Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሕዴድን ስያሜና ዓርማ ለመተካት ሐሳብ ቀረበ

የኦሕዴድን ስያሜና ዓርማ ለመተካት ሐሳብ ቀረበ

ቀን:

የኦሮሞ ሕዝብን የሚወክሉ ሌሎች ፓርቲዎችን በአንድነት ለማሰባሰብም ዕቅድ ይዟል

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ከ28 ዓመታት በላይ እየተጠራበት የሚገኘውን ስያሜውን፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በሚል ስያሜ ለመተካትና ዓርማውን ለመቀየር ሐሳብ ቀረበ፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፣ ኦሕዴድ የሚለውን የድርጅቱን ስያሜ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሚል ስያሜ በመተካት፣ የፖለቲካ መሠረቱ የሆኑት የኦሮሚያ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማሳተፍና ለማገልገል መታሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡

ከመጠሪያው በተጨማሪም የሚገለገልበትን ዓርማ ለመለወጥ ሦስት ዓርማዎች ለውሳኔ ያቀረበ መሆኑን፣ የፓርቲ ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) የማያስፈልግ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚገለገልበት ዓርማና መጠሪያ የፖለቲካ ተልዕኮን የማያመለክት፣ በግለሰብ ደረጃም ለተለያዩ የንግድ ተግባራት ለሚቋቋሙ መገልገያ በመሆኑ ይኼንን መጠሪያ ለመቀየር አንደኛው ምክንያቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ድርጅት የሚለውን ስያሜ ለመተካት የተለመዱት አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜዎች ማለትም ንቅናቄ፣ ትግልና ግንባር የሚሉት መጠሪያዎች ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ተግባራትን ከመግለጽ ይልቅ ውስን የሆነ የፖለቲካ ተግባርንና የትጥቅ ትግልን የሚያመላክቱ በመሆናቸው ፓርቲ የሚለውን መጠሪያ መታሰቡ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚገለገልበትን ዓርማም ለመቀየር ሦስት አማራጭ ዓርማዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የአባ ገዳ ሥርዓት መገለጫ የሆኑትን ጥቁር፣ ቀይና ነጭ ቀለማት ከኦዳ ምልክት ጋር በተለያዩ ሦስት አቀማመጦች ለውሳኔ አቅርቧል፡፡

የኦሕዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ በተያዘው ወር ውስጥ የሚካሄድ ስለሆነ፣ የቀረቡት ዓርማዎችና መጠሪያ ስያሜ ላይ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

የስያሜ ለውጡ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚታገሉ ሌሎች ፓርቲዎችን በአንድ ጥላ ሥር ለማምጣት የሚያስችል ቅድመ እንቅስቃሴ መኖሩን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሕዴድ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ኦሕዴድ ለኦሮሞ ሕዝብ ለዓመታት ሲታገሉ የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የመሥራት ዕቅድ እንዳለው፣ ከተወሰኑት ጋርም የመጀመርያ ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አገሮች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦሮሞ ሕዝብን የሚወክሉ ፓርቲዎች በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅሰቃሴ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ሕጋዊ ዕውቅና ለማግኘት የምዝገባ ጥያቄ አለማቅረባቸውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...