Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወሰን ማስከበር ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ራስ ምታት ሆኖበታል

ወሰን ማስከበር ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ራስ ምታት ሆኖበታል

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ለመንገዶች ግንባታ መዘግየት ምክንያቱ የአቅም ማነስ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የወሰን ማስከበር ችግር መሆኑን አስታወቀ፡፡ ችግሩ ኅብረተሰቡን ለከፍተኛ ችግር ያጋለጠ መሆኑንና በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ብክነት እያስከተለ እንደሆነ የገለጹት፣ የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሲሳይ ወርቅነህ ዝናቡ ናቸው፡፡

ባለሥልጣኑ ዓርብ ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ከተለያዩ ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች የተውጣጡ የሕዝብ አደረጃጀቶችን በተለያዩ አቅጣጫዎች እያስገነባቸው  ያሉትን መንገዶች አስጎብኝቶ ነበር፡፡ በጠቅላላ 16 የሚሆኑ መንገዶች መጠናቀቅ ከሚገባቸው ጊዜ እየዘገዩ ኅብረተሰቡን ለእንግልት የሚዳርጉበት ምክንያት ገለጻ ተደርጓል፡፡ ባለሥልጣኑ ከዓመት ዓመት መንገድ የመገንባት አቅሙ እያደገ ቢሆንም፣ አሁንም  የወሰን ማስከበር ጉዳይ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ‹‹እናንተም ይህንን አይታችሁ ወደ ሕዝቡ ስትመለሱ ሁኔታውን በማስረዳት፣ ችግሩን ለመቅረፍና ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ እንድታስጨብጡልን እንወዳለን፤›› በማለት አቶ ሲሳይ ለጎብኚዎች አስረድተዋል፡፡

ብዙዎቹ መንገዶች በከፊል አስፓልት ለብሰው በከፊል ሳይሠሩ ተቆፍረው ይታያሉ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ከፈረንሳይ-ጉራራ-ኮተቤ-ኪዳነ ምሕረት-ፈረንሳይ አቦ እየተገነባ ያለው መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በእስራኤሉ ትድሀር ኮንስትራክሽን ኩባንያ እየተገነባ ነበር፡፡ ርዝመቱም ሰባት ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ስፋቱ ደግሞ አሥር ሜትር ነው፡፡ ይህ መንገድ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸውን አካባቢዎች አቋርጦ የሚያልፍ በመሆኑ የከተማዋን የመንገድ መጨናነቅ ችግር እንዲፈታ ታስቦ ነበር ግንባታ የተጀመረው፡፡ ለዚህ መንገድ ግንባታ መጓተት ምክንያቱ ምን እንደሆነ የዛሬ ስድስት ወር በተጎበኘበት ወቅት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ሥጦታው በቦታው ተገኝተው ተናግረው ነበር፡፡ ከፍተኛ የወሰን ማስከበር ችግር እንደሆነና ይህንንም ለመቅረፍ ትምህርት በመውሰድ፣ ከዚህ በኋላ የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች 80 በመቶ የወሰን ማስከበር ሥራ ተጠናቆ ነው የሚጀመረው ብለው ነበር፡፡ ዛሬም ይህ መንገድ በየመሀሉ በአስፓልት ተሠርቶ ግማሹ ተመርቆ ነው ሥራ የጀመረው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአሁኑ ጉብኝት ለመንገዶች ግንባታ መጓተት መሠረታዊ ችግር እየሆነ ያለው ከፍተኛ የሆነ የወሰን ማስከበር ችግር መሆኑ በአቶ ሲሳይ ተገልጿል፡፡ ‹‹ከእኛ አቅም በላይ በመሆኑ ከንቲባውና ምክትል ከንቲባው የቀን ተቀን ሥራቸው እየሆነ ነው፡፡ በተለይ ምክትል ከንቲባው በየክፍለ ከተማው እየወረዱ ማስጠንቀቂያም ማሳሰቢያም ቢሰጡም ዛሬም ያልተፈታ ችግር ነው፡፡ ከዚህ በፊት 80 በመቶ የወሰን ማስከበር ሥራ ተሠርቶ ለኮንትራክተር ይሰጣል ብለን የጀመርነው ምንም እንደማይሠራ ነው ያየነው፤›› በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡

ይህ የወሰን ማስከበር ሥራ በወቅቱ ባለመከናወኑ የሚያመጣው ጉዳት ደግሞ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ ተጠቂው ኅብረተሰቡ ነው፡፡ ይህም መንገድ በወቅቱና በጥራት ተጠናቆ ወደ ሥራ ባለመግባቱ ኅብረተሰቡ ችግር ውስጥ ይወድቃል፡፡ ሌላው መንግሥት ከሚመድበው በጀት በላይ የወሰን ማስከበሩ በትክክል ባለመከናወኑ ከፍተኛ ለሆነ ለዋጋ ንረት ይጋለጣል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በኮንትራክተር ላይ የሚያመጣው ችግር ነው፡፡ በተለይ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቶች በተጓተቱ ቁጥር የገንዘብ አቅማቸው ስለሚዳከም ከጨዋታ ውጪ ይሆናሉ ማለት ነው፤›› ሲሉ የችግሩን መጠን አቶ ሲሳይ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ግንባታ መጓተትና መዘግየት 80 በመቶ የሚሆነው ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ችግር መሆኑን፣ ይህ ደግሞ ከከተማው በላይ የአገር ሀብትን በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ እያከሰረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የአሁኑ ጉብኝት አንዱ አካል እንደሆነ፣ በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የሕዝብ አደረጃጀቶች ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲሰጡ ጠይቀው፣ ‹‹ሌላው በተደጋጋሚ ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩ ይቃለልልናል ብለን እናስባለን፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በዚህ ዓመት ስድስት ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን፣ እስካሁን 75 በመቶ በመጠቀም ካለፈው ዓመት የተንከባለሉትን ሥራዎችን ጨምሮ እየሠራበት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ደግሞ 60 ኪሎ ሜትር የተለያዩ መንገዶች ሠርቶ እንዳጠናቀቀም አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...