የጤና ተቋማትን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ መድኃኒቶችን፣ ምግብና ምግብ ነክ ነገሮች ላይ ፍተሻና ቁጥጥር ለማድረግ በአዋጅ ቁጥር 661/2002 የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ የ2009 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡
በሪፖርቱ መሠረት ለድኅረ ገበያ ጥናት ከተሰበሰቡ 215 የማንጎ ጁሶች መካከል 103 ናሙናዎች መሥፈርቱን ሳያሟሉ ተገኝተዋል፡፡ ምርቶቹም ከገበያ እንዲሰበሰቡ፣ ወደፊትም ጥበቃና ቁጥጥር እንዲደረግባቸው አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ሌሎች እንደ ለውዝ ቅቤና የሕፃናት ምግብ ናሙናዎችም በምርመራ ሒደት ላይ ናቸው፡፡
በተቋሙ የምግብ ላቦራቶሪና በተስማሚነት ምዘና ድርጅት ላቦራቶሪ በ283 ናሙናዎች ላይ በተሠራ የኮንሳይንመንት ጥራት ምርመራ 76ቱ መሥፈርቱን ሳያሟሉ ቀርተዋል፡፡ ከ120 የጁስ ናሙናዎች ውስጥ 20ዎቹ፣ ከ28 የጨቅላ ሕፃናት የወተት ናሙናዎች 22ቱ፣ ከ94 የዘይት ናሙናዎች 19ኙ፣ ከ13 የጨው ናሙናዎች ስድስቱ፣ ከ16 የቆርቆሮ አሳ ሶስቱ፣ ከ21 ካችአፕ አራቱ፣ ከ5 ኑድልስ ሁለቱ መሥፈርቱን ሳያሟሉ መቅረታቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
አግባብ ያልሆነ አመራረት የሚከተሉ 16 የከረሜላ ፋብሪካዎችም ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ከረሜላ ፋብሪካ እንዳላቸው በማስመሰል አየር በአየር የሚሠሩ 13 ተቋማት ላይም ዕርምጃ ተወስዷል፡፡
በባለሥልጣኑ የምግብና ጤና ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ አብነት ወንድሙ እንደሚሉት፣ ተቋማቱ ከረሜላ ለማምረት ሲጠቀሟቸው የነበሩ ማቅለሚያዎችና ሌሎችም ግብዓቶች ካንሰር አምጭና ከደረጃ በታች የሆኑ ናቸው፡፡ የሚጠቀሟቸው ማቅለሚያዎች ከየት እንደሚመጡና በምን ያህል መጠን መጠቀም እንዳባቸውም ተቋማቱ እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡
‹‹ከነጭ ከረሜላዎች ውጪ አብዛኛው በአገሪቱ የሚመረቱ ከለር ያላቸው ከረሜላዎች አግባብ ያላቸው ማቅለሚያዎችን አይጠቀሙም›› ብለዋል፡፡
እንደእሳቸው ገለጻ፣ አገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ላይ ባዕድ ነገር የመቀላቀል ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እንዲህ ባሉ ተግባራት የሚሰማሩ ፈቃድ የሌላቸው ሕገወጦች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ተቋማትን ለመቆጣጠር የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከክልል ተቆጣጣሪዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ለ39 ተጨማሪ ምግብ፣ ለአምስት የጨቅላ ሕፃናት፣ ለስምንት የታዳጊ ሕፃናት፣ በጠቅላላው ለ58 አዳዲስ የምግብ ዓይነቶች ባለሥልጣኑ ፈቃድ መስጠቱን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ለ776,216.44 ቶን ምግብና 73,579.128 ቶን የምግብ ጥሬ ዕቃ ጥራትና ደኅንነቱ ተረጋግጦ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የመመልቀቂያ ፈቃድም ተሰቷል፡፡
በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ለ559 መድኃኒቶች ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻና በመደበኛ ቁጥጥር የተያዙ አግባብነት የሌላቸው 84,472,452.675 ብር የሚገመቱ የአገልግሎት ዘመን ያለፈባቸው ሕገወጥ መድኃኒትና ዕቃዎች፣ 2828.71 ቶን የተበላሸና የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈ የምግብና የምግብ ጥሬ ዕቃ እንዲወገዱ ተደርጓል፡፡
በዕለቱ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረበው ኤፍኤምሀካ ብቻ አልነበረም፡፡ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በመድኃኒት አቅርቦት፣ ሥርጭት፣ በሕክምና፣ በሕክምና መሣሪያዎችና በሌሎችም የአስተዳደር ጉዳዮች ዙርያ የታዩ ስኬቶችንና የአፈጻጸም ክፍተቶችን እንዲሁም የመፍትሄ ዕርምጃዎችን ጭምር ያካተተ ሪፖርት አቅርቧል፡፡
ኤጀንሲው በ2009 የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት 6,000,000,130 ብር ዋጋ ያለው መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን ግዥ ለማከናወን አቅዶ ነበረ፡፡ ይሁንና በኤጀንሲው በኩል የተፈፀመው ግዢ የብር 5,117,381,498.51 ወይም የዕቅዱን 85 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾች የሚቀርቡ አቅርቦቶች ግዢ ዘግይቶ መጀመር፣ አቅራቢ የታጣላቸው ግብአቶች መኖር ለተፈጠረው ክፍተት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩልም አጋር ድርጅቶች 4,906,392,101.34 ብር ዋጋ ያላቸው ግብዓቶች ማቅረባቸውም በኤጀንሲው በጀት የተገዙ የሕክምና ግብዓቶች ወጪ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡
1,027,303,531.64 ብር በመደበኛ በጀትና 51,067,672.68 ብር ዋጋ ያላቸው በጤና ፕሮግራም በጀት ከአገር ውስጥ አምራቾች ለመግዛት የውል ስምምነት ተፈጽሞ ነበር፡፡ ይሁንና በውጭ ምንዛሪ እጥረትና የአገር ውስጥ ግዥ ዘግይቶ በመጀመሩ ለኤጀንሲው ማስረከብ የቻሉት የውላቸውን 52 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ 14,400,000,00 ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያዎች ሥርጭት ለማከናወን ታቀዶ 8,000,011,518.95 ብር ዋጋ ያላቸው ግብዓቶች ብቻ ለማሰራጨት ተችሏል፡፡ ይህም ከ2008 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከተሰራጨው ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ቢሊዮን ብር ቅናሽ ማሳየቱ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
የመጋዘንና የቢሮ ጥበት መኖር በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ከታዩ ክፍተቶች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ የተገነቡ መጋዘኖች የወለል ጥራት መጓደል፣ የኤጀንሲው መጋዘኖች በመጋዘን መሣሪያዎች በደህንነት ካሜራዎች እንዲሁም የእሳት አደጋን መከላከል በሚችሉ መሣሪያዎች አለመደራጀታቸው ችግሩን እንዳባባሰው በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡
ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም. የሚኖረውን የመሠረታዊ መድኃኒት የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት የግዥ ትንበያም በሪፖርቱ ተካቶ ቀርቧል፡፡ ለ2010 ዓ.ም. የበጀት ዓመት 2,781,421,904.73 ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያዎት የግዢ ሒደት ተጀምሯል፡፡
ቋሚ ኮሚቴውም፣ የሁለቱን ተቋማት የ9 ወራት ሪፖርት መልካም የሚባል አሠራር እንደሚያሳይ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ማብራርያ የሚሹ ጥያቄዎችም ከተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዘሪሁን አበበ፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የመድኃኒት ችግር እንዳለና አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ‹‹ኢትዮጵያ መድኃኒት እንዳይገባ የተፈረደባት አገር ነች፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ስኳር፣ ግፊት፣ ካንሰር፣ ስትሮክ ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በከፍተኛ መጠን እየተሰራጩ ነው፡፡ ለእነዚህ በሽታዎች የሚሆኑ ከፍተኛ ፈዋሽነት ያላቸው ዓለም እየተጠቀመባቸው ያሉ መድኃኒቶች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ አይደለም፤›› በማለት ዓለም እየተጠቀመባቸው የሚገኙ መድኃኒቶችን ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ጉዳዩ እንዲታሰብበትና ምላሽ እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
ከምግብ ጋር ባዕድ ነገር ቀላቅለው የሚሸጡን ሕገ ወጦች በተመለተ የሚሠሩ ሥራዎች ከአዲስ አበባ ውጭ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ፣ ወጣቶች በሥነ ተዋልዶ የጤና ችግሮች በሱሰኝነት መዘፈቃቸውንና በወጣቶች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክረው መሠራት ኮሚቴው አስተያየት ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩልም በመድኃኒት አቅርቦት ረገድ ከመጋዘን ጋር የተያያዙ ችግሮች መንግሥትን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጉት እንደሚገኙና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር እንደሚያስፈልግ በዕለቱ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል፡፡