Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክትምባሆን የሚከለክለውን ሕግ የመፈጸም ፈተና

ትምባሆን የሚከለክለውን ሕግ የመፈጸም ፈተና

ቀን:

በተለያዩ ጊዜያት የተሠሩ የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ትምባሆ በዓለም ላይ ሰፋ ያሉ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡ በዓመት አራት ሚሊዮን አካባቢ የሆነው ሞት በትምባሆ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፣ ይህም ትምባሆ ከአሥር አዋቂ ለአንዱ ሞት ምክንያት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በጥናቶቹ ትንበያ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2030 በአጠቃላይ ሞትና በትምባሆ ምክንያት የሚመጣ ሞት በፍጥነት እየጨመረ እንደሚሄድ ነው፡፡ በትምባሆ ምክንያት የሚመጣውን የሞት ቁጥርም በዓመት ወደ አሥር ሚሊዮን ወይም ከስድስት ሰው አንዱ የሚሞትበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ይታመናል፡፡ ይህ ማለት በአሁኑ ወቅት በሕይወት ያሉ ወደ 500 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በትምባሆ ምክንያት መሞታቸው አይቀርም ማለት ነው፡፡ ይህ አኃዝ በአንድ ወቅት ባደጉ አገሮች የሰፋ እንደሆነ መረጃዎች ቢያሳዩም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩ ባላደጉትና በማደግ ላይ ባሉት አገሮች እጅጉን ተስፋፍቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2030 አሁን ካለበት 50 በመቶ በትምባሆ ምክንያት ከሚመጣው ሞት 70 በመቶው በማደግ ላይ ባሉት አገሮች እንደሚሆን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ችግሩን የበለጠ የሚያወሳስበው ደግሞ አሁን ዓለም የገባችበት የሉላዊነት (Globalization) ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ትምባሆ ከአንዱ አገር ወይም አኅጉር ወደ ሌላው በቀላሉ እንዲዳረስ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትምባሆን የማስተዋወቂያና የማስፋፊያ የመገናኛ ዘዴዎች መስፋፋታቸው የባህል ልውውጥ በቀላሉ መከሰቱ ትምባሆን በማስፋፋት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የችግሩ አሳሳቢነት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትምባሆ ቁጥጥር ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዲይዝ ያስቻለ ሲሆን፣ ይህ አቋም ወደ ተግባራዊ ቁርጠኝነት ተቀይሮ ዓለም አቀፉ የሕግ ማዕቀፍ እንዲቀረጽ ምክንያት ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 በዓለም የጤና ድርጅት አባል አገሮች “WHO Framework convention on Tobacco Control” የፀደቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 172 አገሮች ስምምነቱን ፈርመውታል፡፡ ይህ ስምምነት ትምባሆን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዘዴዎችን የቀረፀ ሲሆን፣ አባል አገሮችም ላይ የተለያዩ ግዴታዎችን ይጥላል፡፡ አገራችን እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. ስምምነቱን የተቀበለች ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ ስምምነቱን በምክር ቤት በማፅደቅ ተግባራዊ የሚሆንበትን የሕግ ሥርዓት ነድፋለች፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለክልከላው ሕጉን መሠረት አድርገን አንዳንድ ነጥቦች የምናነሳ ሲሆን፣ በዚህ ሰሞን ሕጉን ለማስፈጸም የተጀመሩ ሙከራዎችን የማገዝ ዓላማ ይኖረዋል፡፡

አከራካሪው የትምባሆ ክልከላ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ትምባሆ ሕዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ እንዳይጨስ መከልከል በብዙ አገሮች በሕግ ሥርዓት ተቀርጿል፡፡ የሕግ ሥርዓቱ ሲቀረፅ ግን ትምባሆን የመከልከል ዕርምጃው አከራካሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ መንግሥትና አንዳንድ የሲቪል ማኅበረሰብ ትምባሆ በጤና ላይ የሚያስከትላቸውን ጉዳት ምክንያት በማድረግ የክልከላውን ተገቢነት ያሰምሩበታል፡፡ በሌላ በኩል ግን መንግሥት ትምባሆን ለመከልከል የሚያወጣው ሕግ ተገቢ አለመሆኑን፣ ችግሩንም የሚያባብስ እንጂ የሚቀንስ አለመሆኑን በመግለጽ የሚቃወሙ አካላት አሉ፡፡ ትምባሆ የሚጠቀሙ (የሚያጨሱ፣ የሚያኝኩ ወይም የሚስቡ) አካላትና በትምባሆ ንግድ የሚተዳደሩ ታላላቅ የዓለም ኩባንያዎች ትምባሆን መከልከል ከግለሰብ ምርጫና የንብረትና የውል ነፃነት መብት ጋር ይጋጫል በሚል ተቃውሟቸውን ያሰማሉ፡፡

በተለያዩ አገሮች ሕግ ትምባሆ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዳይጨስ የሚከለከልባቸው ምክንያቶች ቢያንስ ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመርያው ምክንያት የትምባሆ ተጠቃሚዎችና አምራቾች የሚፈጥሩት አሉታዊ ሁኔታ (Negative externality) ኃላፊነት ያለባቸውን ሰዎች ከኃላፊነት ነፃ ስለሚያደርግ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የትምባሆ አምራች ድርጅትም ሆነ አጫሽ በድርጊታቸው ምክንያት በሌላው ኅብረተሰብ ላይ ተጨማሪ ወጪ የሚያስከትሉ ቢሆንም ይህንን ወጪ አይሸፍኑም፡፡ እነርሱ በማጨሳቸው ወይም ትምባሆ በማምረታቸው ሌላው ታሞ ብዙ ወጪ ሲያወጣ፣ በሥራ ቦታና በሕዝብ ተቋማት ለጤና አጠባበቅ ለሚወጡ ወጪዎች ምክንያት ቢሆኑም አጫሾችም ሆነ ትምባሆ አምራቾች ተጠያቂ አይሆኑም፡፡ የሕግ ማዕቀፍ ተቀርፆ ተጨማሪ ታክስ ቢጣልባቸው፣ የሚፈቀደው የትምባሆ መጠን ቢወሰን ወይም የመጠቀሚያው ቦታ ቢወሰን ለችግሩ ምክንያት የሆኑ አካላት ወጪውን የሚሸፍኑበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ ሁለተኛው ዋናው ምክንያት ትምባሆ በማይጠቀመው ሰው (passive smoker, secondhand smoker) ላይ የሚያመጣው አደጋ ነው፡፡ የሚያጨሱ ሰዎች ራሳቸው ላይ ከሚያመጡት የጤና ችግር ባልተናነሰ በአካባቢው የሚገኘው የሚያጨሰው ሰው ላይ የሚያመጡት አደጋ አለ፡፡ የሚያጨሱት ሰዎች ለመርዛማ ጋዞች፣ ኬሚካሎችና ትናንሽ የጭስ እንክብሎች በመሳብ ጤናቸው የሚጓደልበት ሁኔታ ሰፊ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፉ በሚያጨሱ ሰዎች የሚጐዱ ሰዎችን ለመታደግ ይጠቅማል፡፡ ሦስተኛው ፀባይን የመግራት የሕግ ሐሳብ ነው፡፡ ትምባሆን መከልከል ሕግ የሕዝቡን ፀባይ፣ ሥነ ምግባር ለመግራት (Shaping Preference) ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሚያጨሱ ሰዎች በአብዛኛው ማጨስ ጥሩ አለመሆኑንና ማቆም እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ፡፡ የሕጉ ክልከላ እንዲህ ዓይነት ሞራል ያላቸውን ተጠቃሚዎች ያበረታታል፡፡ ሌላው በአደባባይ ማጨስ በሕፃናት ላይ ያለው ተፅዕኖ ነው፡፡ ሕፃናት በሌሎች ሲፈጸም የሚያዩትን ነገር ኮፒ ለማድረግና ለመከተል ጉጉት ያድርባቸዋል፡፡ የሚያውቋቸው ሰዎች የሚያደርጉትን ድርጊት መደበኛ የኑሮ ሒደት አካል እንደሆነ በማሰብ ሊፈጽሙት ይችላሉ፡፡ ብዙ አጫሾች ማጨስ የጀመሩት ‹እከሌ› ሲያጨስ ተመልክተው፣ ዘመናዊነት መስሏቸው፣ ሌሎች ያደረጉትን ለመሞከር በማሰብ መሆኑን መረዳት ብዙም አያስቸግርም፡፡ ከዚህ በመነሳት ሕግ ትምባሆ በአደባባይ እንዳይጨስ የሚከለክለው ሕፃናቱ በተሳሳተ ሞዴል እንዲያድጉ፣ የሚያጨሱም የማያጨሱበትን ምልልስ (frequency) እንዲቀንሱ ብሎም እንዲያቆሙ ለማስቻል ነው፡፡

ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች ትምባሆን የሚከለክል ሕግጋት ይቀረጹ እንጂ በተለያየ አመክንዮ የሚቃወሙ አልጠፉም፡፡ እነዚህ አካላት በዋናነት የሚያነሱት ትምባሆ መከልከል የግለሰቦችን ነፃነት መጋፋት ነው የሚል ነው፡፡ ግለሰቦች የሚከተሉት ፀባይ የሚያስከትለውንም ችግር እያወቁ ወደውና ፈቅደው የሚፈጽሙትን ድርጊት መከልከል ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ትምባሆ በጤና ላይ የሚያስከትለውንም ችግር አነስተኛ ግምት በመስጠት የማይቀበሉትም አይጠፉም፡፡ በኤችአይቪ ኤድስ ወይም በትራፊክ አደጋ የሚሞተውን ሰው ቁጥር በትምባሆ ከሚሞተው ጋር እያነፃፀሩ የትምባሆን አሉታዊ ውጤት ለመቀበል የሚቸገሩ አሉ፡፡ ትምባሆን በቤት (indoor) እና በአደባባይ (outdoor) በሚል በመክፈል የተለያዩ ሕግጋትን መቅረጽ መነሻ የሚያደርገው የባለቤትነት መብትን መሆኑን በመግለጽ እንዲህ ዓይነት ደንቦች ወጪ የመሸፈን አመክንዮን ፍትኃዊ እንደማያደርጉ ይገልጻሉ፡፡ ውጩ የሕዝብ ስለሆነ ትምባሆን በመከልከል የሚያስከትለውን ወጪ መንግሥት እንዲሸፍን፣ በቤት ውስጥ ያለውን የመከልከል መብትን ለባለቤቱ በመተው ከወጪው ነፃ ማድረግ ፍትኃዊ አለመሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ ጉዳዩ ለግለሰቦች ምርጫና ነፃነት መተው እንደሚገባው ይገልጻሉ፡፡

የሁለቱ ጽንፍ ሙግት ገለልተኛ ዳኝነትን የሚፈልግ ቢሆንም፣ የትምባሆ አሉታዊ ውጤቶችን በየዕለቱ ለሚያስተውል ብልህ ሰው ትምባሆ ሕዝብ በሚበዛበት ቦታ እንዳይጨስ የሚከለክል ሕግ በአገራችን መውጣቱ ቢዘገይ እንጂ አግባብነቱ አከራካሪ አይሆንም፡፡ ሕጉ የሚያጨሱ ሰዎችን ከራሳቸው ያልተገባ ድርጊት ይታደጋቸዋል፣ የሕዝብን ጤንነት ይጠብቃል፣ ሕፃናትን በጥሩ ሥነ ምግባር ለማሳደግም ይረዳል፣ ሳያጨሱ የሚጐዱ ንፁኃንንም ፋታ ያሳጣል፡፡ ያም ሆኖ ትምባሆን የሚከለክሉ ሕግጋት አፈጻጸም ፈተና የሚበዛባቸው እንደሆኑ በጽሑፉ የኋላ ክፍል የምንመለከተው ይሆናል፡፡

የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን

ይህ ኮንቬንሽን በ2003 በዓለም የጤና ድርጅት የወጣ ሲሆን፣ አገራችን ከመፈረም ባለፈ በሕግ አውጪው ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 3 እንደሚያመለክተው የኮንቬንሽኑ ዓላማ አሁን ያለውንና የወደፊቱንም ትውልድ ትምባሆ ማጨስና ለትምባሆ ጭስ መጋለጥ ከሚያስከትሏቸው አስከፊ የሆኑ የጤና፣ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የአካባቢ ብክለት ችግሮች የመጠበቁ ጉዳይ መላውን ሕዝብ ያሳሰበ መሆኑንና አገሮች ኮንቬንሽኑን በማፅደቅና ተግባራዊ በማድረግ ትምባሆ ያስከተለውንና የሚያስከትለውን ችግር ለመግታት ተገቢውን ቁጥጥርና የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው፡፡

ኮንቬንሽኑ የትንባሆ ፍላጐት መቀነስና የአቅርቦት ቁጥጥር ስትራቴጂን አካቷል፡፡ በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 4 መሠረታዊ የትግበራ መርሆች የተካተቱ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው ትምባሆ መጠቀምና ለትምባሆ መጋለጥ የሚያስከትለውን የጤና ችግርና ሱስ የማስያዝ አቅም እንዲያውቅ መደረግ እንዳለበት ለዚሁም ውጤታማ ሕግ የማውጣት፣ የማስፈጸም፣ የአስተዳደር ሥራዎችና ሌሎችም ዕርምጃዎችን መንግሥት መውሰድ እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ ኮንቬንሽኑ የትምባሆ ቁጥጥር ዘዴዎችን በዋናነት የትምባሆ ፍላጐትን (demand side) እና አቅርቦትን (supply side) በመቀነስ ላይ ያነጣጠሩ እንዲሆኑ ያሳስባል፡፡ በፍላጐት መስመር የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 6 እስከ 14 በአቅርቦት በኩል ደግሞ ከአንቀጽ 15 እስከ 17 የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተካተዋል፡፡

በኮንቬንሽኑ ክፍል 3 የተለያዩ የትምባሆን ፍላጐት መቀነሻ ዘዴዎች ተካተዋል፡፡ እነዚህም የዋጋና የግብር ዕርምጃዎች እንዲሁም ዋጋ ነክ ያልሆነ የትምባሆ ፍላጐት መቀነሻ ስልቶች በመባል ተከፍለዋል፡፡ ዋጋ ነክ የትምባሆ ቁጥጥር በትምባሆ ላይ የሚጣል የግብርና የትምባሆ ዋጋ ትምባሆ የሚያስከትለውን የጤና ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት ጉዳቱን ለመከላከል አስተዋጽኦ ማድረጉን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲሆኑ ሊያሳስብ በተለይም የዓለም አቀፍ ተጓዦች ከግብርና ከጉምሩክ ግዴታ ነፃ የትምባሆ ምርቶች የሚያገኙት አሠራር እንዲከለከል ወይም እንዲወሰን ያስገድዳል፡፡

ዋጋ ነክ ያልሆኑ የትምባሆ ቁጥጥር ስልቶች ውስጥ ለትምባሆ ጭስ መጋለጥን መከላከል፣ የትምባሆ ምርቶች ይዘትና ወደ አካባቢ የሚለቁትን ንጥረ ነገሮችን በተመለከተ የመንግሥት አካላት መረጃ እንዲኖራቸው ስለማስፈለጉ፣ የትምባሆ ምርቶች ማሸጊያና ገላጭ ጽሑፎች ምን ዓይነት መልዕክት እንዴት ማስተላለፍ እንዳለባቸውና የትምባሆ ምርቶችን የማስተዋወቅና ተጠቃሚነትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያበረታታ ተግባር በአጠቃላይ ክልክል ሊሆኑ እንደሚገባና እነዚህን ግዴታዎች ለመተግበር የኮንቬንሽኑ አባል አገሮች ተገቢውን የትምህርትና የሕዝብ ንቃት ማጐልበትን ጨምሮ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡

የኮንቬንሽኑ ክፍል 4 ማለትም ከአንቀጽ 15 እስከ 17 የትምባሆ አቅርቦትን የሚቀንሱ የቁጥጥር ስልቶች አካቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሕገወጥ የትምባሆ ምርቶች ንግድን የማስወገድ፣ በሕፃናትና ለሕፃናት የትምባሆ ምርቶች ሽያጭ ማከናወን ስለመከላከልና ከትምባሆ ምርቶች ሽያጭ ጋር የተያያዘ የገቢ ምንጭ ላላቸው ግለሰቦች አስተማማኝ የሆነ አማራጭ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ ማስቻል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ኮንቬንሽኑ አባል አገሮች መደበኛ ሪፖርት በማቅረብ፣ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትና ዓለም አቀፍ ትብብር የሚኖርበትን ሁኔታ ያካተተ ሲሆን፣ ወደ 172 አገሮች የፈረሙት ሁሉንም የዓለም አገሮች ያስማማ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ ኮንቬንሽኑን የሚያግዝ ሕገወጥ የትምባሆ ንግድን ማስወገጃ ፕሮቶኮል እ.ኤ.አ. በ2012 በተጨማሪነት በኮሪያ ፀድቋል፡፡

ትምባሆና አገራችን

አገራችን እንደሌላው የዓለም ክፍል ሁሉ ዜጐቿ በትምባሆ ጐጂነት ተጠቂ የሆኑባት፣ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የሕግና የተቋም አደረጃጀት በመቅረጽ በመንቀሳቀስ ላይ ናት፡፡ አገራችን የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽንን ያፀደቀች ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቷ የዜጐችን የጤንነት መብት እንዲሁም በንፁህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብትን የሕግ ዋስትና ሰጥታለች፡፡ የኅብተሰቡን ጤና ደኅንነት በተሻለም ለማረጋገጥ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 661/2002 አውጥታለች፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ትምባሆን ጨምሮ በኅብረተሰቡ ጤንነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚኖራቸውን ንጥረ ነገሮች የመመርመር፣ የመቆጣጠር፣ ፈቃድ የመስጠትና መመሪያዎች መተግበራቸውን የሚያረጋግጥ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ተቋቁሟል፡፡ በዚህ አዋጅ ትምባሆን የተመለከተ ድንጋጌ የሚገኘው በአንቀጽ 22 ላይ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው ትምባሆ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ወይም ለማከፋፈል ከአስፈጻሚው አካል ልዩ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡ የትምባሆ ማስመጣት፣ ማከፋፈል፣ ሽያጭ አጠቃቀም አስተሻሸግና ገላጭ ጽሑፍ፣ የማስተዋወቅና የአወጋገድ ተግባራት በደንብ እንደሚወሰን ተደንግጓል፡፡

ትምባሆን የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ሳይዘጋጅ መዘግየቱ አገራችን ለችግሩ አሳሳቢነት የሰጠችውን አነስተኛ ቦታ አመላካች ነው፡፡ አገራችን እ.ኤ.አ. 2003 የተፈረመውን ኮንቬንሽን ፈራሚ ሆና ሕግ በማውጣትና ትምባሆን በመቆጣጠር ረገድ እስከ እ.ኤ.አ. 2009 (2002 ዓ.ም) መዘግየቷ ተገቢ አልነበረም፡፡ ከአዋጁም በኋላ ማስፈጸሚያው ደንብ ለአራት ዓመታት ሳይወጣ ቀርቶ ዘንድሮ መውጣቱ ቢረፍድም ምስጋና የሚነፈገው አይደለም፡፡ በዚህ ሳምንት የፀደቀው ስለ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር የወጣው ደንብ የትምባሆ ዝግጅት ቁጥጥርን በተመለከተ በክፍል ሦስት ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ የድንጋጌዎቹን ይዘት በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክር፡፡

ትምባሆን በተመለከተ ደንቡ አራት ጉዳዮችን የሚገዙ አራት ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ እነዚህም የትምባሆ ዝግጅት ፈቃድ፣ ሕፃናትን ከትምባሆ ስለመጠበቅ፣ ስለትምባሆ ማሸጊያና ገላጭ ጽሑፍ እንዲሁም ማጨስ ስለሚከለከልባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት ማንኛውም የትምባሆ ዝግጅት ማስመጣት፣ ማከፋፈል ወይም መሸጥ የሚቻለው ዝግጅቱ መሥፈርቶችን ማሟላቱ ተረጋግጦ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን ብቻ ይሆናል፡፡ ደንቡ ማንኛውም ሰው የትምባሆ ምርቶችን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ አካለ መጠን ላልደረሰ ሰው እንዲጠቀም መሸጥ ወይም መገፋፋት የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ በተለይ በከተማ አካባቢዎች አካለመጠን ያልደረሱ ልጆች በአደባባይ፣ በትምህርት ቤት፣ በሺሻ ቤቶች፣ በቀን የፓርቲ ቤቶች የትምባሆ ምርቶችን ሲጠቀሙ ለሚስተዋለው ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ነው፡፡ በአዋጁ በተሰጠው ትርጉም መሠረት የትምባሆ ዝግጅት በከፊልም ሆነ በሙሉ ከትምባሆ ቅጠል የተዘጋጀ በማጨስ፣ በመሳብ፣ በማኘክ ወይም በማሽተት የሚወሰድ ማንኛውም ንጥረ ነገር ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ትምባሆ ሰፋ ያለ ትርጉም እንደተሰጠው መረዳት ይቻላል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው የኮንቬንሽኑ ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ ላይ እንደተገለጸው እ.ኤ.አ. በ2003 በዓለም የጤና ድርጅት ተባባሪነት በአገራችን በተሠራ ጥናት በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች ውስጥ 7.9 በመቶ የትምባሆ ምርቶች ይጠቀማሉ፡፡ እንዲሁም 41.2 በመቶ ወጣቶችና ሌሎች ሰዎች ትምባሆ ከሚጨስበት አካባቢ ውስጥ ይመላለሳሉ፡፡ የደንቡ ሕፃናት በአንድም በሌላ ትምባሆ እንዳይጠቀሙ መከልከሉ በአገራችን በስፋት የተንሰራፋውን ችግር ይቀንሳል የሚል ግምት አለ፡፡

ደንቡ የትምባሆ ማሸጊያና ገላጭ ጽሑፍን በተመለከተ ግልጽና ዝርዝር ይዘት ሊኖረው እንደሚገባ ደንግጓል፡፡ የምርቱን ባህሪ፣ የጤና ችግር ማስከተሉንና አደገኛነቱን የመጥቀስ ግዴታ አዘጋጁ ላይ ተጥሏል፡፡ የትምባሆ ዝግጅት ነጠላ፣ ፓኬት፣ ጥቅል ማሸጊያና የውጭ ማሸጊያ ገላጭ ጽሑፍም አስከፊነቱን፣ ለበሽታ እንደሚዳርግ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ሊገልጽ እንደሚገባው ተገልጿል፡፡

የደንቡ የመጨረሻ ግን ዋናው ይዘት ትምባሆ በማንኛውም ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ማጨስን መከልከሉ ነው፡፡ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በሕዝብ ማጓጓዛዎች ውስጥ፣ እንደ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ባሉ የመመገቢያ ቦታዎች ማጨስ ተከልክሏል፡፡ ሆኖም ለማጨሻ በተለዩ ቦታዎች ማጨስ እንደሚቻል ደንቡ ደንግጓል፡፡ የደንቡ ክፍተት እነዚህን ክልከላዎች በዝርዝር በመለየት የቅጣቱን ሁኔታ አለማመላከቱ ነው፡፡ ቅጣት ከሌለ ደግሞ ክልከላ በራሱ ጠንካራ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ቅጣት በደንቡ ላይ በግልጽ ባይመለከትም ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ማጨስ አያስቀጣም ማለት አይደለም፡፡ የደንቡ ክፍተት በአዋጁ ወይም በወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች ሊሸፈን ይችላል፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 53(1)(ሠ) ትምባሆን የተመለከቱ የንግድ ማስታወቂያዎችን ያስተላለፈ ከስድስት ወር በማያንስና ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም ከብር 5000 እስከ 10,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ሊያስቀጣ ይችላል ሲል ደንግጓል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 522 ጤናን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በሕግ የተደነገጉትን የጥንቃቄ ዕርምጃዎች መጣስ ከአንድ ዓመት የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም መቀጮ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ደንቡ ትምባሆ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች መከልከሉ በጣም ጥሩ ጅማሬ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ በማያደርጉ አጫሾች እንዳይጐዳ፣ ሕፃናትም መጥፎ አርዓያ እንዳያደርጉ፣ ልብ ያለውም አጫሽ እንዲያቆም ይበረታታል፡፡ ይሁን እንጂ ደንቡን ማስፈጸም እጅጉን አስቸጋሪ እንደሚሆን ማሰብ አያስቸግርም፡፡ አጫሽ በበዛበት፣ የትምባሆ ምርቶች ዓይነትና ብዛት ለቁጥር በሚያስቸግርበት አገር ሕጉን ማስፈጸም የማውጣቱ ያህል ቀላል እንደማይሆን ይታሰባል፡፡ ስለዚህ በሚቀጥለው ክፍል የትምባሆ ቁጥጥርን የሚያጠናክሩ መፍትሔዎችን በአጭሩ ለመጠቆም እንሞክር፡፡

መፍትሔ ቢሆን

ሕጉ መውጣቱ በጐ ጅምር ነው፡፡ ሕጉ በአግባቡ እንዲፈጸም ማድረግ ግን ፈተናና የባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ ሦስት መፍትሔዎችን መጠቆም ቁጥጥሩን እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል፡፡ የመጀመርያው የፋይናንስ ገቢን ማጠናከር ነው፡፡ መንግሥት በትምባሆ ስርጭትና ሽያጭ ላይ ታክስ በመጣል፣ በመቅጣት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ገንዘብ በመፈለግ የትምባሆ ቁጥጥር መርሐ ግብሮች እንዲጠናከሩና ሌሎች የጤና ማስፋፊያዎች እንዲጨምሩ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ሁለተኛ ትብብር ሲሆን የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 5 በሚጠይቀው መልኩ የትምባሆ ቁጥጥርን የሚያስተባብር ብሔራዊ አካል ማቋቋምና አፈጻጸሙን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ የትምባሆ ችግር በአንድ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ብቻ የሚፈጸም ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት ሊተባበሩ ግድ ይላቸዋል፡፡ የመጨረሻው መፍትሔ የትምባሆን ችግር ከጤናና የልማት መርሐ ግብሮች ጋር በማቀናጀት መፈጸም ነው፡፡ ትምባሆን የተመለከተ የነጠላ ዕቅድ፣ የሰው ኃይል አስተዳደርና በጀት ማዘጋጀት ላላደገች አገር ፈታኝ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ትምባሆን ተያያዥ ከሆኑ የካንሰር ወዘተ በሽታዎች ከወጣቶች ልማት፣ ከስፖርት ወዘተ ጋር በማቀናጀት ከተሠራ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡         

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

                     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...