Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሶማሌ ክልል የደረሰው ሰብዓዊና ፖለቲካዊ ቀውስ

በሶማሌ ክልል የደረሰው ሰብዓዊና ፖለቲካዊ ቀውስ

ቀን:

በሶማሌ ክልል ሕዝቦችና ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በክልሉ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በድሬዳዋ የተጀመረውን ጉባዔ ተከትሎ በጅግጅጋ የተቀሰቀሰው ግጭት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት በማጥፋት፣ ንብረት በማውደምና ከፍተኛ ሥጋት በክልሉ ከፈጠረ በኋላ ወደ አንፃራዊ መረጋጋት ተመልሷል፡፡ እንዲህም ሆኖ በአካባቢው የሚኖሩ ወገኖች ምግብና ውኃ በፅኑ ከመቸገራቸውም በላይ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉም በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት በክልሉ እንዲሰማራ ከተደረገ በኋላና የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ዓብዲ ዑመር መሐመድ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በክልሉ ለሁለት ቀናት የቆየው ግጭት እንዴት ሊቀሰቀስ ቻለ?

የሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች፣ የቀድሞ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን፣ የተለያዩ ምክር ቤቶች አባላትና በውጭ የሚኖሩ የሶማሌ ተወላጆች በክልሉ የሚስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ ለመምከር፣ ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ያቀዱትን ጉባዔ ለማካሄድም ከከተማዋ አስተዳደር አስፈላጊውን ፈቃድ ቀድመው ካገኙት በኋላ፣ ስብሰባው በሰላም እንዲጠናቀቅ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አመልክተው ይሁንታን አግኝተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ ይህ ጉባዔ መካሄድ የለበትም ብሎ ያወጀው የሶማሌ ክልል አስተዳደር የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለጉባዔው ፈቃድ መስጠት እንደሌለበት በይፋ ከመጠየቅ አንስቶ ከፍተኛ ጫና ሲያደርግ መቆየቱን፣ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በከተማ አስተዳደሩ ላይ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ፈጥሮ የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም፡፡ ነገር ግን ስብሰባው እንዳይካሄድ ለመከላከል በቂ ምክንያት አልነበረንም፡፡ አንደኛ ይህ የዜጎች መብት እንጂ የምንፈቅደውና የምንከላከለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለተኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ አይደለንም፤›› ሲሉ ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

ጉባዔውን ያዘጋጁት አካላት የጠየቁትም ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንጂ የተለየ ፈቃድ አለመሆኑን የተናገሩት ከንቲባ ኢብራሂም፣ ተሰብሳቢዎቹ የጠየቁት ጥበቃ በሚያርፉበት ሆቴልና በመሰብሰቢያ አዳራሹ እንዲመደብ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሶማሌ ክልል የተሰነዘረው ምላሽ እጅግ አስገራሚና ሥርዓተ አልበኝነት የታየበት ነበር ብለዋል፡፡

‹‹ስምንት መኪና የታጠቀ ኃይል የድሬዳዋ ከተማ ከሶማሌ ክልል በምትዋሰንበት በሽንሌ ዞን በኩል መጣ፡፡ ነገር ግን በሥፍራው የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ስለነበር ከድንበር አላለፈም፡፡ በዚህ በኩል ሳይሆን ሲቀር ተልዕኮ የተሰጣቸው ወጣቶች ወደ ከተማዋ እንዲዘልቁና ስብሰባው እንዲጨናገፍ እንዲያደርጉ ተሰማርተው ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ ገንዘብ በመርጨት ስብሰባው እንዲደናቀፍ ጥረት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የከተማዋና የፌዴራል ፀጥታ አካላት ተቀናጅተው ስብሰባው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ችለዋል ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የተካሄደው ጉባዔ በሶማሌ ክልል ላለፉት አራት ዓመታት የተስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የፖለቲካ መብቶች መጨፍለቅና የግለሰብ የበላይነት የነገሠበት ሥርዓተ አልበኝነት፣ እንዲሁም መደረግ በሚገባቸው መፍትሔዎች ላይ በመወያየት የፌዴራል መንግሥትና ክልሉን የሚመራው የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) በጋራ ተንቀሳቅሰው ሕጋዊ የፖለቲካ ሥርዓት በክልሉ እንዲያሰፍኑ ጫና መፍጠር መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የሚታየው አጠቃላይ የፖለቲካዊ ሥርዓት መንቀጥቀጥ መነሻ ምንጩ በሶማሌ ክልል የሰፈነው የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነትና በግለሰቡ ዙሪያ የተሰበሰቡ የጥቅም ተጋሪዎች ጭፍን እንቅስቃሴ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ይኼንን ችግር በፍጥነት መቅጨት ካልተቻለም ኢትዮጵያን የማፍረስ አደጋ የማስከተል አቅም እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

የሶማሌ ክልልን መገንጠልና የጅግጅጋ ቀውስ

በድሬዳዋ ከተማ ሐሙስ ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የተጀመረውን ስብሰባ ማደናቀፍ ያልቻለው በጅግጅጋ ከተማ የከተመው የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ሊያፈርስ የሚችል ድብቅ ሴራ ነድፎ ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ውሳኔ የማሳለፍ ዕቅድ መያዙን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ይህ ዓላማም በጥቂት የክልሉ ካቢኔ አባላት ጠንሳሽነት የክልሉን ምክር ቤት አባላት በኃይል በማስገደድ፣ የሶማሌ ክልል ከኢትዮጵያ እንዲገነጠል ውሳኔ ማሳለፍ እንደነበር ባለሥልጣኑ ያስረዳሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ መረጃ የደረሰው የፌዴራል መንግሥት እንቅስቃሴው የጥቂት የከሰሩ ፖለቲከኞች ሴራና ኃይልን ተጠቅሞ በማስገደድ ሊፈጸም የታቀደ መሆኑን በመገንዘብ፣ በጅግጅጋ ከተማ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ማንቀሳቀሱን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ የተንቀሳቀሰው የክልሉ ምክር ቤት አባላትን በማስገደድ ሊፈጸም የነበረውን ፀረ ዴሞክራሲያዊና ሕግን ያልተከተለ እንቅስቃሴ ከማስቆም የዘለለ ዓላማ እንዳልነበረው እኚሁ ከፍተኛ ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የታቀደው ሴራ የተደረሰበት መሆኑን የተረዳው የጀግጅጋው ውስን የካቢኔ ስብስብ፣ የከተማውን ሰላም የማደፍረስ ተግባር ውስጥ መግባቱን ለዚህም የተደራጁ ወጣቶችንና የክልሉን ፖሊስ ማንቀሳቀሱን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በጀግጅጋ የሚኖሩ የሌላ ብሔር አባላትን በመለየት ማጥቃት፣ መዝረፍና የእምነት ተቋማትን ማቃጠል ቅዳሜና እሑድ በመፈጸም በሺዎች የሚቆጠሩ የጅግጅጋ ነዋሪዎች ሸሽተው በቤተ ክርስቲያናት እንዲጠለሉ መገደዳቸውን የተገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን በሰጡት መግለጫም፣ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ይፋ በማድረግ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡ በሌላ በኩል የተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ከዚህም በላይ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

በሁለት ቀናት በተሰነዘረው ጥቃት ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ የነዋሪዎችን ንብረት የመዝረፍና የማውደም፣ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትንም እንዲሁ በግልጽ የመዝረፍ ተግባር መፈጸሙ ታውቋል፡፡ በጅግጅጋ ከተማ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንዲወድም ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈጠር የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ወደ አካባቢው በመዝለቅ የመከላከል ተግባር አለመፈጸማቸው ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን መግለጫ የሰጡት የፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፣ ከሰኞ ከቀትር በኋላ አንስቶ የመከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ መታዘዙን ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ የተሰማራውም የክልሉ መንግሥት በጅግጅጋና አካባቢው የተከሰተውን ቀውስ ለመቆጣጠር ከአቅም በላይ በመሆኑ፣ የፌዴራል የፀጥታ አካላትን ድጋፍ በመጠየቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሥልጣኔን ከምለቅ ብሞት እመርጣለሁ››

በዋናነት በጀግጅጋ ከተማና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች ከቅዳሜ ጀምሮ የተከሰተው ቀውስ በክልሉ መንግሥት ጥቂት አመራሮች እነሱ ያደረጁት ቡድንና የፀጥታ ኃይሉ የፈጠረው መሆኑን ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

ምክንያቱን ሲያብራሩም የሶማሌ ክልል ተወላጆች በድሬዳዋ ከተማ ያካሄዱት ስብሰባ የሶማሌ ክልል አመራሮች ከሥልጣን እንዲለቁ የታቀደ እንደሆነ በመገመት፣ ‹‹ሥልጣን ልቀቅ ተብያለሁ በማለት የክልሉ አመራር›› የቀሰቀሰው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ተግባር ውስጥም የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በግጭቱ እንዲሳተፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ አመራሮች በሙሉ ሳይመክሩበትና ስለጉዳዩ አስፈላጊነት እንኳን ሳይገነዘቡ፣ የሶማሌ ክልልን የመገንጠል እንቅስቃሴ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ሥልጣኔን ከምለቅ ሞት እመርጣለሁ›› በማለት በቀውስ ውስጥ የመሸሸግና አገርን የማፍረስ አደጋ ያዘለ እንቅስቃሴ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተ የኢሶሕዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ እድሪስ ኢብራሂም በተደጋጋሚ መረጃ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ይሁን እንጂ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ፕሮግራም ቅዳሜ ቀን በሰጡት አስተያየት ክልሉን የመገንጠል እንቅስቃሴ መኖሩን አስተባብለዋል፡፡

‹‹ለጊዜው ለመገንጠል አላሰብንም፣ በፌዴራል ሥርዓቱ እንተዳደራለን፡፡ ነገር ግን መገንጠል ምንም ሐሳብ አይደለም፣ ሕገ መንግሥቱም ለዚህ ዋስትና ይሰጣል፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን የመከላከያ ሠራዊቱ ቅዳሜ ዕለት በሕገወጥና ከሕገ መንግሥቱ በተቃራኒ፣ የሶማሌ ክልል ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳያቀርብለት በጅግጅጋ ከተማ መሰማራቱን ኃላፊው አውግዘዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከሥልጣን መልቀቅ

የፌዴራል መንግሥት ክልሉን ከሚመራው ኢሶሕዴፓ አመራሮች ጋር የተፈጠረውን ቀውስ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲመክር ቆይቶ፣ ሰኞ ዕለት ከውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ የፀጥታ ማስከበር ተግባር ለመፈጸም፣ የዚያኑ ዕለት በፍጥነት በጅግጅጋ ከተማ መሰማራቱን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡

ሌላው ጉዳይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ አሌ) ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ የሥልጣን መልቀቂያ እንዲያቀርቡና በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር በጊዜያዊነት ርዕሰ መስተዳድሩን ተክተው እንዲሠሩ መወሰኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ይህ ውሳኔ ተደፈጻሚ የሆነው በክልሉ ፓርቲ በኩል በመሆኑ፣ የሕጋዊነት ቅደም ተከተሉ በቀጣዮቹ ጊዜያት በክልሉ ምክር ቤት እንደሚፈጸም ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ይኼንንም የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ እድሪስ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ተቋማትን የማጠናከርና የሕግ ተጠያቂነትን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጅግጅጋ ከተማ አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ ነዋሪዎች አሁንም ፍራቻ እንዳላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ሰላም ማስፈን መጀመራቸው ግን ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁንም የምግብና የተለያዩ አቅርቦቶች ችግር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ከጅግጅጋ ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ግን አሁንም ችግር መኖሩን አስረድተዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ለኢቲቪ ማክሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት በስልክ እንደገለጹት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ በማረጋጋት ላይ ናቸው፡፡ በሌሎች የክልል ከተሞች መከላከያ በማረጋጋት ላይ መሆኑንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...