Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአርባ ምንጭ የተጠራ ሰላማዊ ሠልፍ ገጽታውን በመቀየሩ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ

በአርባ ምንጭ የተጠራ ሰላማዊ ሠልፍ ገጽታውን በመቀየሩ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ

ቀን:

የአገር ሽማግሌዎች ከተማውን ከጥፋት ታድገዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማና አካባቢው በተፈጸመ ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉ ከተሰማ በኋላ፣ በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ የተጠራ ሰላማዊ ሠልፍ ወደ ግጭት ተቀይሮ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ ከሕይወት ማለፍ በተጨማሪ በሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት ሲደርስ፣ በአገር ሽማግሌዎችና በፀጥታ ኃይሎች ጥረት በሰዎች ላይም ሆነ በንብረት ላይ ሊደርስ ይችል የነበረ ከፍተኛ ጉዳት መክሸፉ ተመልክቷል፡፡

- Advertisement -

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በፍትሕ፣ የፀጥታና የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ፆራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከመስከረም 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በቡራዩና አካባቢው በሚኖሩ የጋሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምሮ ነበር፡፡

በወቅቱ በነበረው ጥቃት ምክንያት ሰላማዊ ሠልፉን ለማስተባበር የተቋቋመ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ መስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ ለማካሄድ ጥያቄ አቅርቦ፣ ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ መካሄድ እንደሚችል ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፈቃድ አግኝቷል ብለዋል፡፡

ሠልፍ እንዲካሄድ የተወሰነው በአርባ ምንጭ ከተማ ከጋሞ አደባባይ እስከ ስታዲዮም ድረስ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአርባ ምንጭና የአካባቢው ነዋሪዎች በሠልፉ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡

 ጉዞ ወደ ስታዲዮም እየተደረገ ባለበት ወቅት፣ ‹‹በጋሞ ሕዝብ ላይ የሚካሄድ ጥቃት ይቁም፣ መንግሥት ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቅርብ፣ የጋሞ ሕዝብ ከየትኛውም ብሔር ጋር መጋጨት አይፈልግም. . . ፤›› እና የመሳሰሉ መፈክሮች ተደምጠዋል፡፡

  አቶ ገበየሁ እንደሚሉት ግን እነዚህ መፈክሮች እየተስተጋቡ ጉዞው ቀጥሎ እያለ የጋሞ ብሔረሰብን የማይወክል ክስተት ተፈጥሯል፡፡

‹‹በአርባ ምንጭ ከተማ ሰላም የማይፈልጉ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ድንገት አጥቂዎችን ማጥቃት አለብን በማለት የተወሰኑ የግልና የመንግሥት ተቋማትን ለማጥቃት እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የአገር ሽማግሌዎችና የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ጥረት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር ተችሏል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ገበየሁ፣ ‹‹የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ንብረት የሆነ አንድ ተሽከርካሪ ከመቃጠሉ ውጪ በንብረት ላይ የከፋ አደጋ አልደረሰም፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን በወቅቱ መልኩን እየቀየረ በነበረው ሠልፍ የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ ገበየሁ አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ገበየሁ ጨምረው እንደገለጹት፣ በጋሞ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በሚመለከት ከዞኑ የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች ከፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ረቡዕ መስከረም 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ይንቀሳቀሳሉ፡፡

ከዚህ ውጪ ይህን ጉዳይ በሚመለከት በአርባ ምንጭ ከተማ የሚካሄድ ሰላማዊ ሠልፍ እንደማይኖር አቶ ገበየሁ አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት በቡራዩና በአካባቢው የ23 ዜጎች ሕይወት ማለፉን ያስታወቀ ሲሆን፣ አቶ ገበየሁ እንደሚሉት ከሟቾች ውስጥ 20 ያህሉ የጋሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ናቸው፡፡

‹‹የት እንደገቡ የማይታወቁ ሰዎች አሉ፤›› ሲሉም አቶ ገበየሁ የጠፉ ሰዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ወጣቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በደም ፍላት የሰው ሕይወት እንዳያጠፉና ንብረት እነዳያወድሙ እርጥብ ሳር በመያዝ ያደረጉት ተግባር በብዙዎች ዘንድ በአርዓያነት ታይቷል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁት ፎቶዎች የብዙዎችን ልብ ነክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...