Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የብርሃን ለሕፃናት ስኬቶች

ወ/ሮ እቴነሽ ወንድማአገኘሁ በሕፃናት አካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚሠራ ‹‹ብርሃን ለሕፃናት›› የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ወርክ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ሲል ድኩማን ድርጅት፣ በኋላ ደግሞ ተሃድሶ ድርጅት ውስጥ፣ ከዚህም ውጪ በኤስኦኤስ በልዩ ልዩ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ በእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ቆይታቸው፣ እንዲሁም በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ያስተዋሉትን የኅብረተሰቡን ችግሮች ከግንዛቤ በመውሰድ መፍትሔ መስጠት የሚያስችለውን ግብረ ሠናይ ድርጅት ለማቋቋም በቅተዋል፡፡ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ወ/ሮ እቴነሽን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅትዎ በአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው?  

ወ/ሮ እቴነሽ፡-  አካል ጉዳተኛ ሕፃናትንና ለችግር የተጋለጡ ቤተሰቦቻቸው ላይ ነበር ያተኮረው፡፡ በኋላ ግን ድርጅቱ እያደገና እየሰፋ ሲመጣ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ችግር ለመፍታት አካል ጉዳተኛ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ትኩረት መደረግ ያለበት ሌላውንም ኅብረተሰብ ማቀፍ ያስፈልጋል ከሚል የፀና እምነት ላይ ደርሷል፡፡ ሌላውንም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ የሚቻለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን ነው፡፡ በተለይ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን በተመለከተ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ አናሳ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የተዛባ ግንዛቤ ስላለ ነው፡፡ በትምህርት ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እንኳ ሲታይ ትምህርት መግባት ካለባቸው ሕፃናት መካከል የገቡት አራት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ የአካል ድጋፍም መሣሪያም ሲታይ በጣም ውድ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተደራሽ አይደሉም፡፡ ይህም በመሆኑ የአካል ድጋፍና የትምህርት መሣሪያዎች ወይም ቁሳቁሶችን ድርጅቱ በነፃ ይሰጣል፡፡ ራሱን የቻለ የአካል ድጋፍ ማምረቻ ወርክሾፕም አለው፡፡ ወርክሾፑንም ያቋቋምነው መቀመጫቸውን ህንድና እንግሊዝ ውስጥ ካደረጉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው፡፡ የብርሃን ለሕፃናት ድርጅታዊ ተልዕኮ አካል ጉዳተኛንና ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት በማንኛውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ውስጥ ጤናማና ምሉዕ ሕይወት የሚመሩበት፣ ራሳቸውን ችለው ብቁ ዜጎች የሚሆኑበትን ማመቻቸት ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረጉ የድጋፍ፣ የእንክብካቤና የተሃድሶ ተግባራትን ማከናወን፣ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን መደገፍ፣ አካል ጉዳተኝነትንና ኤችአይቪን በመከላከል ድጋፍ ላይ መሥራት ነው፡፡ በጥምረት ከተለያዩ አካላት ጋር ተባብሮ መንቀሳቀስና የአቅም ማጎልበት ሥራዎችንም ያከናውናል፡፡   

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በየትኞቹ ክልሎች ነው የሚንቀሳቀሰው?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ በሚገኙት ስምንት ክፍላተ ከተሞች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ በልደታ ክፍለ ከተማ፣ በአማራ ክልል ጎንደርና ደሴ ከተሞች፣ እንዲሁም በጭልጋ ወረዳ 5 ቀበሌዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱና በገጠራማ አካባቢዎች ይንቀሳቀሳል፡፡ ከትምህርት ቤቶችና ከመምህራን ጋር የምናከናውናቸው ተግባራት አሉ፡፡ ከትምህርት ቤቶች ጋር የምንሠራው ሥራ መምህራንን በማሠልጠን ያተኮረ ነው፡፡ የትኩረት አቅጣጫውም መምህራኑ በትምህርት ቤትና በመማርያ ክፍሎች ውስጥ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን እንዴት ነው መርዳት የሚችሉት? በሚሉትና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ትምህርት ቤቶች ከመግቢያው በራቸው ጀምሮ እስከ የመማርያው ክፍሎች ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተደራሽ የሚሆኑበትን መንገድ የማመቻቸትም ተግባር አቅም በፈቀደ መጠን እያከናወንን ነው፡፡ የትምህርት መገልገያ መሣሪያዎችን እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በትምህርት ዘርፍስ ምን አከናወናችሁ?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- ድርጅቱ ሕፃናትን በቀጥታ ከመርዳትና ከማገዝ ጎን ለጎን ዘላቂ ለውጥ በሚያመጡና የፖሊሲ መሻሻሎችን በሚጠይቁ ተግባራት ውስጥ በመሳተፍ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህንን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በብርሃን ለሕፃናት ሐዋሳ ፕሮጀክት እየተሠራ ያለውን ትምህርት ተኮር እንቅስቃሴ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፕሮጀክቱ በተቻለ መጠን ሁሉን አቀፍ አተገባበርን በመከተልና ተቀናጅቶ መሥራትን በማንገብ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኮሌጆች፣ ከትምህርት መምርያ ጽሕፈት ቤት፣ ከትምህርት ቤቶች፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ድጋፍ ከሚያደርጉለት አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በትምህርት ተኮር እንቅስቃሴው ያስገኛቸውን ውጤቶች ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- ከውጤቶቹ መካከል አንዱና ዋነኛው በትምህርት አተገባበር ዙሪያ የተከናወኑት ናቸው፡፡ በመሠረቱ አካቶ ትምህርትን ለመተግበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አንዱ ተግዳሮት በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ የኮሌጅ ምሩቅ መምህራን የብሬልና የምልክት ቋንቋ ተግባራዊ ሥልጠና አለመኖሩ ነው፡፡ ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ብርሃን ለሕፃናት ከዚህ ቀደም ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ጋር ቅርብ ትስስር በመፍጠር ከኮሌጁ ተመርቀው የሚወጡ መምህራን በሙሉ በሁለቱ ሠልጥነው በመውጣት ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች በየአካባቢያቸው እንዲደገፉ የተደረገው ጅማሮ በሁለቱ ባለድርሻ አካላት ጥረት፣ እንዲሁም በኮሌጁ ሴኔት ይሁንታ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ዲፓርትመንት ለማስከፈት ተችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ በኮሌጁ ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ ሠልጥነው የሚወጡ ዕጩ መምህራን በብሬልና በምልክት ቋንቋ በመሠልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነው የብሬልና ምልክት ቋንቋ ሞጁል በዘርፉ ባለሙያዎች እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ ይህም ተሞክሮ በደቡብ ክልልም ይሁን በኢትዮጵያ ደረጃ ብቸኛ ተሞክሮ በመሆኑ በኢትዮጵያ ላሉ ከ35 በላይ ኮሌጆች፣ በሐዋሳ መምህራን ኮሌጅ አማካይነት ለሌሎች ኮሌጆች ተሞክሮው በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

ከኮሌጁ ተመርቀው የሚወጡ መምህራን ወደ የአካባቢያቸው ሲመለሱ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች እንዲደግፉ የማድረግ ሥራም ይሠራል፡፡ በዚህም መሠረት በሐዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ውስጥ አንድ፣ በሐዋሳ ዙሪያ አሥራ አንድ፣ በሲዳማ ዞንና በአላባ ወረዳ በነፍስ ወከፍ አንድ፣ በአጠቃላይ 22 የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶች በቁሳቁስ እንዲሟሉና አገልግሎት ላይ እንዲውሉ በማድረግ ተማሪዎች እንደየፍላጎታቸው የሚደግፉበት ሁኔታ እንዲመቻችም ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አጋርነት ለማጠናከርና በአካቶ ትምህርት ዙሪያ ክልላዊ መግባባት ለመፍጠር፣ እንዲሁም ልምድ ለመለዋወጥ ላለፉት አምስት ዓመታት ክልላዊ የአካቶ ትምህርት ፎረም መካሄዱ ከተገኙት ውጤቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህም ፎረም አገራዊና ክልላዊ፣ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ በዚህም ሰፊ መግባባት ተደርሶበታል፡፡ የልዩ ፍላጎት በመምርያ ደረጃ፣ እንዲሁም የልዩ ፍላጎት ባለሙያ በሥራ ሒደት እንዲመደብ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኙና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆን መምህራን በልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት እንዲሠለጥኑ ተደርጓል፡፡ ይህ በመሆኑ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍና ግንዛቤ ጨምሯል፡፡ በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኙ 942 አካል ጉዳተኛ ሕፃናት የተለያዩ ድጋፍ ማግኘታቸው ሌላው ውጤት ሲሆን፣ ከእነዚህም 477 ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ተችሏል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጀመር በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ቁጥር 92 ብቻ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- በሐዋሳ አንገብጋቢ ችግር በነበረበት ሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ሴት ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ ድርጅቱ መሥራቱ ይነገራል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የተደረገውን ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- የሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ በሐዋሳ ካሉ ስምንት ክፍለ ከተማዎች በቆዳ ስፋት 40 በመቶ ድርሻ የሚይዝና የከተማው ገጠራማ ክፍል ነው፡፡ በአካባቢውም የሚማሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወደ መሰናዶ ለመግባት በቱላ ብቻ ሳይሆን፣ በአጎራባች ባሉ እንደ መልጋ ወረዳን ጨምሮ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በተለይ አካል ጉዳተኞችና ሴት ተማሪዎች ሐዋሳ ቤት ተከራይተው ትምህርታቸውን ለመቀጠል አቅም ስለማይኖራቸው ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ሥራ መሰማራት ነው፡፡ ይህን አንገብጋቢ ችግር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ብርሃን ለሕፃናት በቱላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ስምንት ክፍል ያለው ሕንፃ በመገንባት ችግሩ እንዲቀረፍ አድርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር መሰናዶ የገቡ ልጆችን ለማብቃት በተደረገው ተከታታይ የማጠናከሪያ ፕሮግራም በተገነባው ሕንፃ የተማሩ የመጀመርያ ዙር ተፈታኞች መቶ በመቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ትምህርት ቤቱ ምቹና ጥራት ያለው ሞዴል ትምህርት ቤት በመሆን ለተከታታይ ዓመታት በክልል ደረጃ ተሸላሚ እንዲሆን ብርሃን ለሕፃናት የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማድረጉም በተጨማሪም በአካቶ ትምህርት ክበባት የታቀፉ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተሰጧቸውን በማሳደግ እስከ ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሕፃናት ፓርላማ አመራር ድረስ ተሳትፏቸው እንዲያድግ ድጋፍ ተደርጓል፡፡  

ሪፖርተር፡- የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ብቃት ለማሳደግ ያካሄደውን እንቅስቃሴ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- ከዚህ ቀደም የሃዌላ ቱላ የአካል ጉዳተኞችና የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ መቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ የትምህርት ውጤታቸው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ የቴላ ስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ማሽቆልቆል ታሪክ ለመሆን ችሏል፡፡ ይኼም ብርሃን ለሕፃናት በ2005 ዓ.ም. የስምንተኛ ክፍል አጠቃላይ ውጤት 49 በመቶ መሆኑንና እንደ አንድ የትምህርት ባለድርሻ አካል ኃላፊነታችንን መወጣት ስላለብን ዓመቱን ሙሉ የሚሰጥና ወቅታዊ ክትትልና ምዘና የሚካሄድበት የሴቶችና ልጃገረዶች የማጠናከሪያ ትምህርት በ13 የስምንተኛ ብሔራዊ ፈተና የሚያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች፣ በአሥረኛና በአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ተችሏል፡፡ ይኼውም በ2005 ዓ.ም. የነበረው የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት 49 በመቶ ሲሆን፣ በ2006 ዓ.ም. 83 በመቶ፣ በ2007 ዓ.ም. 98.86 በመቶ፣ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. 99 በመቶ እንዲሆን ብርሃን ለሕፃናት ከፍተኛውን ሚና ተወጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በጤናው ዘርፍ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር አብራችሁ የምትሠሯቸው ተግባራት ይኖራሉ?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- ሕፃናት የፀረ ስድስት ክትባት እንዲያገኙ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ቤተሰቦች በክትባቱ ዙሪያ የተዛባ አመለካከት ስላላቸው ሕፃናቱ እንዳይከተቡ፣ ባለሙያዎችም ተደራሽ የማያደርጉበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ እኛ በመሀል ገብተን ቤተሰብን የማነቃቃትና ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ እንዲሁም ሕፃናቱ ክትባቱን እንዲያገኙ የበኩላችንን አድርገናል፡፡ በየቀበሌው ከተመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ጋር የመግባቢያ ሰነድ እየተፈራረምን የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛ ከእኛ የመስክ ሠራተኞች ጋር በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ ግንዛቤ እናስጨብጣለን፡፡ ይህንኑ ሥራችን በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በወቅቱ ለነበሩት ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሐሳቤን አቅርቤ ነበር፡፡ ሚኒስትሩም ሐሳቡን ቢቀበሉትም አገራዊ ለማድረግ በኤክስቴንሽን ሠራተኞች ላይ ጫና ማብዛት ይሆናል፡፡ ለወደፊቱ ግን እናየዋለን አሉኝ፡፡ በተረፈ በእኛ በብርሃን ለሕፃናት በኩል ወደፊት ያሰብነው ነገር ቢኖር አካል ጉዳተኛ ሕፃናት እንዳይወለዱ ቅድመ መከላከል ማድረግ፣ ከተወለዱ በኋላ ደግሞ በሕፃንነታቸው አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉና የተከሰተው የአካል ጉዳት ገፍቶ ሥራ ለመሥራት ወደማያውክ ደረጃ እንዳይደርስባቸው ዕገዛ እንዲደረግ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኛ ሕፃን እንዳይወለድ ማድረግ ይቻላል እንዴ?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- አዎ! ይኼም በቅድመ እርግዝና፣ በእርግዝና በወሊድ ጊዜ የሚደረጉ አንክብካቤዎች አሉ፡፡ ይኼውም አንድ አባትና እናት ልጅ መውለድ በቅድሚያ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እናት ደግሞ በእርግዝና ወቅት የተሻለ ምግብ መመገብና ቀለል ያለ ሥራ መሥራት አለባት፡፡ በሌላ ሳይሆን በሠለጠነ ባለሙያ መውለድ አለባት፡፡ አንዲት ነፍሰ ጡር የተመጣጠነ ምግብ ካላገኘች የአዕምሮ ዕድገት ዝገመት ያለበትን ሕፃን የምትወልድበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በወሊድ ወቅት በትክክል የማይመጣው ሕፃን አንዳንድ ጊዜ ታፍኖ የሚሞትበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ወይም ደግሞ ለአካል ጉዳተኝነት ይዳረጋል፡፡ በሠለጠነ ባለሙያም በሚወለድበት ጊዜ ወይ ሕፃኑ ይወድቃል፣ ወይ በሚሳብበት ጊዜ የመሳቢያው መጫን የአዕምሮውን ክፍል ይነካና ይጎዳል፡፡ በትምህርት ቤትም አካል ጉዳተኛ የሚሆኑ ልጆች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ በጥፊ ተመትተው ጆሯቸው የማይሰሙ ልጆች አሉ፡፡ በአግባቡ ያልተቀመጠን መድኃኒት ሕፃናት አግኝተው ከተጠቀሙ ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና፣ በወሊድ ጊዜና በዕድገት ላይ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ተደምሮ ሕፃናት አካል ጉዳተኛ እንዳይሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ በታዳጊ ሕፃናት አካል ጉዳተኛ የሚሆኑበትን ምክንያት ልንገታው፣ ልናቆመውና ልንቀንሰው እንችላለን፡፡      

ሪፖርተር፡- መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስመልክቶ እስካሁን እየተሠራበት ያለው ሕግ በሥራችሁ ላይ ያስከተለው ችግር አለ?

ወ/ሮ እቴነሽ፡- አስቸግሮናልም፣ አላስቸገረንም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት እኛ ሁለቱንም  የአድቮኬሲና አገልግሎት የመስጠት አሠራር በመሥራታችን ነው፡፡ አድቮኬሲውን ወደ ሠርቶ የማሳያ ሥራ ለወጥነው፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ቤቶች ለማንኛውም ተማሪ ምቹ መሆን አለባቸው እያልን ድሮ በቃል የምናስተምረውን አሁን እዚያው እየሠራን እናሳያቸዋለን፡፡ ሌላ ደግሞ የቻይልድ ፕሮቴክሽን ፖሊሲ [የሕፃናት ጥበቃ ፖሊሲ] አወጣንና ከእኛ ጋር አብረው ለሚሠሩ መንግሥታዊ አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ሒደቱንም እንከታተላለን፡፡ ይህም ሆኖ ግን የምንችለውን ያህል መሄድ አልቻልንም፡፡ የግሉ ዘርፍ እንደነዚህ ዓይነት ሥራ የሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማገዝ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ  ድርጅቶችም በተቻለ መጠን ግልጽ መሆንና ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው መሥራት አለባቸው፡፡ መንግሥት ለግምገማ መምጣት ብቻ ሳይሆን መከታተል፣ ያጠፋውን መቅጣትና መቆጣጠር አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...