Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ካቢኔ የልማት ድርጅቶችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ ወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል መንግሥት ባፀደቀው የግልና የመንግሥት አጋርነት አዋጅ ቁጥር 1076/2010 መሠረት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥሩ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በቦርድ የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ለማልማት የሚያስችል ውሳኔ አሳለፈ፡፡

በታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ፣ የከተማው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በቦርድ የሚመሩ የልማት ድርጅቶች ከግሉ ዘርፍ ጋር በሽርክና የሚያለሙበት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚባሉት የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ኤጀንሲ ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ በቦርድ የሚመሩ የልማት ድርጅቶች ከሚባሉት ውስጥ አንበሳ አውቶብስ ድርጅትን ጨምሮ በከተማው ሥር የተቋቋሙ የትራንስፖርት ድርጅቶች፣ ከነማ ፋርማሲዎች፣ ቄራዎች ድርጅትና የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእነዚህ ድርጅቶች ላይ ያለውን አክሲዮን ለገበያ በማቅረብ፣ አክሲዮን ከሚገዙ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ጋር በጋራ የመሥራት ዕቅድ አውጥቷል፡፡

አስተዳደሩ እዚህ ውሳኔ ላይ ሊደርስ የቻለበትን ምክንያት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ሲገልጹ፣ ሥራውን በአግባብ የሚረዳ ኩባንያ ለማስገባትና አገልግሎት አሰጣጡን በተሻለ ለማሳደግ፣ የሚሸጠው አክሲዮን ተጨማሪ ካፒታል የሚፈጥር በመሆኑ ተቋማቱን ለማሳደግ፣ እንዲሁም በዕውቀትና በፋይናንስ ከፍ ያለ ደረጃ የሚፈጥር በመሆኑ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአግባቡ ለመፍታት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከግሉ ዘርፍ ጋር በሽርክና ለመሥራት ሲወስን ይህ የመጀመርያው ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃ ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ሲሠራ የቆየው የፌዴራል መንግሥት በግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ የሚያስችል አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ አፀድቋል፡፡

በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸው ይታወሳል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የፈለጉ የውጭ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ በሩን የሚከፍትበት ሕግ የሌለ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የውጭ ኩባንያዎች በአገልግሎት ላይ የታሪፍ ጭማሪ እንዲደረግ የሚፈልጉ በመሆናቸው እስካሁን ሳይከፈት ቆይቷል፡፡

በግልና መንግሥት አጋርነት የመንግሥት ድርጅቶችን አክሲዮን ይዘው የማልማት እንቅስቃሴ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን የተጀመረ ቢሆንም፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ጅማሮው ተስፋፍቶ ቀጥሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች