Tuesday, April 23, 2024

‹‹የባንዲራ›› ነገር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በ18ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻና በ19ኛው ምዕተ ዓመት የመጀመርያው ሩብ ምዕተ ዓመት አካባቢ ኢትዮጵያን በመውረርና በሥልታዊ ወዳጅነት የምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ የቋመጠው የፋሽስት ኢጣሊያ መንግሥት፣ ጥረቶቹ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥንካሬና በአገራቸው ጉዳይ በሚያሳዩት አይበገሬ አንድነት ሳይሳካለት ብቻ ሳይሆን ውርደትንም ተከናንቦ መመለሱን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን በወቅቱ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ በተለይ ሥልታዊ ወዳጅነትን ዘዴው ያደረገው የጣሊያን መንግሥት፣ በኢትዮጵያን በወረራ በያዛባቸው ዓመታት በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ሊገለጹ የሚችሉ አሻራዎቹን ትቶ አልፏል፡፡ ለአብነትም ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ቋንቋና የራሳቸውን ፊደል የሚጠቀሙ ቢሆኑም፣ በወቅቱ በነበረው የጣሊያን ተፅዕኖ አንዳንድ መግባቢያ ቃላት ዘመናትን ተሻግረው ይጠቀሙባቸዋል፡፡

የራሳቸው ቋንቋ አካል እስኪመለሱ ድረስ ዛሬም ድረስ ይፋና ይፋ ባልሆነ መንገድ ይግባቡባቸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የዚህ ዘገባ ማጠንጠኛ ጉዳይ የሆነው ‹‹ባንዲራ›› ተጠቃሽ ነው፡፡ ሊሂቃኑም ሆነ የተቀረው ማኅበረሰብ፣ ከአገሪቱ መሪ እስከ ዝቅተኛው የመንግሥትና የፖለቲካ አመራር ድረስ የአገሪቱን ‹‹ሰንደቅ ዓላማ›› በአገሩ መጠሪያ ሲጠሩት አይደመጡም፡፡ ከዚያ ይልቅ ‹‹ባንዲራ›› የሚለው የጣሊያንኛ መጠሪያው ይቀላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በርካቶቹ ‹‹ባንዲራ›› ሲሉ ከልባቸው ያለውን ትርጉም እንጂ፣ የጣሊያንኛ ቃል ስለመሆኑ አይገነዘቡም፣ ወይም አይረዱም፡፡

ባንዲራ በሚለው መጠሪያ የሚዘወተር ተገቢነት ላይ ሲወዛገቡ ባይታወቅም፣ ኢትዮጵያ ካለፈችባቸው የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻዎችና የሥልጣን ለውጦች ጋር ተያይዞ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ለውጥ መከተሉና በዚህም መወዛገብና መነታረካቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለማስተካከል የተለመደ ነው፡፡

እስከ ዘንድሮ ድረስ ባለው የፖለቲካ ሕይወታቸው ውስጥ ግን አንድም ጊዜ የሰንደቅ ዓላማቸው መሠረታዊ በሆኑት ሦስት ቀለማት ማለትም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት እንዲሁም አቀማመጣቸውን በተመለከተ ቅራኔ ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡

ከላይ ወደታች በዕኩል ምጣኔ ተከፋፍለው የተያያዙት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማቸው አድርገው መቼ እንደተቀበሉ ትክክለኛና ሁሉም የተስማማበት የታሪክ ማስረጃ ማቅረብ ባይቻልም፣ ከአፄ ምንሊክ ዘመን አንስቶ እስካሁን ድረስ በነበሩት መንግሥታት ኦፊሴሊያዊ የአገሪቱ መወከያ ቀለማት ሆነው ዘልቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሦስቱን ቀለማት በዋናነት በያዘው በዚህ ሰንደቅ ዓላማ ላይ አገሪቱን ያስተዳድሩ የነበሩ መንግሥታት ባህሪን የሚወክል ዓርማ ሲያስቀምጡ፣ አዲስ የመጣውም የራሱን ባህሪ የሚወክል ዓርማ ሲያስቀምጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት የሚወክል የአንበሳ ምሥል በዓርማነት በሰንደቅ ዓላማው መካከል የነበረ ቢሆንም፣ ንጉሣዊውን ሥርዓት አስወግዶ የወጣው ወታደራዊ መንግሥት በበኩሉ ዘውዳዊ ሥርዓት አገሮችም ለልማትና ብልፅግና የሚታትር መንግሥት መምጣቱን ለማሳየት ወካይ ያለውን ዓርማ በሰንደቅ ዓላማው መሀል ላይ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ ወታደራዊውን መንግሥት በትጥቅ ትግል ያስወገደው የኢሕአዴግ መንግሥትም ነባሮቹን ቀለማትና አቀማመጣቸውን ሳይቀይር፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነትን ይወክላል ያለውን ባለ ኮከብ ዓርማ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡

ይህ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት የሚወክል ነው የተባለው ዓርማ የያዘው ሰንደቅ ዓላማ ላለፉት 20 ዓመታት ሲውለበለብ ቢቆይም፣ ከጅምሩ አንስቶ በዚህ ዓርማ ላይ የነበረው ቅራኔ ተዳፍኖ ቆይቶ በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ ኃይል የኦሮሞና የአማራ ብሔሮች በጋራ ከጎኑ በማሠለፍ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን የውስጥ ትግል አሸንፎ ወደ ሥልጣን ከመጣበት መጋቢት 2010 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት ጊዜያት፣ የሥልጣን ለውጥን የሚከተለው የሰንደቅ ዓላማ ውዝግብ ከፍ ብሎ ተከስቷል፡፡

በኢሕኤዴግ የውስጥ ትግል ያሸነፈውን የለውጥ ኃይል የሚወክሉትና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጥቂት ቀናት የሥልጣን ቆይታቸው ያመጡትን ለውጥና የፈጠሩትን ተስፋ ለማመሥገን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአዲስ አበባና የአካባቢው ነዋሪዎች ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄዱት የድጋፍ ሠልፍ ላይ ከተስተዋሉት ትዕይንቶች መካከል አንዱ፣ ይኸው የሰንደቅ ዓላማ ምርጫ ጉዳይ ነበር፡፡

በድጋፍ ሠልፉ የተገኙ ወጣቶች ዓርማ የሌለበትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ‹‹ይኼ ነው ባንዲራው›› እያሉ ሲዘምሩ ተስተውለዋል፡፡ ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ዕውቅና ያገኘውን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ለመጠበቅና የአጠቃቀም ሥነ ሥርዓቱን ለመወሰን የወጣው የወንጀል ሕግ ሰንደቅ ዓላማው አሁን ያለውን ቅርፅና ይዘት ይዞ ከመጣ ከ20 ዓመት በኋላ የፀደቀ ቢሆንም፣ የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ይህ አዋጅ ሥራ ላይ እንዳይውል በይፋ አልታገደም፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ቦታ የሕግ ዕውቅና በተሰጠው የአገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያላቸውን ቅራኔና የአዲስ ሰንደቅ ዓላማ ምርጫዎቻቸውን፣ ያለምንም ክልከላና ከልካይ በአደባባይ እየገለጹ ነው፡፡ ሺሕ ሜትሮች ድረስ የሚዘረጋ ሰንደቅ ዓላማ አሠርተው ምርጫቸውን በመያዝ በርዝማኔ ፉክክር ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አመራር ድጋፍ ለማድረግ በባህር ዳርና በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በተደረጉ ሠልፎች ለብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማነት የቀረበው ዓርማ የሌለው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በስፋት ተውለብልቧል፡፡ ይህ ሰንደቅ ዓላማ የአማራን የበላይነትና የአሃዳዊ ሥርዓት ናፍቆት መገለጫ አድርገው የሚያምኑ አካላት የተቃውሞ ትችታቸውን በወቅቱ ለመሰንዘር ሞክረው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ የፖለቲካ ትግላቸውን በአገር ውስጥ እንዲያደርጉ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ አመራሮች የትጥቅ ትግል አቁመው አዲስ አበባ ሲገቡ አቀባበል ለማድረግ ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓ.ም. የወጡት በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ዓርማ የሌለውን የሰንደቅ ዓላማ ምርጫቸውን ከፍ አድርገው አውለብልበዋል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሞ ወጣቶችም የትግላቸው ምልክት አድርገው የሚቆጥሩትን  የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ዓርማ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ሲያውለበልቡ፣ እንዲሁም ተሰደው የከረሙ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ወደ አገራቸው በሚገቡበት ወቅት በአዲስ አበባ በመገኘትና ይኼንኑ ዓርማ በማውለብለብ ሲቀበሏቸው ሰንብተዋል፡፡

መሰንበቻውን የኦነግ አመራሮች ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አቀባበል ለማድረግና በአዲስ አበባ ከተማ የኦነግ ዓርማዎች ለማውለብለብ፣ እንዲሁም በጎዳናዎችና በመሳሰሉት ዓርማውን ለመቀባት ባደረጉት ጥረት ግጭት ተከስቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከተማዋ ውጥረት ውስጥ ሰንብታለች፡፡

መንግሥትና የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ምን ይላሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን በመጡ በጥቂት ቀናት ያስመዘገቧቸውን ውጤቶችና የፈጠሩትን ተስፋ ለመደገፍ በባህር ዳር ከተማ የወጣው ሕዝብ ዓርማ የሌለበትን የሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልብ፣ የኢሕአዴግና የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ፊት ያለ ከልካይ በስፋት ማውለብለቡ የሕግ ጥሰት ስለመሆኑ በቅድሚያ በመግለጽ ተቃውሞውን በይፋ ያሰማው፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትና ክልሉን የሚያስተዳድረው የገዥው ፓርቲ አባል የሆነው ሕወሓት ነበር፡፡

‹‹የባንዲራ›› ነገር

 

የክልሉ መንግሥትና ሕወሓት በይፋ ባወጡት መግለጫ በባህር ዳሩ ሠልፍ በዋናነት፣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ ሠልፎች ሕጋዊ ዕውቅና ካለው የአገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ውጪ የተለያዩ የሰንደቅ ዓላማ ፍላጎቶችን በአደባባይ ይዞ መውጣትና ማውለብለብ የሕግ ጥሰት እንደሆነ፣ በእንጭጩ ሃይ ባይ ካላገኘ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ አደጋ እንደሚያስከትል ሥጋቱን በመግለጽ ድርጊቱንም ተቃውሟል፡፡

በትግራይ ክልልና በሕወሓት የተሰነዘረውን ተቃውሞ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ድርጊቱን ሐሳብን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ ነፃነት መሆኑን በመግለጽ፣ አፀፋዊ ምላሽ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በመስጠት አጣጥሎታል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ ገዥ ፓርቲ ብአዴን ይኼንኑ ጉዳይና ሌሎች አገራዊና ክልላዊ ፖለቲካ ሁኔታዎችን የሚተነትን ሰነድ ለከፍተኛ አመራሮቹ በመበተን ውይይት አድርጓል፡፡ ሪፖርተር ያገኘው ይህ የብአዴን ሰነድ የክልሉ ነዋሪዎች በስፋት ያውለበለቡትን ሰንደቅ ዓላማ በተመለከተ፣ ‹‹ተግዳሮቶች›› በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር መነሻውንና አንድምታውን የተመለከተ ሰፊ ትንታኔ ሰጥቶበታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማም ሆነ የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ በባህር ዳርም ሆነ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ለውጡን በመደገፍ ሲደረጉ በነበሩት ሠልፎች ደጋፊዎች ሲያውለበልቧቸው አለመታየቱ፣ የወቅቱ ፖለቲካ ተግዳሮትና የሕግ ጥሰት መሆኑን ሰነዱ ያትታል፡፡ ነገር ግን ለተስተዋለው ችግር ማኅበረሰቡን ከመውቀስ ይልቅ፣ ብአዴን ራሱንና ኢሕአዴግን እንዲሁም ሁለቱም የሚመሩዋቸውን መንግሥታዊ አስተዳደሮች ተጠያቂ አድርጓል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ መተግበር ከጀመረ 23 ዓመታት የደፈነ ቢሆንም፣ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያረፈው ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነትና እኩልነት ተከባብረው ለመኖር ቃለ የመግባታቸው ምልክት ስለመሆኑ በማስገንዘብ፣ ሕዝቡ እንዲቀበለውና እንዲታገልለት የተከናወነው ሥራ ደካማ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ሰንደቅ ዓላማን ከእነ ትርጓሜው የማወቅና የማክበር ጉዳይ በተቋማት ግቢ ውስጥ እንዲውለበለብ በማድረግ ተቀባይነትን አግኝቷል ማለት እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡

‹‹በሕዝቡ ውስጥ ያሉ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን መመለስ ባልቻልንበት ልክ፣ ለሕዝቡ የአንድነት ምልክት ነው ያልነውን ዓርማ የድህነትና የበደል ምልክት አድርጎ ቢመለከተው ሊገርመን አይገባም፤›› ሲል ምክንያታዊ ትንታኔ ያቀርባል፡፡

በሌላ በኩል ይኼንን ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች ካጎናፀፈው ሐሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ መብት ጋር አያይዞ መመልከት ተገቢ መሆኑን ያትታል፡፡

‹‹ሕዝብ ምን ያስብ እንደነበር የሚታወቀው ነፃ ሲሆን ነው፡፡ ነፃ ሲሆን ያሰበውን ተግባር ያወጣዋል፡፡ አሁን ሕዝቡ (በሰንደቅ ዓላማ ውስጥ) ያሳየን ውስጡን ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማን በሕግ አስገዳጅነት ብቻ እንዲወደድ የማድረግ ሙከራና እልህ አስወግደን ራሳችንን በመፈተሽ የአስተምህሮ ሥራችንን ማጠናከርና ከሕዝቡ ጋር መክሮ መግባባት ይገባናል፤›› በማለት ይደመድማል፡፡

ከሰሞኑ የኦነግን ዓርማ የኦሮሞ ሕዝብ የትግል ምልክት በማድረግ የፖለቲካ ታጋዮቹን ለመቀበል የኦሮሞ ወጣቶች የዓርማው ቀለማት የሆኑትን አረንጓዴና ቀይ ቀለማት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች፣ አደባባዮች እንዲሁም በግለሰቦችና በተቋማት ንብረቶች ላይ በመቀባታቸው ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ነዋሪዎች ጋር ግጭት በመቀስቀስ ከፍተኛ ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ ይኼንን ድርጊት የአዲስ አበባ አስተዳደር በማውገዝ ሐሳብን በማንኛውም ሰንደቅ ዓላማና ምልክት መግለጽ መብት ቢሆንም፣ የሌሎች ነዋሪዎችን መብት የመጣስ ድርጊት ሕገወጥ በመሆኑ ሊቆም  እንደሚገባ በመግለጽ፣ መታረም ካልቻለ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ባለፈው ሳምንት ገልጾ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሐሙስ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በተመሳሳይ ጉዳይ በሰጡት አስተያየት በዋናነት ሁለት መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡

አንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማውን የመቀየር ሙሉ ፍላጎት ካለው በውይይትና ሕገ መንግሥታዊ መንገድን በመከተል መቀየር ይቻላል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የስንደቅ ዓለማ ምርጫን ወደ አደባባይ ይዞ መውጣት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት አካል መሆኑን፣ ነገር ግን አንዱ በሌላው ላይ ምርጫውን ለመጫን መሞከር ሌላኛም ጉልበቱን አሰባስቦ አፀፋዊ ተግባር እንዲፈጽም በማነሳሳት አገሪቱን ወደ ኋላ ሊመልሳት፣ ከዚህ አልፎም እንደ ጎረቤት አገሮች ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ሊያፈርሳት እንደሚችል በመግለጽ ማኅበረሰቡ በሐሳብና በውይይት የመግባባት መንገድን እንዲመርጥ አሳስበዋል፡፡

የሕግ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

የተለያዩ አገሮች ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማቸው፣ የዜጎቻቸውን ክብር እንዲያገኝና በማንም የማይገሰስ ሞገስን የተጎናፀፈ የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ሆኖ ከፍ እንዳለ እንዲውለበለብ አስገዳጅ ሕጋዊ ግዴታን ይጥላሉ፡፡

በተለይም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የገነቡ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ደግሞ ለብሔራዊ ሰንደቃቸው ክብር እንደሚገባው ቢያምኑም፣ ዜጎቻቸው የተቃውሞ ወይም የልዩነት ሐሳባቸውን ለመግለጽ የብሔራዊ ሰንደቃቸውን ክብር ቢያዋርዱ ሐሳብን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ ነፃነታቸውን ተጠቀሙ እንጂ፣ ድርጊታቸው የሕግ ተጠያቂነትን ፈጽሞ አያስከትልም፡፡ ይኼንን መሰል መብት ለዜጎቻቸው ከሚያጎናጽፉ አገሮች መካከል ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ዴንማርክና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተቃራኒው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማቸውን ክብርና ዓርማ በሕግ ከሚያስጠብቁ አገሮች መካከል ደግሞ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ፈረንሣይ፣ እስራኤልና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ጎራ ትካተታለች፡፡ ለዚህም ሲባል የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት አዋጅ 546 የዛሬ አሥር ዓመት በማፅደቅ ተግባራዊ አድርጋለች፡፡

ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ክብር የማዋረድ፣ ሕዝብ በተሰበሰባቸው አካባቢዎች የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን ክብር የሚያጎሉ ተግባራትን በመፈጸም በሰንደቅ ዓላማው ላይ ጉዳት ማድረስ የወንጀል ተግባር መሆኑንና የአንድ ዓመት እስራት ወይም የሦስት ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣትን ያስከትላል፡፡

አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ሌላ የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 16/1988 ፀድቆ ሥራ ላይ እንደዋለ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ አቶ እንዳልካቸው ገረመው ይገልጻሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን ከወሰነ በኋላ ዓርማ እንደሚኖረው፣ በዓርማው መተላለፍ ስለሚገባው ጥልቅ መልዕክት እንጂ ስለዓርማው ዓይነት እንደማያመለክት ገልጸዋል፡፡

የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 16 ላይ የዓርማው ዓይነት መቀመጡን፣ በኋላም በ1989 ዓ.ም. የዓርማውን መጠን በተመለከተ ማሻሻያ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ የሰንደቅ ዓላማው አዋጆች ምንም ዓይነት የወንጀል ግዴታ የማይጥሉ መሆናቸውንዋ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከምርጫ 97 በኋላ የመጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 546 ወጥ የሆነ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም የሚል ማሻሻያ አንቀጽ በማካተት፣ ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ በሕዝብ መድረኮች መጠቀም እንዳይቻል ገድቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰንደቅ ዓላማ ክብር እንዳይጎድል በሚል መነሻ የወንጀል ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ የተከለከሉ ተግባራትን መዘርዘሩን ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም ይኼንን ሕግ ያወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ገደቡን አልፎ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት ላይ የወንጀል ተጠያቂነትን በመጣል ስህተት መፈጸሙን ይገልጻሉ፡፡

አቶ እንዳልካቸው እንደሚሉት ይህ ተግባርም ብዝኃነትን ማስተናገድ መሠረታዊ ዓላማው ያደረገ ሕገ መንግሥትን መጋፋት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎቹ አካባቢዎች የሚታየው የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን ይዞ የመውጣትና የመፎካከር ተግባር ግን፣ ከዚህ የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ፡፡

ከዚያ ይልቅ የማኅበራዊ መሠረት ሽሚያ በፖለቲከኞች መካከል በመካሄድ ላይ እንደሚመስል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጥ ኃይል ቃል እየገባ ያለው የለውጥ ፕሮግራም ተጠንቶ የታወቀ አለመሆኑ፣ ወይም ድንበር የሌለው በመሆኑ የተፈጠረ ፉክክር ባህርይ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ እነዚህን ፍላጎቶች ማስተናገድ የማይችል በመሆኑ፣ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይንም የሪፎርሙ አካል አድርጎ ለመመለስ መሰናዳትና ይኼንንም በይፋ በመግለጽ ውዝግቡን መፍታት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -