Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት አድርገው የፓርላማውን ነፃነት ያግዛሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት አድርገው የፓርላማውን ነፃነት ያግዛሉ

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲሱ የአገራችን መሪ ከመሆናቸው ልክ ከአንድ ዓመት በፊት መጋቢት 2009 ዓ.ም. ላይ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የተባለ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ድንብ የተቋቋመና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ተቋም ባቀረበው የጥናት ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ የተካሄደና በቴሌቪዥንም ለሕዝብ የቀረበ፣ ሌሎች ውይይቶችንም ያስከተለ ውይይት፣ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ራሱን የቻለ ዜናና ወሬ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ ጥናትና ውይይት ውስጥ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ሥራ አስፈጻሚው በተግባራዊ እንቅስቃሴው በምክር ቤቶች ሥር አለመሆኑ፣ በግልጽም ይሁን በሥውር እጅ መሥራቱ፣ ሕግ ለመተላለፍ ለዛቻና ለጣልቃ ገብነት ባይተዋር አለመሆኑ፣ እንዲያውም ያልፈልጋቸውን የምክር ቤት አባላት ሕዝብን በመጠቀም ጭምር ውክልናቸውን እስከማንሳት ሲሄድ መታየቱ፣ ምክር ቤቶች የመቆጣጠርና የመጠየቅ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ተነገረ፡፡ ሥራ አስፈጻሚው የሥልጣን አፈጻጸሙ ገደብ አጥቷል የሚል መደምደሚያ እስከ መስጠት ሁሉ ሲደረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አየን፡፡ ሩብ ምዕት ዓመቱ ሙሉ ፊት ለፊት ሲታይ፣ ሲሠራ የቆየ አድራጊ ፈጣሪነትና ተራ እውነት ይመሥገነውና በ26ኛው ዓመት ላይ ሊታመን በቃ ብለን እኛም በዚህች አገር የማያልቅ ግርምት ተገረምን፡፡

ይህ ሁሉ ግርምትና ድፍረት፣ ከሞላ ጎደል ደግሞ ‹‹እውነት መናገር›› ብዙ አልዘለቀም፡፡ ጉድ የአንድ ሰሞን ነው ሆኖ አረፈው፡፡ መጋቢት አጋማሽ ላይ የአገር መነጋገሪያ ሆኖ ብቅ ያለው፣ አስፈጻሚውን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ አኳኋን ‹‹ያብጠለጠለው››፣ በአስፈጻሚው ውስጥ ያሉ፣ የአስፈጻሚው የራሱ አፍና እጅ የሆኑ ሁሉ አፍ ማሟሻ የሆነው ይህ ሪፖርትና ውይይት ግን ሚያዝያ ወር ላይ ድንገት ‹‹ተመታ›› እና ኩምሽሽ ብሎ ወደ ነበረበት ቦታ ተመለሰ፡፡

- Advertisement -

ሪፖርቱ ከቀረበ፣ ውይይቱ ከተካሄደና ከተቀጣጠለ በኋላ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢትዮጵያ ሚዲያ ጋር ፊት ለፊ በተገናኙበት በመጀመርያው አጋጣሚ ስለዚህ ጉዳይ ተጠየቁ፡፡ ጥናቱን መንግሥት አያውቀውም፡፡ ሁለተኛው ጥልቅ ተሃድሶ የጀመረው በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ ጥናት አለ ወይ ብለው ጠየቁ፡፡

ይልቁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ኢሕአዴግ ያንዣበቡበትን ብዥታዎች አጥርቶ ወደ ጤንነት መመለሱን›› (ሪፖርተር ሚያዝያ 15 ቀን 2009 ዓ.ም.) አስታወቁ፡፡ ፓርላማውም ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ክንፍ ከሚላቸው አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ‹‹የአስፈጻሚው ተፅዕኖ የለብኝም›› አለ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ከመስከረም 28 ቀን 209 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ወራት የመጀመርያው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ፀንቶ በቆየበት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚው ‹‹ሂድ ዞር በል መባል አለበት››፣ ‹‹ሃይ የሚለው አጥቷል›› የተባለበት፣ ገዥው ፓርቲ ለገዛ ራሱ ግምገማ እንዲታመን የተጠየቀበት የፖሊሲ ጥናትና ምርመር ማዕከል መድረክ በመጋቢት 2009 ዓ.ም. የአገር ወሬ በሆነ ልክ በዓመቱና በዚያው ሳንምት ውስጥ፣ ኢሕአዴግ አዲስ ሊቀመንበርና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹የማፈላለግ›› የመምረጥ ሕዝብ ጭምር ያሳሰበና ያስጨነቀ ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ሒደት ውስጥ ነበር፡፡ የሚገርመው የአስፈጻሚ ሥልጣን ገደብ የለሽ፣ ልጓም አልባ ሆኗል ያለውን ፓርላማው የአስፈጻሚው ተፅዕኖ የለበትም ብሎ የተከራከረውን፣ ከዚያም በኋላ የመፍትሔው አካል ለመሆን የአስፈጻሚውን አካል ዋነኛ ሥልጣን በገዛ ፈቃዱ መልቀቁን ያስታወቀውን፣ የትኛውን ከየትኛው ለያይቶ ዛሬም የትኛውን ‹‹ግራ›› የለውጥ ኃይል የትኛውን ‹‹ቀኝ›› ላለው ሁኔታ ተጋዳይ፣ የየትኛውን ተራማጅ፣ የቱን አድሃሪ ማለት እስኪያስቸግር ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁንም ገና ለይቶለት አላየንም፡፡

ሥራ አስፈጻሚው ገደብ አጥቷል ማለት ትርጉሙና ዝርዝሩ ወሳኝ ነው፡፡ የአገር ሕመም ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላት (በየትኛውም ደረጃ ያሉ) እንዲያፀድቁ የቀረበላቸውን ከማፅደቅና አስቀድሞ ውጤቱ ለታወቀ ውሳኔ እጅ ከማውጣት ያልወጣ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝብና ለህሊናቸው ከመታመን ይልቅ ለፓርቲ የሚታመኑ ናቸው፡፡ ይህንንም አፍጥጦና ሥራዬ ብሎ የሚቆጣጠርና የሚያንጓልል፣ በጥቅም የሚደልል የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጠናን አለ፡፡ ሕዝብ በነፃ ፍላጎቱ ሰይሟቸው፣ ጠይቋቸው፣ አውርዷቸው አያውቅም፡፡ ሥራ አስፈጻሚ በምክር ቤት አማካይነትም ሆነ በሌላ ሕጋዊ መንገድ የሕዝብ ተቆጣጣሪነትና ጠያቂነት የለበትም፡፡ ሕዝብ በልምምጥ አቤቱታ ከማቅረብ አልፎ በተቆጣ ጊዜ፣ አማራጩ ወይ በሆነ ማሻሻያ ነገር ተደልሎና ተደቁሶ መኮራመት፣ ወይም የነበረውን መንግሥት እስከ ማፍረስ መሄድ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሌላ አባባል ሕዝቡ በተወካዮቹ ላይም ሆነ በሥራ አስፈጻሚው ላይ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተቀመጡት ጎዳናዎች ተፅዕኖ እያደረገ ባለመሆኑ፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው ማለት (የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ ሪፐብሊክነት) ከወግ ያለፈ አልሆነም፡፡

ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ናት ማለት ሕዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር ተገናኝቷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮችም አስፈጻሚውን መግራትና መቆጣጠር ችለዋል ማለት ነው፡፡

ዓብይ በርካታ የለውጥ አቅጣጫዎችን ያመላከቱ፣ ከሞላ ጎደል መላውን አሊያም የአብዛኛውን ሕዝብ ተስፋና ድጋፍ ያሰባሰቡ አዲስ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ሥራ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ወይም ይህን መንገድ እንደሚከተሉ አስተዋውቀዋል፡፡ የገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በዚህም አጠቃላይ የተቋማት ግንባታ ተግባር ውስጥ በሕገ መንግሥቱ ‹‹የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው›› የተባለው ተቋም ላይ ሀ ተብሎ የተጀመረው የተግባር ማሻሻያ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ማሻሻያ መጀመርያ ያስተዋወቁት ለካቢኔያቸው የመጀመርያውን የሥራ መመርያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡ በዚያ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ይህንን ፓርላማውን የሚመከለከት ጉዳይ እንዳለ ከዚህ ቀጥሎ የማቀርበው ከዋናው ጉዳይ በተጨማሪ፣ ከዚያ እኩል እዚህ ጽሑፍ ውስጥ መልሰን መላልሰን የምናነሳውን የሚዲያም ጉዳይ ያስረዳልኛል ብዬ ስለማምን ጭምር ነው፡፡

እንዲህ ይላል፣ ‹‹መስከረም ላይ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሊቃነመናብርት ከእያንዳንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር አንድ ገጽ ሁለት ገጽ ፎርማል ኮንትራት ይፈራረማሉ፡፡ ኮንትራቱ ይኼ ሚኒስትሪ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ . . . ስድስት ነገር በሚቀጥለው ሰኔ መጨረሻ ላይ ዴሊቨር ያደርጋል ብሎ ኮንትራት ይገባል፡፡ ኦፊሺያል ዌብሳት ላይ ይለቀቃል፡፡ ያ ልክ የቋሚ ኮሚቴ ያን ሚኒስትሪ ሲገመግም ላይቭ ጥያቄዎች ከሕዝብ እንቀበላለን፡፡ ተደርጓል? አልተደረገም? ዴሊቨር የማያደርግ ሰው በፍፁም አይቆይም፡፡ ይህን ሁላችሁም ማወቅ አለባችሁ፡፡ በዴሊቨር ብቻ ነው ሰርቫይቭ የምናደርገው፡፡ እንደ ጋራም እንደ ግልም፡፡ የገቡትን ኮንትራት በዓመት ውስጥ ሁለት ሥራዎች እንሠራለን፡፡ አንደኛ ፓርላማ ማለት የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ኮንትራት የሚያስፈጽም ትልቅ ኢንስቲትውሽን መሆኑን እናሳያለን፡፡ ሕዝቡ ፓርላማን ያከብረዋል፡፡ ሁለተኛ በገባው ቃል መሠረት አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ዴሊቨር የማያደርግ ሰው ካለ፣ በማግሥቱ ማስተካከያ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ ተጠያቂነት ያለበት መንግሥት መሆኑን እናረጋግጣለን ማለት ነው፡፡ ይኼ ለሕዝብ ክፍት ሲሆን አንደኛ ሰው ይሠራል፡፡ ሁለተኛ ሕዝብ መንግሥት ላይ ያጣውን ኮንፊደንስ እየገነባ ይሄዳል፡፡ ይኼ አንዱ ፕላን ላይ simple የሚሆነው እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ ፎርማል ግልጽ የሆነ ኮንትራት ይይዛል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት አካባቢ ግን በደንብ ሳንለማመድ በመንግሥት ነው የምናደርገው፡፡ ሁሉም ካቢኔ ተቀምጦ፣ ሁሉም ቋሚ ኮሚቴ ተቀምጦ ኮንትራቱን ላይቭ ሕዝቡ ጥያቄ እየጠየቀ (ቀላል ነው እሱ ሶሻል ሚዲያ ስላለ) ማን ይሠራል? ማን አይሠራም? ሕዝቡ ራሱ ይፈርዳል ማለት ነው፡፡ አንዳንዱ እየለፋ አንዳንዱ እየተኛ ዓይነት ጨዋታ የሚቀርበት መንገድ በፕላኒንጋችን እንፈጥራለን ማለት ነው፤›› ይላል፡፡

በዚህ ዕቅድና ውሳኔ መሠረት ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ጋር የ2011 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ውል ተፈራረመ ማለትን ውሎ አድሮ ሰማን፡፡ ውሎ አድሮ የሰማነው በተለይም ዝርዝሩን ነው፡፡ ፓርላማው ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. እረፍት ወጥቶ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው፣ ምሕረት ለመስጠት የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ለማፅደደቅ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተጠራው ፓርላማ ነው በቋሚ ኮሚቴዎቹ ሊቃነ መናብርት አማካይነት ከየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር የ2011 የበጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ውል የተፈራረመው፡፡ ኢቲቪ ራሱ መረጃውን ያደረሰን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው›› ብሎ ነው፡፡ በሰማነው ዜና መሠረት የፊርማው ሥነ ሥርዓት የተካሄደው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ በተጨማሪም በዚህ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ መገኘታቸውን፣ እሳቸውም ለምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ አስፈጻሚውን አካል መከታተልና መቆጣጠር መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ የሥራ ዕቅድ ውል ስምምነትም የምክር ቤቱን ሥራ ይበልጥ ውጤታማና የተጠናከረ ያደርገዋል ማለታቸውን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ንግግር ማድረጋቸውን ተነግሮናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የተወካዮች ምክር ቤት የእኛ አለቃ ነው፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የእኛ አለቃ መሆኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን የቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበሮችን ኑሮ በማስተካከል ይጀምራል፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አጠቃላይ ስታንዳርድ በሚኒስትር ስታንዳርድ ሆኖ ይስተካከላል፡፡ ከመስከረም ጀምሮ፡፡ የተለመደው የሱፐርቪዥን አሠራር በሕግ የተቀመጠና ሥራችሁ ቢሆንም በቂ ስላልሆነ ሰደን ሱፐርቪዥን ማድረግ መጀመር አለባችሁ፡፡ ለማንም ሳትናገሩ በድንገት በየሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ እየሄዳችሁ ከሚኒስትር ጀምሮ እስከ ተራ ሠራተኛ ቢሮ ክፍት መሆኑንና አገልጋይ መሆኑን ማረጋገጥ አለባችሁ፡፡ ሕዝብ የወከላቸሁና የሕዝብ ሀብት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ያለበት የምክር ቤት/የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ፣ ይህንን ተግባር በሙሉ አቅሙ እንዲፈጽም በእኛ በኩል በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ አቅሙ እንዲሠራ አስፈላጊው ድጋፍ በአስፈጻሚው የሚደረግና ከእነሱ የሚሰጠንን አቅጣጫና ምክር ሐሳብ ተቀብለን የምንፈጽም መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እየገለጽኩ፣ ሚኒስትሮች ወደ ፓርላማ ስትሄዱ የሠራችሁትን ለማቅረብና የተሰጣችሁንን ትዕዛዝ ለመቀበል ጭምር መሆኑን ከወዲሁ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፤›› እንዲሁም፣ ‹‹አሁን የተፈራረምነው ፊርማ እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ በሚቻለው የሚዲያ አውታር ሁሉ ለሕዝብ ማሳወቅና እያንዳንዱን ተቋም ሲገመገም ለሕዝብ በቀጥታ አሁን ባለው ቴክኖሎጂ አማካይነት ጥያቄዎችን እያቀረበ የሕዝብ ጥያቄ ተብሎ ሳይሆን የሕዝብ ጥያቄ በላይቭ ሰክሪን መታየት አለበት፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ ብለዋል፡፡ ጥሩ ጀምረዋል፡፡ ጥሩም የሕዝብ ፍቅር አላቸው፡፡ በጎ ፈቃዳቸውም ምኞታቸውም ጥሩ ነው፡፡  

የተቋም ምሥረታ ጉዳይ ግን ከበጎ ፈቃድና ከመሪዎቻችን ምኞትና ቁርጠኝነት ውጭ መኖር አለበት፡፡ አገራችንን ያጎደለው ይኼው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዚህ ረገድ እንደሚባለው ‹‹እንከን የለሽ›› ባይባልም ብዙ የሚጎድለው ነገር የለውም፡፡ የሚጎድለውን ነገር ነቅሰን ጎልጉለን እንድናወጣና በሒደትም እንድናሟላ ያደረገን፣ ሰዎች በተለይም ባለሥልጣናት ከፈለጉ ከሕግ በላይ መሆን ስለሚችሉ፣ ከሕግ በላይ መሆንን የሚከለክል ፍጥርጥር ስለሌለን ነው፡፡

በዚህ ረገድ ያለብንን ችግር ለማሳየት ለመግቢያ ያህል በስፋት በተጠቀሱት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ንግግሮች ውስጥ በግልጽ፣ በስፋትና በተለየ ሁኔታ የተጠቀሰውን የሚዲያ ሚናና ቦታ እንመልከት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና በመጀመርያው የፓርላማ ሪፖርታቸው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በመለሱበት ጊዜ፣ በአጭር አስተያየት የመንግሥታቸውን የሚዲያ ፖሊሲ አስረግጠው የተናገሩ ይመስለኛል፡፡ ጥያቄው የቀረበበት (ማለትም የግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽንና የኤርትራ) ጉዳይ ‹‹በሚዲያ መገለጹም አንደ ትችት (ኮሜንት) ስሚነሳ›› ብለው የተናገሩት የመንግሥታቸው/የፓርቲያቸውን አቋም ጭምር ይመስኛል፡፡ ‹‹የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ በየሰዓቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጽ አለበት፡፡ የድብቅ ፖለቲካ ከእንግዲህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አይሠራም፡፡ ለምን? ያ ሥራ አስፈጻሚው ነው መንግሥት የሚመራው፡፡ እኛ ለሕዝብ ስንናገር ሕዝብ የሚናገረውን ለመስማት ጭምር ነው የምንጠቀምበት እንጂ ለማገድ አይደለም፡፡ ‹‹በመደበቅና ሸርበን፣ እኛ አብስለን፣ የበሰለ ኬክ የምናቀርብበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የለም ግርድፍ ይቀርባል፡፡ እንወያያለን፡፡ አብረን እናበስለዋለን፡፡ ካልሆነ ሕዝብ ይወስናል፡፡ ምን ችግር አለው? የእኔ ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ከድርጅቴ ጋር ማስፈጸም ብቻ ነው፡፡ ድበቃ አይጠቅምም፡፡ ይህን ሐሳብ መተው ጥሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ዓብይ ይህ ያህል ስለሚዲያ እያወሩ ከእንግዲህ ወዲያ ድብቅ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ አይሠራም አሉ እያልን፣ እስከ ዛሬ ድረስ አንድም ቀን ሚዲያውን አለማስቀረባቸው፣ ሚዲያውን አለማስከተላቸው፣ አንድም ቀን የፕሬስ ኮንፈረንስ አደረጉ ሲባል አለማየታችን የሚከነክነው የሚዲያ ባለሙያተኞን ብቻ አይደለም፡፡ ሁላችንንም ነው፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች (ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ አርቲስትቶች፣ መምህራን፣ ወዘተ) ሕመምህ ምንድነው? ሲባሉ ሚዲያው ለምን እንዲያ አልተባለም ብዬ ለመጠየቅ አልቀናጣም ይሆናል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ሚዲያው ሊገለል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአስፈጻሚው አካል ጋር የ2011 የበጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ውል ሲፈራረም ያ ክንውን ከሚዲያ ዕይታ ውጪ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚያን ቀን ‹‹የሥራ መመርያ›› በዝግ ስብሰባ ተካሄደ ሲባል ግን አሠራሩ ከፖሊሲ፣ ከመርህ፣ ከሕገ መንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን ከምንጠቅሰው ከእሳቸው ንግግር ጋር ያጋጭብናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተወካዮች ምክር ቤት የእኛ አለቃ ነው ወዳሉት የፓርላማ ጉዳይ እንመለስ፡፡ እውነት ነው፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥቱ በተለያዩ ቦታዎች ደጋግሞ ይለዋል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይም ይህንን ይላሉ፡፡ ከልብም ያምናሉ ብዬ መወራረድና ዕዳ መግባት ድረስ እሄዳለሁ፡፡ ለዚህም የተወካዮች ምክር ቤት የእኛ አለቃ መሆኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን የቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበሮች ኑሮ በማስተካከል ይጀምራል፡፡ ከመስከረም ጀምሮ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አጠቃላይ ስታንዳርድ በሚኒስትር ደረጃ ሆኖ ይስተካከላል ብለዋል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ጥሩነቱ ግን አስፈጻሚው ጥሩ እስከሆነ ድረስ ብቻ የሚቆይ ነው፡፡ ይበልጥ ጥሩ የሚሆነው የአስፈጻሚውን መልካምና በጎ ፈቃድ በማብዛት ሳይሆን፣ በልምድና በሥልጣን ስስት ምክንያት ሥራ አስፈጻሚው በፓርላማው ብቻ ሳይሆን፣ በመላው አገሪቱ የሠራ አካላት ውስጥ እንደ ሰርዶ ተሠረጫጭቶ፣ እንደ ሥርና ጅማት ተቀጣጥሎ የተንሠራፋውን የበላይነት በመቆራረጥ ነው፡፡

ፓርላማውን ብቻ ሳይሆን የበርካታ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ነፃነት ለማረጋገጥ ሲባል ለምሳሌ ፍርድ ቤቶች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ዋናው ኦዲተር፣ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን የየራሳቸውን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ራሳቸው አዘጋጅተው በቀጥታ ያስፈቅዳሉ፡፡ የምክር ቤቱ በጀት በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 214 መሠረት በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ተዘጋጅቶ ለአፈ ጉባዔው ቀርቦ፣ በአፈ ጉባዔው ኣማካይነት እንዲመረመር ለበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ፣ ቋሚ ኮሚቴውም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በመመካከር ተመርምሮ በምክር ቤቱ ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ቀርቦ፣  ለምክር ቤቱ ቀርቦ የሚወስን ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ያለው ተፅዕኖ የምክር ቤቱን የሥልጣን አካላትና አባላት ጥንካሬ ያህል የታወቀ ነው፡፡

በሕግ የተደነገገው የበጀት ነፃነት አለው ቢባል እንኳን የተመደበው በጀት የመግዛት አቅም በሠራተኛው ደመወዝ፣ አበል፣ በሚገዛው ዕቃ ዓይነት፣ የዕቃ አገዛዝ ሥነ ሥርዓት ላይ ሁሉ የተንጠለጠለ ነው፡፡ አብዛኛው የዚህ ወሳኝ ደግሞ ሥራ አስፈጻሚው ነው፡፡

ዶ/ር ዓብይ የቋሚ ኮሚቴ ሊቃነመናብርት ስታንዳርድ በሚኒስትር ስታንዳርድ ሆኖ ይስተካከላል ሲሉ የነገሩን፣ ይህንን የመሰለውን የአስፈጻሚውን አካል የቅርብና የሩቅ መቆጣጠሪ ክርና ቁጥጥር አንዱን ገጽታ ብቻ ነው፡፡

በተለይም በሠራተኛ አስተዳደር ረገድ የተወካዮች ምክር ቤት ዕድሜ ልኩን ከዚህ ቀንበር መውጣት እንዳልቻለው ሁሉ፣ የዳኝነት አካሉ በሲቪል ሰርቪስ ሕግ ሥር ነው፡፡ ምክር ቤቱ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ሠራተኞች ይኖሩታል ተብሎ ከተደነገገበት ከመጀመርያው ይህን የሚመለከተው የ1988 ሕግ ጀምሮ ዛሬም ድረስ (አዋጅ ቁጥር 906/2007) የጽሕፈት ቤቱ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሠረት የሚቀጠሩና የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ ሕግ ውጪ የሆኑት የጽሕፈት ቤቱ ዋና ጸሐፊ፣ ምክትል ዋና ጸሐፊና የመምርያ ኃላፊዎች ብቻ ናቸው፡፡ እንዲህ ባሉ የተለያዩ ሰንሰለቶች የተቆራኘ አካል አይዞህ ነፃ ነህ ስላሉት ብቻ ነፃ አይሆንም፡፡ አስፈጻሚው ሕገ መንግሥቱ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል በሚለው ተቋም ላይ አውቆም ሳያውቅም የተከለውን መርዝና አሜኬላ በዝርዝር አውቆና ለይቶ መንቀል ካልተቻለ በቀር፣ ነፃ ነህ ማለት ብቻ ለነፃ ተቋም ግንባታ ፋይዳ ያለው ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡ ይህ ግዙፍ ተግባር ዶ/ር ዓብይን ከመሰለ ፈቃደኛና ቁርጠኛ መሪ በተጨማሪ፣ በተቋሙ ውስጥ ነፃ መውጣት የፈቀደ፣ ነፃ መውጣት ውስጥ ጥቅም ያላቸው ባለሙያዎችንና ኤክስፐርቶችን ይሻል፡፡              

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...