Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትቀጣይዋ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ከሩሲያ ምን ተማረች?

ቀጣይዋ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ከሩሲያ ምን ተማረች?

ቀን:

‹‹ራሲያ ራሲያ ራሲያ›› ከየአገሮቹ የተሰባሰቡ የዓለም ዋንጫ ታዳሚዎች የሩሲያ ስም እየጠሩ ያመሠገኑበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በስታዲየሞቹ የሩሲያ ስም ሲጠራ የሁሉም ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ማበረታቻ ድምፅ ሆኖ ከርሟል፡፡ አንድም ብሔራዊ ቡድናቸው ሲመራ ወይም ግብ ሲያስቆጥር ‹‹ራሲያ›› ማዳመቂያ ቃል ነበረች፡፡ ለዚህ ሁሉ መገለጫ ሊሆኑ የቻሉት ደግሞ ዓለም ዋንጫውን ከምንጊዜም በላይ ደማቅ ማድረግ መቻላቸው ነው፡፡ በጨዋታዎች ያልተጠበቁ ውጤቶች ከመመዝገብ ባሻገር፣ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ድግስ አነጋጋሪ ነበር፡፡

21ኛውን የፊፋ ዓለም ዋንጫ በስኬት ያስተናገደችው፣ ሩሲያ ቀጣዩን የቤት ሥራ ለተረከበችው ኳታር ኃላፊነቱን አስረክባለች፡፡ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለኳታሩ ገዥ አብዱል ቢን ናሲር ቢን ካሊፋ አልታሀኒ የ2022 ዓለም ዋንጫ ግዴታ እንዲወጡ አስረክበዋል፡፡ ሩሲያ በዓለም ዋንጫው ያሳየችው መሰናዶ፣ ለኳታር ከፍተኛ ራስ ምታት የሆነባት ይመስላል፡፡ ሁለቱ አገሮች በነዳጅ ሀብታቸው የታወቁ ቢሆንም በመልክዓ ምድራቸው ግን የሰማይና የምድር ርቀት ያህል ናቸው፡፡

የሩሲያውን ዓለም ዋንጫ መሰናዶ ተከትሎ የኳታር ልዑካን ቡድን ሞስኮ ላይ ከትሞ ነበር፡፡ በከተማዋ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ የሰፈረው ልዑካን ቡድኑ የኳታርን የተለያዩ ባህላዊ ትውፊቶች፣ ሙዚቃ፣ የስታዲየም ግንባታዎችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለኅብረተሰቡ ሲያስተዋውቅ ሰንብቷል፡፡ በዚህም የዓረቡ ዓለም ገጽታና መሰናዶውም ምን ይመስላል? የሚለውን ለተመልካች ሲያስጎበኝ ነበር፡፡

ሁሉም አገሮች ከራሳቸው የፖለቲካ አመለካከትና ተሳትፎ አንፃር ከተለያዩ ኃያል አገሮች ጋር ሲጋጩና ማዕቀብ ሲጣልባቸው ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም በአገሮች ተቀባይነት እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ስፖርታዊ ዝግጅቶችን በማሰናዳት የአገራቸውን ገጽታን ሲገነቡ ይስተዋላል፡፡ ሩሲያም ይኼን አጋጣሚ በአግባቡ የተጠቀመችበት ይመስላል፡፡

በሩሲያ ከተሞች የተሰናዳውን ኳታርን የሚያስተዋውቀው ዐውደ ርዕይ የተለያዩ አገሮች ደጋፊዎች፣ ቱሪስቶች ተጎብኝተዋል፡፡ የፊፋን ዋና ጸሐፊ ሴኔጋላዊቷ ፋትማ ሳምባን ጨምሮ የተለያዩ አንጋፋ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጨዋቾች፣ አሠልጣኞች እንዲሁም ባለሥልጣናት በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡

‹‹የፊፋ ዓለም ዋንጫ ቤተሰብን በኳታርም በደስታ ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ ለዚህም ኳታር ከወዲሁ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው፤›› በማለት የፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋትማ በጉብኝታቸው ወቅት አስረድተዋል፡፡

በዐውደ ርዕዩ ስለስታዲየሞች ግንባታ፣ ስለትራንስፖርትና ተመልካቾች እንዴት ወደ ከተማው መትመም እንዳለባቸው ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ፋትማ አልኑሚ የዝግጅቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከሩሲያው ዓለም ዋንጫ ጎን ለጎን ኳታርን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በዐውደ ርዕዩ የኳታርን መሰናዶ ምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንዳለና የኳታርን ባህል ከወዲሁ እንዲያውቁ የሚረዳ ዝግጅት አቅርበናል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

 በሩሲያው ዓለም ዋንጫ ከውድድሩ ባሻገር የዓለም ሕዝብ ስለሩሲያ የነበረውን አሉታዊ አመለካከት እንዲቀይር ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ኳታር ለመጀመርያ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚሰናዳውን ዓለም ዋንጫ ላይ በአኅጉሩ ላይ የሚታየውን አሉታዊ አመለካከት ለመቀየር እንደታቀደ በዐውደ ርዕዩ ተገልጿል፡፡

‹‹የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በሚዲያውም እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ ሥጋት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሩሲያ ግን ያን ጥርጣሬና ፍርኃት መቀየር ችላለች፡፡ እኛም የዓለም ኅብረተሰብ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያለውን አመለካከት እንዲቀየር ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን፤›› በማለት ፋትማ አክለዋል፡፡

የዓለም ዋንጫን የማዘጋጀት ዕድል ያገኘችው ኳታር ምንም እንኳ የተለያዩ ችግሮች ቢቀርቡባትም መሰናዶዋን ግን ቀጥላለች፡፡ ኳታር ከዚህ ቀደም ከገነባቻቸው አምስት ስታዲየሞች በተጨማሪ፣ አራት አዳዲስ ግንባታዎች እያካሄደች ትገኛለች፡፡ ሁሉም ስታዲየሞች በ2021 ይጠናቀቃሉ ተብሏል፡፡ ምዕራብ እስያ የምትገኘው ኳታር 11,581 ስኴር ካሬ ሜትር የቆዳ ስፋት ላይ በመኖሯ ከተሞቿ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከስታዲየሞች ስታዲየሞች ለመጓዝ የአምስት ደቂቃ ዕድሜ ይወስዳል፡፡ ረዥም ርቀት የሚወስደው  ሁለት ሰዓት ሲሆን፣ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

የስታዲየሞቹ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘት ተመልካቹ እንደፍላጎቱ ተንቀሳቅሶ ጨዋታን እንዲመለከትና የውድድሩ ድግሶች ላይ በቀላሉ እንዲሳተፍ ያስችለዋል ተብሏል፡፡

በአሸዋማ መሬት ላይ የተቀመጠችው ኳታር ሙቀቷ ከፍተኛ ነው፡፡ በበጋው ወቅት እስከ 45 ዲግሪ ሲልሼስ ይደርሳል፡፡ ዓለም ዋንጫን ለማሰናዳት ዕድሉ ሲሰጣትም ይኼ ጉዳይ አነጋጋሪ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ኳታር ግን ለስታዲየሞች የረቀቀ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ማቀዷን አስታውቃለች፡፡ በዚህም መሠረት በጨዋታ ወቅት ስታዲየሙን የውስጥ አካል 19 ዲግሪ ሲልሼይስ ድረስ የሙቀት መጠኑን ለማውረድ፣ ከስታዲየም ውጪም ቢሆን ተመልካቾቹ በከተማዎቹ ሲዘዋወሩ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለማቀዝቀዝ እንደሚጥሩ ተገልጿል፡፡ ፊፋም የውድድሩን ጊዜ በማሻሻል ከኅዳር 12 ቀን እስከ ታኅሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. (ከኖቬምበር 21 እስከ ዲሴምበር 18 2022) ላይ ማድረጉን የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተናግረዋል፡፡ ይኼም የኳታሮችን የአየር ፀባይ የተሻለ ወቅት ላይ እንዲሆን ይረዳዋል፡፡

ከስታዲየሞቹ ባሻገር የትራንስፖርት ግንባታዎች እንዲህ በከተማው ውስጥ እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ ሪፖርተር በአዘጋጇ ከተማ ተገኝቶ መታዘብ እንደቻለው አዳዲስ የከተማ መንገዶች፣ የከተማ ቀላል ባቡሮችና አየር ማረፊያዎች ላይ ከፍተኛ ግንባታ ላይ መሆናቸውን ተገንዝቧል፡፡ በ2022 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተመልካች ሊገኝ እንደሚችል ያዘጋጁ አገር ኮሚቴ ግምቱን አስቀምጧል፡፡  

በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ኳታር 2,641,669 ነዋሪ ሲኖራት፣ ከ88.4 በመቶ የውጭ አገር ዜጎች ይኖሩባታል፡፡ 11 በመቶ ደግሞ ኳታራውያን ናቸው፡፡ ኳታር በስታዲየም ግንባታውና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የሚሠሩ የቀን ሠራተኞች በሚፈልሱ የውጭ አገር ዜጎች ላይ በደል እያደረሰች ነው የሚል ቅሬታ እየደረሰባት ይገኛል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኳታር ከግብፅ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ዮርዳኖስ ጋር ያላት ግንኙነት መላላቱን ተከትሎ፣ የተለያዩ ፍራፍሬና የአትክልት ምርት እጥረት ስላጋጠማት በዘጠኝ ወር ውስጥ በራሷ አቅም ችግሩን መፍታት መቻሏ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ቀድሞ የጎረቤት አገሮችን ደጅ ያስጠናት የነበረው የወተት ምርትንም በቅርቡ ከሆላንድ ላሞችን በመግዛት በራሷ አቅም ችግሩን መፍታት ችላለች ተብሏል፡፡

ከዚህ ዓለም ዋንጫ ውድድሩን በብቃት ከማዘጋጀት ባሻገር ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍታት እንደምትችል እየተነገረ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...