Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገሪቱን ለኪሳራ የዳረገ የማዳበሪያ ግዥ የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ የክዋኔ ኦዲት እየተካሄደ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አገሪቱን ለኪሳራ የዳረገውን ማዳበሪያ 450 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ግዥ እንዲፈጸም ያደረጉ አካላት ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል የክዋኔ ኦዲት እያካሄደ ነው፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር እያካሄደ የሚገኘውን የክዋኔ ኦዲት በሚቀጥለው ሁለት ሳምንታት አጠናቆ ሪፖርት ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡ በኦዲት ግኝቱ መሠረት ጥፋተኛ የሚባሉ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስቴር፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ግብርና ንግድ ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

በሦስቱ መንግሥታዊ ተቋማት ስምምነት በ2006 ዓ.ም. 450 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የተገዛ ማዳበሪያ፣ ለአምስት የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ላቋቋሟቸው ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ተከፋፍሎ ነበር፡፡ ማዳበሪያውን ተረክበው ለየአካባቢያቸው የአፈር ዓይነት ተስማሚ እንዲሆን አድርገው አዘጋጅተው ለማቅረብ የተስማሙት ጊቤ ደዴሳ፣ መርከብ፣ እንደርታ መልህቅና በቾ ወረሶ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ናቸው፡፡

ነገር ግን ለእነዚህ ማዳበሪያ ፋብሪካዎች የቀረበው ማዳበሪያ ከአካባቢያቸው የአፈር ዓይነት ጋር የሚጣጣም ብቻ ሳይሆን፣ ከፋብሪካዎቹ ሥሪት ጋር የሚሄድ ስላልነበር ፋብሪካዎቹን ጭምር ለብልሽት ዳርጓል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታትም ማዳበሪያ የተከማቸባቸው መጋዘኖች ጠንቀኛውን ማዳበሪያ በመያዛቸው ለኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ተጨማሪ ወጪ እያስከተሉ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ይህንን ችግር ለመፍታት ሁለት ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ተገልጿል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት ግብይትና የገጠር ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመፍትሔ ሐሳቦቹ ያላግባብ ግዥ እንዲፈጸም ያደረጉ አካላትን ተጠያቂ ማድረግና ማዳበሪያውን በድጋሚ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡

በማዳበሪያ ግዥው ላይ ተፈጽመዋል ከተባሉ ስህተቶች መካከል፣ ከዝርዝር መሥፈርት (ስፔሲፌኬሽን) ውጪና ከሚያስፈልገው በላይ ማዳበሪያ በብዛት መግዛት፣ ማዳበሪያው የተገዛላቸው የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ይሁንታ ሳይሰጡ መግዛት ተጠቃሾች ስህተቶች ናቸው፡፡

ይህ እንዲሆን ያደረጉ የሦስቱ መንግሥታዊ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ አቶ ሰይፉ እንደገለጹት፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት እያካሄደ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ሪፖርቱ ይቀርባል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ ይህ ማዳበሪያ ዘመናዊ አሠራርን ተከትሎ ወደ ጥቅም መለወጥ ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ለሞሮኮ ግዙፍ ኩባንያ ኦሲፒ ሥራው የተሰጠው ሲሆን፣ ይህ ኩባንያ አምስቱ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች የገጠማቸውን ችግር ከፈታ በኋላ ፋብሪካዎችን ለአምስት ዓመታት በሊዝ ያስተዳድራቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ከጥቅም ውጪ የነበሩት ማዳበሪያዎች ጥቅም ለመስጠት እንደሚችሉ የታሰበ ሲሆን፣ የሞሮኮ ኩባንያ ለዩኒየኖቹ የዕውቀት ሽግግር ያደርጋልም ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች