Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንኮች አጠቃላይ ሀብት ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር አደገ  

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግልና የመንግሥት ባንኮች ያስመዘገቡት አጠቃላይ የሀብት መጠን አንድ ትሪሊዮን ብር መድረሱ ተጠቆመ፡፡ የግል ባንኮች ብድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰጠው መብለጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥና የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪና የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባል አቶ ተክለ ወለድ አጥናፉ እንደገለጹት፣ አሥራ ስምንቱ የአገሪቱ የግልና የመንግሥት ባንኮች በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ያስመዘገቡት የሀብት መጠን አንድ ትሪሊዮን ብር ሊደርስ የቻለው በ2002 ዓ.ም. ከነበረበት 167 ቢሊዮን ብር ተነስቶ ነው፡፡

አቶ ተክለ ወልድ ይኼንን የገለጹት፣ ለእሳቸውና ለቀድሞው የባንኩ ምክትል ገዥና ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ላበረከቱት አገልግሎት በተዘጋጀው የሽኝትና የዕውቅና ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ሁለንተናዊ ዕድገትን በማስመዝገብ ውጤታማ እንደነበር የገለጹት አቶ ተክለ ወልድ፣ የባንኮቹ የሀብት መጠንና ሌሎች ስኬቶች እያደጉ የመጡትና የተጠቀሰው የሀብት ዕድገት ውጤት የተገኘው ከ2002 ዓ.ም. በኋላ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ብሔራዊ ባንክ በተገበራቸው ፖሊሲዎች አማካይነት ነው፡፡

የፋይናንስ ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከቱ ሳቢያ በተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ረገድ በ2002 ዓ.ም. 96 ቢሊዮን ብር አካባቢ የነበረው የአገሪቱ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን፣ በአሁኑ ወቅት ከ720 ቢሊዮን ብር በላይ ስለመድረሱ አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ የፋይናንስ ዘርፉ ከፍተኛ ዕድገት ስለማሳየቱ ሲያብራሩ፣ በ1998 ዓ.ም. ባንኮቹ የነበሩበትን ደረጃ አሁን ካለው ጋር በንፅፅር አስቀምጠዋል፡፡ የአገሪቱ ባንኮች በ1998 ዓ.ም. የነበሩበትን ደረጃ መነሻ በማድረግ አቶ አዲሱ እንደገለጹት፣ ሁሉም ባንኮች የነበራቸው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 15.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ግን የሁሉም የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 738 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በ1998 ዓ.ም. 15.1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ካሰባሰቡት የወቅቱ ባንኮች መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን ጨምሮ፣ አራት የግል ባንኮች እንደነበሩ አቶ አዲሱ አስታውሰዋል፡፡ በዚያን ወቅት ከተሰበሰበው 15.1 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 14 ቢሊዮን ብር ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች አሰባስበው ነበር፡፡ ቀሪውን አንድ ቢሊዮን ብር የግል ባንኮች እንደተጋሩት አቶ አዲሱ ገልጸው፣ አሁን 16 የግል ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 277 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የንግድ ባንክ ተቀማጭ ግን 451.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ1998 ዓ.ም. ስለአራቱ የግል ባንኮች ማለትም አዋሽ፣ አቢሲኒያ፣ ዳሸንና ወጋገን የሚጠቀሰው ሌላው ጉዳይ የሰጡት የብድር መጠን ነው፡፡ በወቅቱ 816 ሚሊዮን ብር ብቻ አበድረው ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. ግን ይህ መጠን ከ182 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡

ንግድ ባንክና የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከ12 ዓመታት በፊት በጥቅል ማቅረብ የቻሉት የብድር መጠን 8.8 ቢሊዮን  ብር ሲሆን፣ አሁን ግን ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ ማበደር እንደተቻለና ይህም የአገሪቱን የባንኮች የዕድገት ሒደት እንደሚያመላክት አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመት የሁሉም ባንኮች አጠቃላይ የብድር መጠን 361.8 ቢሊዮን ብር ያስመዘገበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የግል ባንኮች የሰጡት ብድር ከንግድ ባንክ አኳያ ብልጫውን እንደወሰዱበት ያሳያል፡፡  

ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ የግል ባንኮች ከሚሰጡት አንፃር ብልጫ ያለውን የብድር መጠን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲያቀርብ ቢቆይም፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን 16 የግል ባንኮች በጥቅሉ የሚሰጡት የብድር መጠን እያደገ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ንግድ ባንክ ለመብለጥ አስችሏቸዋል፡፡

አቶ አዲሱ የአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ያሳየውን እመርታ በተመለከተ በሰጡት ገለጻ፣ በ1998 ዓ.ም. ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች የነበራቸው የቅርንጫፎች ብዛት 187 ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ በዚሁ ወቅት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አራት የግል ባንኮች በበኩላቸው 29 ቅርንጫፎች ብቻ እንደነበሯቸውና ይህም በአገሪቱ የነበሩት የሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር 216 ብቻ እንደነበር ጠቋሚ ስለመሆኑ አስታውሰዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ግን የባንኮች ቅርንጫፎች ብዛት በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች 4,445 ቅርንጫፎች እንደከፈቱ አኃዞች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብዛት 1,288 ሲሆን፣ 16 የግል ባንኮችም 3,157 ቅርንጫፎችን እንደከፈቱ ታውቋል፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ሰፊ የሥራ ዕድል ስለመፈጠሩም አመላካች ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ1998 ዓ.ም. ሁሉም ባንኮች 6,966 ሠራተኞችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የመንግሥት ባንኮች 5,524 ሠራተኞች ሲኖሯቸው፣ የግል ባንኮች ግን 1,142 ሠራተኞችን በመያዝ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንኩ ዘርፍ ከ35 ሺሕ በላይ ሠራተኞች እያስተዳደረ ይገኛል፡፡

ይህ የ12 ዓመታት የባንኮች ታሪክ በየጊዜው ብዙ ለውጥ የታየበት መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ተጨማሪ ማሳያ የሚሆነው የተከፈለ ካፒታል ሲሆን፣ የሁለቱ የመንግሥት ባንኮች የወቅቱ ካፒታል 684 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ የግሎቹ 1.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ንግድ ባንክ ከአንድ ዓመት በፊት የነበረው የተከፈለ ካፒታል 13 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ዘንድሮ ወደ 40 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ የግል ባንኮች የተከፈለ ካፒታል መጠን ወደ 26.2 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡

የባንኮቹ ዕድገት ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ሽኝት ጋር በተወሳበት ወቅት፣ እንደ ባንኮች ማኅበር ሁሉ ብሔራዊ ባንክም የራሱን የቀድሞ ገዥዎች የምሥጋና ፕሮግራም በማዘጋጀት ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ወቅትም የቀድሞዎቹ የባንኩ ገዥዎች በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ያበረከቱት አስተዋፅኦ ተወድሷል፡፡

በፕሮግራሙ ወቅት ንግግር ያደረጉት አቶ ተክለ ወልድ፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ቢያድግም ከዚህ በኋላ የሚጠበቅበት ሥራ ከበፊቱ የበለጠ እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነቱ ከተስተጓጎለ የአገሪቱ ባንኮች እንደሚጎዱ ጠቁመው፣ ሁሉም በየፊናው የኢኮኖሚው ዕድገት እንዳይገታ ተረባርቦ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች