Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ፉከራ

ትኩስ ፅሁፎች

ምርቱም፥ገለባውም፡ተደባልቋልና፥

የምታበጥረው፡ጐራው፡ና፥ጐራው፡ና።

 ዐርበኞች፡ሲመጡ፡እየተኳኰሱ፥

 ያንበጣ፡ጕዞኛ፡ይመስላል፡ርሳሱ።

 እኛው፡መጡ፥እኛም፡አየናችው፤

 መድኀኒት፡የጠጡ፡ይመስላል፡ፊታቸው።

እኛው፡መጡ፥እንደ፡ባርማሽላ፡እየተመረጡ፤

በመጡበት፡መንገድ፡መመለሻ፡ሊያጡ።

ራሰ፡ዘናኑ፥እግረ፡ውትርትሩ፥

እጁ፡መርዘኛ፡ነው፤አይኖርም፡አገሩ።

  ምናባቱ፤ንብረት፡ምናባቱ፤

ንብረት፡ባይኖረው፡ነው፡ነብር፡መፈራቱ።

  ድዋሮ፡ከጉሙ፥ጣርማበር፡የዋሉ፥

ይማግዱት፡ቢያጡ፡ነዶ፡ሣር፡ቅጠሉ፥

በመትረየስ፡ጥይት፥ባረር፡እየቈሉ፥

ያርባ፡ዓመት፡ጭንኵሮ፥ባርማሽላ፡በሉ።

 እገጭ፡እጓ፡ሲል፡ነው፡የወንድ፡አብነቱ፤

ሴትም፡ትዋጋለች፡ተረጋ፡መሬቱ። •••

ጦር፡መጣ፤ጦር፡መጣ፤ጫፉን፡ነቀነቀው፤

ጐበዝን፡ደስ፡አለው፤ፈሪንም፡ጨነቀው።

 የወንድ፡ልጅ፡እናት፡ታጠቂ፡በገመድ፤

    ልጅሽን፡አሞራ፡እንጂ፥አይቀብረውም፡ዘመድ።

  • ስብስብ በእ.ነ.ሥ. ‹‹ዝክረ አርበኞች››

* * *

‹‹ነግ በኔ ነው›› አለች ኮንዶሚኒየም!

ግራ ገባንኮ ጓዶች …ስለሕክምና ስህተት ስናወራ …ከሆስፒታል ዘበኛ እስከ ዶክተር …” ስህተት ያለ ነው ምን ታካብዳላችሁ፤” ይሉናል …ስለወታደር ስናወራ ወታደር ቦይ ፍሬንድ ካላት ልጅ እስከ ሜጀር ጀኔራል ማንትስ …” ቤታችሁ ተጎልታችሁ ጀግና አትተቹ፤” ይሉናል ….ስለዘፋኝ ስንናገር “ንጉሣችንን አትንኩ፤” ይሉናል … ስለፊልም ስናወራ ስሙኒ እያስከፈለ ፊልም ከሚያሳየው ጀምሮ እስከ ፕሮዲውሰርና ዳይሬክተር ይንጫጫብናል ….ይኼው ዛሬ ደግሞ ስለተደረመሰ ሕንፃ ልንናገር ነው ….በባሬላ አሸዋ ከሚያግዘው ጀምሮ እስከ አርክቴክትና ሲቪል መሐንዲስ ያለህ ተንጫጫብን ….ሰሚት አካባቢ ባለአራት ፎቅ ሕንፃ ተደረመሰ! አደጋው ሌሊት ስለነበር ሰው አልሞተም ተብሏል … እሺ አሁን የምኖርበት ኮንዶሚኒየም ቢሆን ኑሮ ለማንኛውም አሁንም እንላለን በተለይ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ያለው ሙስና፣ የብቃት ማነስና የግንባታ ዕቃዎች ጥራት ጉዳይ ይጤን!! እኔኮ እፈራለሁ አሁን ያለውን ዝርክርክነት ስመለከት ….ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የሕንፃ መናድና መደርመስ እንደትራፊክ አደጋ በየሳምነትና በየቀኑ እንዳይዘገብ እፈራለሁ!

–  አሌክስ አብርሃም

* * *

በስህተት ለዓመታት በእስር ላይ የቆየው ግለሰብ ነፃ ወጣ

ሰዎች በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ ወህኒ ይወርዳሉ፡፡ አልፎ አልፎም የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል፡፡ ይህም ከስህተታቸው እንዲማሩ፣ ሌሎች እንዳያጠፉ ለማስፈራራት፣ ወንጀለኛው ዳግመኛ ሌላ ወንጀል እንዳይፈጽም ለማድረግ ነው፡፡ ይሁንና የፍርድ ሒደቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተሞላ ነው፡፡ የተጠረጠረው ሰው ወንጀሉን ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ቢያዝ ጉዳዩን ለማጣራትና ተገቢውን ውሳኔ ለማስተላለፍ የሚወስደውን ጊዜ ይቀንሰዋል፡፡ ፍርዱንም ያቀላጥፋል፡፡

ነገር ግን እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ የማጣራት ሥራው ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ንፁህ ግለሰብ ወንጀሉን እንደፈጸመ ተደርጐ በስህተት ሊፈረድበትና ያለጥፋቱ ወህኒ እንዲገባ ይሆናል፡፡

የ81 ዓመቱ ፖውል ጋትሊንግ ተመሳሳይ ዕጣ ከደረሰባቸው መካከል ነው፡፡ በኒውዮርክ ከተማ ብሩክሊን ግዛት ውስጥ ይኖር የነበረው ሎውረንስ ሮበርት እ.ኤ.አ. በ1963 ቤቱ ውስጥ ሳለ ተገደለ፡፡ ለተፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ወህኒ የወረደው ግን ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ያልነበረው ፖውል ነበር፡፡ በወቅቱ ፖውል ጠበቃ ቀጥሮ ንጽህናውን ለማረጋገጥ ጥረት አድርጐ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱን የበለጠ ማሳመን የቻሉት ከሳሾቹ ነበሩ፡፡

ሁኔታው ያሳሰባቸው የፓውል ጠበቃና ባለቤቱም ምንም እንኳ ፖውል ወንጀሉን ባይፈጽምም ፍርድ ቤቱ ዋና ወንጀል አድራጊ እንደሆነ ካመነበት እስከ ሞት የሚያደርስ ከፍተኛ ቅጣት ሊጥልበት እንደሚችል ገመቱ፡፡ በመሆኑም በሁለተኛ ደረጃ ወንጀሉን እንደፈጸመ (በወንጀል ድርጊቱ ተባባሪ እንደሆነ) ለፍርድ ቤቱ እንዲያምን ግፊት አደረጉበት፡፡ ከመሞት መሰንበት ይሻላል ያለው ፖውልም እንዳሉት አደረገ፡፡ ጉዳዩን ይከታተለው የነበረው ፍርድ ቤትም የዕድሜ ልክ እስራት ፈረደበት፡፡

ይሁን እንጂ ከአሥር ዓመታት በኋላ ነፃ የሕግ አገልግሎት በሚሰጥ አንድ ተቋም ፖውል ወንጀሉን እንዳልፈጸመ ተረጋገጠ፡፡ ከእስርም ተፈታ፡፡ ከወንጀል ነፃ እንደሆነ ማንኛውም ዜጋ ሙሉ መብት አልነበረውም፡፡ የመምረጥና የመመረጥ እንዲሁም ሌሎች ሲቪል መብቶቹ ላይ ገደብ ተጥሎበታል፡፡ ስሙም ከወንጀለኛ መዝገብ ላይ አልተፋቀም፡፡

ጉዳዩ ከተከሰተ ከ50 ዓመታት በኋላ ባለፈው ሰኞ በሲቪል መብቶቹ ላይ የተጣለበት ገደብ አግባብነት የለውም በሚል ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳለት ተደረገ፡፡ ብዙ ፈተናዎች ቢጋረጡበትም በትዕግሥት ሁሉንም እንዳለፋቸው የተናገረው ፖውል ነፃ በመውጣቱ በጣም ተደስቶ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ ነፃ መውጣቱ ያስደሰታት የፖውል የቀድሞ ባለቤት ደስታዋን በእንባ ገልጻለች፡፡   

*  *  *

የአምስት ዓመት መከራና ድል በራስ አበበ አረጋይ አንደበት

በመላው ኢትዮጵያ . . . አምስት ዓመት ሙሉ የወረደውን መከራና ሥቃይ፣ ስንኳንስ ከቤታቸው ወጥተው እንዳራዊት በዱር በገደል የተቀመጡት አርበኞች ይቅሩና ማናቸውም ኢትዮጵያዊ የኾነ ሰው ዅሉ ከቶ በፍጹም የማይረሳው ለልጅ ልጅ ጽፎ የሚያስተላልፈው ነው።

ያምስት ዓመት መከራ ብዬ ስናገር የትናንትናውን የቅርቡን ሥቃያችንን ለመናገር ነው እንጂ፣ ግፈኛው ጠላታችን ሐማሴንን በመያዙ ወንድሞቻችን ኤርትራውያን በጠላት እጅ ተጨቁነው ሥቃይ ሲቀበሉ ኀምሳ ዓመታቸው ነው።

ያልፋል ተብሎ ባልታሰበው በዚያ በመከራ ጊዜያት ያላንድ ምክንያት እንዲያው በግፍ እንደ ጐርፍ ዳኝነት ገንዘቡ በኾነ በእግዚአብሔር ፊት በመጮኹ ኢትዮጵያ ዳኝነት አግኝታ ይኸው ከዚያ ቀን ዠምሮ የጠላታችን ደም በተራው ሳያቋርጥ መፍሰሱን እናያለን። ‹‹ኢትዮጵያ ርስቴ ናት›› ብሎ ብዙ ሚልያርድ ገንዘብ አውጥቶ በሠራው ቤት ሳይቀመጥበት፣ በሠራው ሥራ ሳይጠቀምበት መኼዱን አሳየን። ‹‹ንጉሥ›› ተብሎ የመጣው እንኳ ዱካ ዳዎስታ ሳይቀር በወዳጆቻችን በንግሊዞች እጅ ታስሮ ሳለ መሞቱን አሰማን።

በደጉ ንጉሣችን ብርታትና በእግዚአብሔር ቸርነት ያ ዅሉ ግፍና በደል አልፎ ዛሬ እንደዚህ አንድነት ለመሰ፟ብሰብ ስላበቃን ሳናቋርጥ እግዚአብሔርን እናመስግነው።

ይህም ዅሉ መከራ የደረሰብን ምክንያት፣ በተፈጥሮዋ ለምለምና ሀብታም በመኾኗ ጠላታችን ጣሊያን ከብዙ ጊዜ ዠምሮ ይፈልጋት ስለነበረ ነው። ለመውረርም በመጣ ቍጥር ባርበኞቻችን ኃይል ድል እየተመታ እንደ ተመለሰ የኢትዮጵያ ታሪክ በሰፊው ይናገረዋል።

ውድ አገራችንን በታላቁ እግዚአብሔር ቸርነት፣ በንጉሠ ነገሥታችን ብርታት ጨብጠን ይዘናታልና እስላምም ክርስቲያንም አንድነት ተባብረን ስላገራችን እንሥራ። አገርና ንጉሥ ቢኖረን ተሰበሰብን፤ ነጻነትን ብናገኝ እንደ ልብ ለመናገር ቻልን። በዚያ በመከራው ዘመን አርበኞች በበረሃ፣ ስደተኞች በስደት አገር፣ እስረኞች በወህኒ ቤት፣ ረዳታችንም ባላገር በሥቃይ ውስጥ ኾኖ ዅሉም ባንድ ሐሳብ ያስብ የነበረው ይኸን ያየነውን ዓለም ለማግኘት ነበርና አሁን ይኽንኑ ስላገኘነው ለእግዚአብሔር ምስጋና ስናቀርብ ለደስታችን ወሰን የለውም።

ዕድሜ ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥታችን።

ኢትዮጵያ በነጻነት ለዘላለም ትኑር።

  • ራስ አበበ አረጋይ ከ74 ዓመት በፊት፣ ሐምሌ 19 ቀን 1934 ዓ.ም. ላገር ፍቅር ማኅበር ጉባኤ ከተናገሩት ቃል በከፊል የተወሰደ፡፡

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች