህንን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ኤቢኤች ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በአጋርነት ወይም በትብብር ለመሥራት ተስማማን፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓይነቱ አሠራር ዩኒቨርሲቲውም ሆነ ኤቢኤች ያገኙት ጥቃሞት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ማርቆስ፡- በዚህ ዓይነቱ አጋርነት ሥራ ላይ ሁሉም አሸናፊ (ዊን ዊን) ነው፡፡ በዚህም የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተጨማሪ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲውም ተደራሽነት ጨምሯል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ ከመሆኑም ባሻገር በርካታ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች የሚገኙባት ከተማ ናት፡፡ በዚህም የተነሳ ዩኒቨርሲቲው የኤቢኤች ካምፓስ በማቋቋም ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን የማቀፍ ወይም ፕሮግራሙ እንዲካተቱ ዕድል ገጥሞታል፡፡ እኛም እንደተቋም ሀርቫርድና ጃንሆፒኪንስ ከመሰሉ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች፣ እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ማለትም ከዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና ከዩኒሴፍ ጋር አብረን የመሥራት ዕድል አጋጥሞናል፡፡ በተለይ ከሀርቨርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር አሁን እየሠራነው ያለው ሥራ ለፕራይሜሪ ሔልዝ ኬር የሚረዱ ውሳኔዎችን የማሰባሰብና ለሔልዝ ኬር ፋይናንሲንግ የቴክኒክ ድጋፍ የሚውል ፕሮጀክት ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ለአጋር ድርጅቶቹ ማቅረብ ይገኝበታል፡፡ ከጃንሆፒኪንስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ደግሞ በ28,000 ቤቶች ላይ በታብሌት ኮምፒውተር በታገዘ መልኩ ጥናት አካሂደናል፡፡ የጥናቱም ዓላማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተወሰኑ የሕፃናት በሽታዎች ላይ ሕክምና እንዲሰጡ መንግሥት ያወጣው ፖሊሲ ትግበራ ላይ ምን ችግሮች ነበሩት? ምንስ ውጤት አመጣ? በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ ያጠነጠነ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያደረጋችሁት የማዕቀፍ ስምምነትን ቢዘረዝሩልን?

ዶ/ር ማርቆስ፡- ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለን የማዕቀፍ ስምምነት ሰፊ ነው፡፡ በተለያዩ ፕሮግራሞች፣ የምርምር፣ የሥልጠናና የማማከር ሥራዎችን አብረን እንሠራለን፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የአካዴሚክ ትብብር ሲሆን፣ ይህም የተጀመረው በሁለት ፕሮግራሞች ነው፡፡ አንደኛው በማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (ኤምቢኤ) ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ በማስተር ኦፍ ፐብሊክ ሔልዝ (ኤምፒኤች) ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም የተጀመረው ከስድስት ዓመት በፊት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በተረፈ በአጫጭር ሥልጠናዎች ቀደም ብለን አብረን እንሠራ ነበር፡፡ በሁለቱ ፕሮግራሞችን አብረን መሥራት ከጀመርን በኋላ አቅማችንን እያሳደግን፣ ፍላጎቱንና የዩኒቨርሲቲውን ዝግጅት እያየን ፕሮግራሞቹ እየጨመሩ መጥተው በአሁኑ ሰዓት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኤቢኤች ካምፓስ የሚሰጡት የፕሮግራሞች ቁጥር ወደ ስምንት ከፍ ብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሰባቱ የድኅረ ምረቃ ፕሮግሞች ሲሆኑ፣ አንደኛው ግን የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ነው፡፡ የቅድመ ምረቃው ፕሮግራም በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም የተጀመረው ዓምና ሲሆን፣ ዘንድሮ ተማሪዎቹ ሁለተኛ ዓመት ላይ ደርሰዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ወደ 40 የሚጠጉ የሕክምና ተማሪዎች ትምህርታቸው በዚህ ካምፓስ እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የኤቢኤች ካምፓስ አደረጃጀት ምን መልክ ይዟል?

ዶ/ር ማርቆስ፡- ካምፓሱ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኝ ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ነው፡፡ ሕንፃው ኪራይ የሚከፈልበት ሲሆን፣ ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያና ለሌላም አገልግሎት የሚውል ሰፊ ቦታና ለመማር ማስተማሩ ሥራ የሚውሉ ልዩ ልዩ የመገልገያ ክፍሎች አሉት፡፡ ከእነዚህም ክፍሎች መካከል የመማርያ፣ የላብራቶሪ፣ የአይቲ ክፍሎችና ቤተ መጻሕፍት ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራዊ ኃላፊነታችን ለመወጣት የተደረገውን ጥረት ሊገልጹልን ይችላሉ?

ዶ/ር ማርቆስ፡- እንደ ተቋም ያሉብንን ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ለመወጣት በርካታ ሥራዎችን አከናውነናል፡፡ በአካባቢያችን ለሚካሄዱ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ ሠራተኞቻችንና ተማሪዎቻችን በየዓመቱ የደም ልገሳ እንዲያደርጉ እናበረታታለን፡፡ በተለያዩ ተቋማት ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች አጫጭር ሥልጠናዎችን በነፃ ሰጥተናል፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 100 ኮምፒውተሮችን ለሦስት ትምህርት ቤቶች በዕርዳታ ለግሰናል፡፡ በአካባቢያችን ለሚገኝ የወጣት ማዕከል 25 ኮምፒውተሮችን አበርክተናል፡፡ ይህ ዓይነቱም ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...