Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና አዲሱ ረቂቅ አዋጅ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና አዲሱ ረቂቅ አዋጅ

ቀን:

ሰሞኑን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን አስመልክቶ በ2001 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ ያሻሽላል ተብሎ የታመነበት ረቂቅ ወጥቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ የድርጅቶችን ስም ከመቀየር ጀምሮ ወደ 50 በሚጠጉ የአገልግሎት ሥርዓቶች ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡

በረቂቅ አዋጁ መሠረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከውጭ ገንዘብ ተቀብለው መብት ላይ መሥራት እንደሚችሉ፣ 10/90 የሚባል የገቢ ማሰባሰቢያ ገደብ እንደሌለ፣ በብሔራዊ ደረጃ ያሉ ድርጅቶች ወደ ዓለም አቀፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ደግሞ በብሔራዊ ደረጃ ተደራጅተው መንቀሳቀስ እንደሚችሉ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡

‹‹ፈንድ ወይም የገቢ ማስገኛን በተመለከተ እስካሁን ያለው አካሄድ የመጨረሻው አማራጭ ነው፡፡ ይህም ማለት እየሞትክ መሆኑን ካሳየኸን ነው ገንዘብ የምትሰበስበው የሚል አመለካከት ነው የያዘው፡፡ አሁን ግን ድርጅቶቹ እንደ አንድ ስትራቴጂ አስቀምጠው መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ ላይ ምንም ዓይነት ገደብ አይጣልም፤›› ያሉት የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት አባሉ አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል ናቸው፡፡ 

- Advertisement -

የብሔራዊ ምክር ቤቱ ፈንድ የሚገኘው ከአባላት ወዋጮ ሲሆን፣ በነፃ የመንቀሳቀሱ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ እስካላስከተለበት ድረስ ከመንግሥት ተገቢውን በጀት ሊያገኝ እንደሚችል፣ ወጪ መጋራትን በተመለከተ ከተጠቃሚዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችልና በጎጂ ልማድ ላይ መሥራት እንደሚቻል ከአቶ ደበበ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ፍትሕና የሕግ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት አዘጋጅቶ ለክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት አባላት ለውይይት ከቀረበው ከዚሁ ረቂቅ አዋጅ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች›› ወደሚል፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ደግሞ ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ›› ተብለው  እንዲሰየሙ ይደንግጋል፡፡

ከእነዚህም መካከል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመሠርቱ፣ የመንግሥት አካል ያልሆኑ፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ፣ ሕጋዊ ዓላማን ለማሳካት ተመዝግበው ወይም ሳይመዘገቡ የሚንቀሳቀሱ ስብስቦች ናቸው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ደግሞ የሕግ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሲሆን፣ አራት ዓላማዎች አሉት፡፡ ከዓላማዎቹም መካከል በሕገ መንግሥትና ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የመደራጀት መብትን በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ይፈጥራል የሚል ይገኝበታል፡፡ ድርጅቶቹ እንዲስፋፉና ግልጽነትና ተጠያቂነትን በተከተለ መንገድ ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ የሚደግፉ ሁኔታዎች ማመቻቸት ከዓላማዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ድርጅቶችን መመዝገብ፣ ሥራዎቻቸውን መደገፍ፣ ማሳለጥና ማስተባበር፣ ዓመታዊ የሥራና የገንዘብ እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት መመርመርና አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ በሚካሄዱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ በወቅታዊ መረጃ በመደገፍ፣ መተንተን፣ ለሕዝብ ማሳወቅ፣ መንግሥት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ሕጎች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታት፣ ከኤጀንሲው ከሚጠብቁ ተግባራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ኤጀንሲው በመንግሥትና በሶሻል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ የሚቋቋም ቦርድ፣ እንዲሁም በሚኒስትሩ አቅራቢነት በመንግሥት የሚሾም ዋና ዳይሬክተርና አስፈላጊ ሠራተኞች እንደሚኖሩት፣ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆኖ የቦርዱ ሊቀመንበር በቦርድ አባላት እንደሚመርጥና የሥራ ዘመኑም ሦስት ዓመት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ከሆነ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አመሠራረት ራሱን የቻለ መርሆች አሉት፡፡ በመርሆቹ መሠረት አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ አባሉ በፈለገ ጊዜም መወጣት ይችላል፡፡ ማንኛውም አባል አንድና እኩል ድምፅ ያለው ሲሆን፣ ድርጅቶች ለአባላት ትርፍ ለማከፋፈል በማሰብ ሊቋቋሙ አይችሉም፡፡

ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ወይም ኅብረቶች የጋራ ዓላማቸውን ለማሳካት በመካከላቸው በሚያደርጉት ስምምነትና ኅብረት ወይም የኅብረቶች ኅብረት መመሥረት ይችላሉ፡፡ የምሥረታውም ዓላማ ለጋራ ግቦች ስኬታማነት አገልግሎቶቻቸውን መደገፍ፣ የሐሳብ፣ የመረጃና የልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ የአባልነትን አቅም የመገንባት ተግባራትን ማከናወን፣ ሥነ ምግባርና የሙያ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን ናቸው፡፡

ሕጋዊ ሰውነት ለማግኘት የሚፈልጉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኤጀንሲው መመዝገብ ይችላሉ፡፡ ኤጀንሲውም ማመልከቻ በቀረበለት በ30 ቀናት ውስጥ አመልካቹን ድርጅት በመመዝገብ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡ ካልሰጠ ወይም የሚሰጥ መሆኑን ካላሳወቀ ምዝገባውን ለመከልከል የሚያስችል ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለው ይቆጠራል፡፡ ምዝገባው ወደ አሥር የሚጠጉ ውጤቶች አሉት፡፡ ከውጤቶቹም መካከል መሥፈርቱን አሟልቶ የተመዘገበ ድርጅት የሕግ ሰውነት ይኖረዋል፡፡ በስሙ ይከሳል፣ ይከሰሳል፣ ውል ይዋዋላል፣ በመረጠው የሥራ መስክ የመሰማራት መብት አለው፣ ለዓላማው መሳካት በማንኛውም ሕጋዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ የመሳተፍ መብት ይኖረዋል የሚሉና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

ማንኛውም ድርጅት ከተመዘገበ በኋላ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ፈቃድ ሳያገኝ በጤና፣ በትምህርትና በሕፃናት ክብካቤ ሥራ ላይ መሰማራት አይችልም፡፡ ከዚህም ሌላ አስቀድሞ ኤጀንሲውን በማሳወቅ በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ቅርንጫፍን ሊከፍት የሚችል ሲሆን፣ እንዲሁም የስያሜና የምልክት፣ የሥራ ዘርፍና የዋና መሥሪያ ቤት አድራሻና የሥራ ክልል ለውጥ ሲያደርግ ለኤጀንሲው ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ የምዝገባ ሰርተፊኬቱንም በማሳየት በስሙ የባንክ ሒሳብ መክፈት እንደሚችል፣ ይህንንም በአምስት ቀናት ውስጥ ለኤጀንሲው ማሳወቅ እንዳለበት ከረቂቅ አዋጁ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምዝገባ ወረቀት ሊሰረዝ የሚቻለው በፍርድ ቤት በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ ሲሆን፣ እንዲፈርሱ የሚደረገው ደግሞ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ነው፤ እንዲሁም ሁሉንም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ያቀፈና በአባላት ሙሉ ተሳትፎ የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት ይቋቋማል፡፡ ማናቸውም በዚህ ሕግ መሠረት የተመዘገቡ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባል መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ አደረጃጀቶች እንደሚኖሩት፣ የራሱንም መተዳደርያ ደንብ፣ እንዲሁም ዘርፉ ሊከተለው የሚገባውን የሥነ ምግባር ደንብና ማስፈጸሚያ ሥልት እንደሚያወጣ፣ በድርጅቶች ምዝገባና አስተዳደር ላይ ለኤጀንሲውና ለቦርዱ ምክረ ሐሳብ እንደሚያቀርብ፣ ዘርፉን እንደሚወክልና እንደሚያስተባብር መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የውይይቱ ታዳሚዎችም በየተራ በሰጡት አስተያየት ረቂቅ አዋጁ የሚያስደስትና የሚያስገርም ነው ሲሉ አወድሰውታል፡፡ በዚያው መጠንም ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው፣ እንዲሁም ታማኝነትና ብቃት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገንዝበዋል፡፡ ይህን ረቂቅ አዋጅ አሁን ባለበት ሁኔታ ወይም ከ80 በላይ ተቀባይነት አግኝቶ ከፀደቀ ለተግባራዊነቱ ከወዲሁ ራሳቸውን አዘጋጅተው መጠበቅ እንዳለባቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚያም ሌላ ንብረት የማፍራትን፣ ወጪ መጋራትን፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ መሥራትን፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከመንግሥት ፈንድ የማግኘትን፣ በብሔራዊ ደረጃ ያሉት ድርጅቶች ወደ ዓለም አቀፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ድርጅቶች በብሔራዊ ደረጃ ተደራጅተው መንቀሳቀስ መቻል አለመቻላቸውን በተመለከተና ሌሎችም ከረቂቅ አዋጁ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች በታዳሚዎች ቀርበው በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት ዋና ዳይሬክተርና እንዲሁም የፍትሕና የሕግ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት አባል ሰፋ ያለ ገለጻና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል፡፡

የኅብረቱ ዋና ዳይሬክተር መሸሻ ሸዋረጋ (ዶ/ር) የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጁ እመርታ የሆኑ ለውጦች እንደታዩበት፣ ከለውጦቹም መካከል አንዱ ብሔራዊ ምክር ቤት ለማቋቋምና የባንክ አካውንት መክፈት ድርጅቶቹ በሕግ እስካልተከለከለ ድረስ በፈለጉትና በመረጡት አካባቢዎች ምግባረ ሰናይን ማከናወን መቻላቸውና የይግባኝ ባይነት መብታቸው መረጋገጡ እንደሚገኝበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ ፓርላማችን ነው ለማለት ያስችላል፡፡ እርስ በርሳችን እንድንቆጣጠር፣ ችግሮችን በግልጽ ለመለየትና ከችግሮቻችን ተነስተንና ተምረን የበለጠ እንድንሠራ ያነሳሳናል፡፡ መረጃ፣ ተሞክሮና ልምድ እንድንለዋወጥ የበኩሉን ሚና ይጫወታል የሚል የፀና እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር ድርጅቶቹ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ በቅድሚያ ከኤጀንሲው ፈቃድ እንዲያመጡ ይጠየቃሉ፡፡ ፈቃዱን ከኤጀንሲው ለማግኘት የቢሮክራሲያዊ አሠራሩ ተዳምሮ በነፃነታቸው ላይ ትልቅ ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ግን ለችግሩ መፍትሔ ማስቀመጡ እንደ ትልቅ ስኬት አድርገው እንደሚያዩት ነው የተናገሩት፡፡

ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ድርጅቱን የመዝጋት ሥልጣን ያለው የኤጀንሲው ዳይሬክተር ቢሆንም፣ ያልተገደበ ሚናና ያልተገራ ሥልጣን ባላቸው አንዳንድ የዴስክ ሳይቀሩ ድርጅቶችን ይዘጋሉ፡፡ በቅርብ ጊዜም ከ200 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች ተዘግተዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገሮች መካከል ታንዛኒያ 3,000፣ ኡጋንዳ 7,000፣ ኬንያ 35,000 ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሲኖራቸው፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ከ3,000 በላይ እንዳላት የሦስቱም አገሮች ሕዝብ ብዛት ቢደመሩ ወይም ቢጠቃለሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር ያህል እንደማይሆን፣ ከፍተኛውን የሕዝብ ቁጥር ባላት ኢትዮጵያ ውስጥ  4,000 የማይሞሉ ድርጅቶች መኖራቸው አስገራሚ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...