Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አበባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቡና የሚገኘውን ገቢ መተካት ይችላል››

አቶ ዓለም ወልደገሪማ፣ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

አቶ ዓለም ወልደገሪማ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ኤጀንሲን በዋና ዳይሬክተርነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ኤጀንሲው ሲቋቋም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቅርብ ክትትል እንደነበር ይነገርለታል፡፡ ከጅምሩም ብዙ የተባለለትና ብዙ ሲጠበቅበት የነበረ ዘርፍ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የአበባ ዘርፍ እንዳመጣጡ ግለትና ውበት አምሮበት መጓዝ እንዳቃተው የዘርፉ ተዋናዮች ይገልጻሉ፡፡ በየጊዜው እየተቀዛቀዘ በመምጣቱም በአሁኑ ጊዜ ዝምታውን የመረጠ ይመስላል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ቀስ በቀስ ከአበባ እርሻ በመውጣት ወደ አትክልትና ፍራፍሬ እርሻ እየገቡ ይገኛሉ፡፡ ከውጫዊ ምክንቶች ባሻገር በአገር ውስጥ ችግሮች ምክንያት አበባ ማነቆ እንደበዛበት ባለሀብቶች ይገልጻሉ፡፡ የመሬት አቅርቦት ችግር ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ አቅርቦቱም ብቻ ሳይሆን በመሬት አሰጣጥ ችግሮች፣ በካሳ ክፍያ፣ በፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ በቴክኒክ ድጋፍ ዕጦትና በመሳሰሉት ችግሮች መተብተቡን ይናገራሉ፡፡ አቶ ዓለም በበኩላቸው በአብዛኛው የዘርፉ ችግር የመሬት አቅርቦት መሆኑን ያምናሉ፡፡ በተለይ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የማስፋፊያ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያልተቻለው ክልሎች መሬት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው ይላሉ፡፡ ከመሬት ባሻገር ግን አበባ በአብዛኛው በአውሮፓ ገበያ ይበልጡን ደግሞ በኔዘርላንድስ ማዕከላዊ ገበያ በጨረታ ሲሸጥ፣ ግብይቱ በዩሮ መሆኑና ወደ አገር ውስጥ ገንዘቡ ሲመጣ ግን በዶላር የሚመዘር በመሆኑ በዶላርና በዩሮ መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት ጥቅምም ጉዳትም እያስከተለ ቆይቷል ያሉት አቶ ዓለም፣ በተለይ የምንዛሪ ለውጡ ቀድሞ ከነበረው የስድስት ብር ልዩነት (ዶላር ከዩሮ አኳያ) በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ብር ገደማ ዝቅ ማለቱ አበባ አምራቾችን ለጉዳት እየዳረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ አበባ አምራቾችና ላኪዎች በበኩላቸው በዩሮ እየሸጡና ጥሬ ዕቃም እየገዙ በዶላር ክፈሉ መባላቸው፣ ባንኮችም ሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚከተሉት ዶላርን መሠረት ያደረገ የምንዛሪ ግብይት ኪሳራ እየደረሰባቸው እንደመጣ ይገልጻሉ፡፡ በዚሁ ላይ የአውሮፓ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝም በአበባ ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አቶ ዓለምና ላኪዎችም ያምኑበታል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ኤጀንሲው አበባን በዘንግ ይላክበት ከነበረው አሠራር አውጥቶ በኪሎ ግራም እንዲሆን ማድረጉ ብዙ ትችት ሲያስነሳበት ቆይቷል፡፡ የአበባ ላኪዎችን ቢጠቅምም አገርን ግን በእጅጉ ጎድቷል ተብሎ በጣም ሲነቀፍ ነበር፡፡ ይሁንና አቶ ዓለም እንዲህ ያለውን ትችትና ሙግት ውድቅ የሚያደርጉት አገሪቱ በዘንግ ይላክ የነበረውን አበባ ቆጥራ የምታረጋግጥበት፣ ግልጽ የሆነ አሠራር እንዳልነበራት በመከራከር ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ዋነኛ ነጥብ አካቶ የአበባ ዘርፍን ጥያቄ ውስጥ ከተዋል በተባሉ ነጥቦች ላይ አሥራት ሥዩም አቶ ዓለም ወልደገሪማን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለተኛው የኢኮኖሚ ዕቅድ ዓመታት ውስጥ ኤጀንሲው የሚያከናውናቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ዓለም፡- የእኛ ኃላፊነት ሆርቲካልቸር ዘርፉን ማሳደግ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እኛ የምናተኩርባቸው አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ኸርብስ ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች ላይ እናተኩራለን፡፡ የተለያዩ የልማት ኮሪደሮች ላይ ለእነዚህ ምርቶች የሚሆን መሬት ማመቻቸት አንዱ ሥራችን ነው፡፡ ከዚያም በሻገር ባለሀብቶችን የመሳብ ሥራም እንሠራለን፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎችም ጋር በጋራ በመሆን የምንሠራው ሥራ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ አምራቾች የሚገኙበት ዓውደ ርዕይ ላይ እየተገኘን እንመለምላለን፡፡ ቅድመ ምርት እንዲሁም ድኅረ ምርት ተግባራት ላይ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ በመስክ እየተገኘንና እያንዳንዱን እርሻን እየጎበኘን ደካማ ውጤት ያላቸው ባለሀብቶችን የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው ላይ ተሞክሮ በመውሰድ ድጋፍ እናደርግላቸዋለን፡፡ በገበያ የማስተሳሰር ሥራም እንሠራለን፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ውጭ ያሉ ሚሲዮኖቻችን ያዘጋጀናቸውን የምርት ‘ስፔሲፊኬሽኖች’ እንዲያተዋውቁልን እናደርጋለን፡፡ ይህም ብቻም ሳይሆን ያገኘነውን መሬት ተስማሚነቱ ምን ያህል እንደሆነ መረጃ በማደራጀት፣ መረጃውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እናሠራጫለን፡፡ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረም አገልግሎቶችን ለማግኘት እንጥራለን፡፡ ከኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ዘርፍ፣ ከቴሌኮምና ከሌሎችም ጋር በጋራ ለመሥራትና ችግሮችንም እየለየን በሚፈቱበት መንገድ ላይ አብረን እንሠራለን፡፡ ከክልሎችም ጋር በመስማማት መሬት የማዘጋጀት ሥራ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንዳሉት ዋና ዋና ሥራዎች የሚባሉት ገበያ፣ ቴክኖሎጂና ድጋፍ መስጠት ላይ ኤጀንሲው ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከገበያ ጋር በተያያዘ አብዛኛው የኢትዮጵያ አበባ በደች ገበያ ነው የሚሸጠው፡፡ ከበፊትም ጀምሮ ገበያውን የማስፋፋት ተግባር ላይ ከፍተኛ ግፊት ነበር፡፡ እንደሚገባው ገበያውን ማስፋፋት ያልተቻለው በምን ምክንያት ነው? ምን ለማድረግስ ታስባላችሁ?

አቶ ዓለም፡- ገበያውን ለማስፋት አስፈላጊ ከሆኑት አንደኛው ተወዳዳሪ አበባ ማምረት ነው፡፡ ገዥዎችን አፈላልጎ የማግኘት ሥራም ወሳኝ ነው፡፡ የእኛ አበባ 80 በመቶ የሚሆነው ወደ አንድ ገበያ ብቻ የሚያቀና ነው፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬም አብዛኛው የምንሸጠው ምርት በአካባቢው ገበያ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በእኛ በኩልም ሆነ በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር በኩል ብዙ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጥረት እያደረግን ብዙ ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡ ገበያዎችን እያፈላለግን፣ ትላልቅ ገዥዎች የሚገኙበት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ሲዘጋጅና መረጃው ሲመጣ ወደ ማኅበሩ እንልካለን፡፡ ነገር ግን ከአቅም ውሱንነት የተነሳ በሚችሉትና ይጠቅመናል ብለው ባመኑት ንግድ ትርዒት ላይ ብቻ ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ ተሳትፏችን ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ የማስተዋወቂያ ሥራ ዓውደ ርዕይ ማዘጋጀት ነው፡፡  ባለሀብቶች በሚፈልጉ ጊዜ የድጋፍ ደብዳቤ እንጽፋለን፡፡ የምርት ናሙና በነፃ እንዲልኩ እናግዛለን፡፡ ለዚህ እንዲተባበራቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  እንጽፋለን፡፡ ገበያውን ሰብሮ ለመግባት ብዙ ጥረት ቢደረግም፣ ብዙ የንግድ ዓውደ ርዕይ ቢደረግም ገና ብዙ ይቀራል፡፡ በዚያም ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአውሮፓ ኢኮኖሚ ላይ በታየው መዋዠቅ ሳቢያ የዩሮ መገበያያ ገንዘብ የምንዛሪ ተመን በጣም በመውደቁ ፈታኝ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር የዩሮ የምንዛሪ ለውጥ ከ6.5 በመቶ ልዩነት አሳይቷል፡፡ ይህ ማለት ወደ ሁለት ብር ዝቅ ያለ ልዩነት አለው፡፡ ይህ መሆኑ በሁለት መንገድ ባለሀብቶችን ይጎዳል፡፡ አንደኛው የገንዘብ ፍሰታቸው ዝቅ እንዲል ያደርገዋል፡፡ ድሮ ከአንድ ዶላር አኳያ ስድስት ብር ያገኙ የነበሩ አምራቾች አሁን ወደ ሁለት ብር ዝቅ ሲልባቸው አራት ብር ከሰሩ ማለት ነው፡፡ እኛ ደግሞ አጠቃላይ የዘርፉን ገቢ ሪፖርት የምናቀርበው በዶላር ግብይት ተንተርሰን ነው፡፡ ስለዚህ በዩሮ ያገኘነውን በዶላር ስንለውጠው በምንዛሪ ለውጡ ሳቢያ አነስተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይኼ ጎጅ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ገበያውን ሰብረን ባለመግባታችን ምክንያት ባለሀብቱም እየተጎዳ ነው፡፡ ወደ ጃፓንም ለመግባት ሞክረናል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጃፓን መሄድ በመጀመሩ ወደዚያ ሄደው እንዲሸጡ ባለሀብቶችን ብናግባባም ውጤቱ ከምንጠብቀው እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ በድፍረት ወደ ገበያ ሰብረው የማይገቡበት ምክንያት ዶላርም ሆነ ሌላው የውጭ መገበያያ ወደ አገር ውስጥ በግድ ከማምጣት ጋር ስለሚያያዝ ነው፡፡

አበባ ወደ ውጭ በሚላክበት ወቅት ገዥው አስተማማኝና ጠንካራ መሆን መቻል አለበት፡፡ ምርት ኤክስፖርት ከተደረገ በኋላ የውጭ ምንዛሪ መምጣት መቻል አለበት፡፡ የሚያገኟቸው ገዥዎች ጠንካራ ካልሆኑና ከተላከው ምርት የውጭ ምንዛሪ ሳይገኝ ቢቀር፣ ተጠያቂነት የሚያስከትል በመሆኑ በብሔራዊ ባንክ በኩል ሲያወራርዱ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ እንዲህ በተደራረበ ነገር ምክንያት ችግሮች አሉ፡፡ እኛ ግን ሥራችንን አላቆምንም፡፡ አጋጣሚውን እየጠበቅን አበባውን የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ በጥናት ላይ ያሉ ይህንን ሊያግዙ የሚችሉ ሐሳቦች አሉን፡፡ አንድ አዲስ ነገር ሲመጣ በአገር ደረጃ፣ በሌሎች ዘርፎች ላይ ምን ያስከትላሉ የሚለውንም ማየት ስለሚያስፈልግ ጥናቶቹና ሌሎች አገሮች ውስጥ ያሉ አሠራሮችን አምጥቶ መጠቀሙ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አገሪቱ ትስስር በሚፈጥር መንገድ ተጠቃሚ መሆን ስላለባት ሌሎችንም ዘርፎች አብረው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሐሳቦች አሉ፡፡ አሁን ይፋ የማይደረጉ ናቸው፡፡ ከኬንያ ተሞክሮ ወስደን መጥተናል፡፡ ከጃፓን ገበያ ባሻገር ሰሜን አሜሪካ ያለውን ገበያም ለማየት ሞክረናል፡፡ ትልቅ ገበያ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ትልልቅ ገዥ የተባሉ አሥር ኩባንያዎችን አምጥተን ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳሰብነው ሳይሆን ቀርቶ ተመልሰው ሄደዋል፡፡ ከኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የሩሲያ ገበያ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የሩሲያና የአውሮፓ መንግሥታት አለመስማማት እንዲያውም በሌሎች ገበያዎች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ሩሲያ ይሄድ የነበረው አበባ አሁን መግባት ባለመቻሉ ምክንያት፣ ከሌሎች ታዳጊ አገሮች አበባ ወደ አውሮፓ ገብቶ መልሶ እንዲላክ የሚደረግበት አሠራር አሁን በመቀነሱ አቅርቦቱን የተትረፈረፈ አድርጎታል፡፡ የተትረፈረፈ አቅርቦት ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ በመሆኑ የሩሲያ ገበያ ተፈላጊ አይደለም፡፡ የሰሜን አሜሪካና የጃፓን ገበያ ውስጥ ለመግባት ጥረቶች አሉ፡፡ የጃፓን ገበያ ላይ ሙከራ ካደረግንበት ጊዜ ጀምሮ መሻሻል ቢኖርም ይህን ያህል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሩሲያ ገበያ ከዚህ በፊትም ለረጅም ጊዜ የቆየ ነው፡፡ ጃፓንና ጀርመን ላይም ሲሞከር ነበር፡፡ ሩሲያ ላይ አሁን ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ በፊትም ተሞክሮ ስኬታማ አልነበረም፡፡ ምንድነው ችግሩ?

አቶ ዓለም ብዙ ጊዜ ጥረት ተደርጓል፡፡ እኔ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ኤጀንሲውን የተቀላቀልኩት፡፡ ሁለት ዓመት ገደማ፡፡ ቀደም ሲል ብዙ ተሞክሯል፡፡ የንግድ ትርዒት ለማዘጋጀት ብዙ ተሞክሯል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋርም ብዙ ለመሥራት ሲሞከር እንደነበር እሰማለሁ፡፡ ነገር ግን የሩሲያ ገበያን ሰብሮ መግባት አልተቻለም፡፡ ብዙ ጥያቄዎች አሏቸው፡፡ ብዙም ትኩረት የሚስብ ገበያ አልሆነም፡፡ አንድ የሩሲያ ኩባንያ እዚህ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ወደ ሩሲያ ይልክ ነበር፡፡ ይህ ኩባንያ ለሩሲያ ገበያ በር ከፋች ይሆናል የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ ነገር ግን ዘግቶ እርሻውም ጨረታ ወጥቶበታል፡፡ ምክንያቱም ለላከው ምርት ገንዘቡ ሊላክለት አልቻለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ላኪዎቻችንም ሆኑ አምራቾች ገበያ መፈለግ አለባቸው፡፡ ስለፈለግነው ብቻም ግን አይመጣም፡፡ እኛ አገናኝ ሆነን እዚህ ገበያ ተገኝቷልና ሽጥ አንልም፡፡ ብንል እንኳ ብዙ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ጥቅምና ጉዳቱን የሚያውቀው አምራቹ ወይም ላኪው ነው፡፡ ለምሳሌ ላክ ብለን ወትውተነው ባይሳካለት ኃላፊነቱን ማን ነው የሚወስደው? ከገዥው ጋር ያላቸው ግንኙነት ወሳኝ ነው፡፡ ለተላከው ምርት ገንዘቡ ወደ አገር ውስጥ ባይመጣ አደጋ አለው፡፡ ግዴታው ለሁሉም የኤክስፖርት ዘርፍ ነው፡፡ የእኛ ሥራ ነገሮችን ማመቻቸት ነው፡፡

ሪፖርተር– ከገበያ ጋር በተያያዘ የአየር መንገዱን የበረራ መስመሮችን ተከትሎ ገበያ የማስፋት ሥራ ለመሥራት ሲሞከር ነበር፡፡ የጃፓን ገበያ ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጪ አዳዲስ ገበያዎች ላይ ምን የታዩ አማራጮች አሉ?

አቶ ዓለም፡- አሜሪካ ብዬሃለሁ፡፡ አየር መንገዱ ወደ ሎስአንጀለስ በረራ ጀምሯል፡፡ ይህንን መስመር ተከትሎ በማኅበሩ በኩል ገበያ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የእኛም የማኅበሩም ጥረት አንድ ዓይነት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የክብር ቆንስላዎች ጋር እየሠራን ነው፡፡ እዚህ መጥተው በአበባ ልማት ላይ የተሠማሩ ባለሀብቶችን በማነጋገር ከውጭ ገዥዎች ጋር እንዲያገናኙ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ማኅበሩ በበኩሉ በተደጋጋሚ የንግድ ትርዒቶች ላይ በመሳተፍና ባለሀብቶችን ይዞ በመገኘት የአበባ ዘርፉን ለማስተዋወቅ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከገበያ ወደ ድጋፍ ስንወጣ ከመሬት አቅርቦት በተጨማሪ ሌሎች ድጋፎችንም ይሰጣል፡፡ የአበባ እርሻዎች የሚያነሱት ችግር በተለይ ከማስፋፊያ ጥያቄ ጋር በተያያዘ እጥረት እንዳለ ነው፡፡ መሬት አናገኝም የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ መሬት የማይሰጥበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዓለም፡- አንዱ ሥራችን መሬት ማቅረብ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ስንሰጥ አንደኛው ምርታማነት እንዲጨምር ነው፡፡ ሁለተኛ የአመራረት ሥርዓትን በማሻሻል የማምረቻ ወጪዎች እንዲቀንሱ ማገዝ ነው፡፡ ጥሩ ጥራት ያለው አበባ እንዲመረት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ብቻ የሚመረተውን መጠን ከፍተኛ ማድረግ አይቻልም፡፡ ምርቱን ከፍ ለማድረግ ምን ማድረግ ያስፈልጋል ካልን መሬት ማመቻቸት፣ አዳዲስ ኢንቨስተሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ ከዚህ ዘርፍ ለማግኘት የምትፈልገው የውጭ ምንዛሪ ትልቅ ነው፡፡ የተለጠጠ ዕቅድ አላት፡፡ ይህን ለማሳካት መሬት ማመቻቸት ይገባል፡፡ መሬት የሚሰጠው አዲስ ለመጡት ብቻም ሳይሆን ማስፋፊያ ለሚፈልጉትም ጭምር እንጂ፡፡ የማስፋፊያ ጥያቄ የሚያቀርቡት መሠረተ ልማት አላቸው፡፡ ሁሉም ጀምረዋል፡፡ ከቆይታቸው አንፃር ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ተላምደው እየሠሩ በመሆናቸው ብዙ ለመሥራት ያመቻቸዋል፡፡ ባላቸው ላይ ተጨማሪ ቢያገኙ ውጤታማ መሆን ይችላሉ፡፡ መጠኑን እንዲህ ከፍ ብናደርግላቸው አጋነንክ ካላልከኝ ዘርፉ በእጥፍ ሊያድግ የሚችል ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል መሬት የተሰጣቸው ገጠራማ አካባቢ ነበር፡፡ አሁን ግን የክልል ከተሞች እየሰፉ በመምጣታቸው እርሻዎቹ ወደ ከተማ ማስተር ፕላን እየገቡ መጥተዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ የማስፋፋት ዕድላቸው ችግር ውስጥ እየገባ መጥቷል፡፡ ክልሎች የማስፋፊያ መሬት ለመስጠት በመቸገራቸው የማስፋፊያ መሬት ማግኘት አልተቻለም፡፡ ጠንካራ የሆኑና እኛም የምንመሰክርላቸው ባለሀብቶች የማስፋፊያ ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ካሉበት ተነስተው ሌላ ቦታ መሄድ ይቸግራቸዋል፡፡ ወጪውም አስተዳደራዊ ሥራቸውንም ከባድ ይሆናል፡፡ በአንፃሩ ባለሀብቶቹ ርቀው መሄድም አይፈልጉም፡፡ በአጭር ርቀት ውስጥ ሆነው መሥራትን ይፈልጋሉ፡፡

ስለዚህ በአማራ ክልል አማራጭ የማስፋፊያ ሥራዎችን ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡ ከኬንያ የሚመጡ ባለሀብቶች መሬት ወስደው ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ እዚህ ያሉት ባለሀብቶችም እየተቀላቀሏቸው ነው፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ኤርፖርቶች ላይ ማሻሻያ እየተደረገ ነው፡፡ አየር መንገዱም በቀላሉ እየተመላለሰ ለማንሳት የሚያስችለውን የጭነት መጠን ማምረት ያስፈልጋል፡፡ ወደ እርሻው የሚያደርስ 14 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዲሠራና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ምርቱን በእጥፍ ለማሳደግ ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ አበባ ሰፊ ቦታ ሳይዝ ብዙ ገቢ የሚያስገኝ ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም. በ500 ሺሕ ሔክታር ላይ ከተስፋፋው ቡና 780 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚገኘው፡፡ 1,500 ሔክታር መሬት የያዘው የአበባ ኤክስፖርት ግን 203 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ነው፡፡ በቡናና በአበባ መሬት መካከል ያለውን ልዩነት በቀላሉ ማነፃፀር ትችላለህ፡፡ ምጣኔ ቢወጣ አንድ በመቶ የማይሞላ ቦታ በመያዝ አንድ አራተኛውን ከቡና የሚገኘውን ገቢ አበባ እያስገኘ እንደሆነ ትመለከታለህ፡፡ ስለዚህ ማስፋፊያ በሚፈቀድባቸው አካባቢዎች የክልሎችን ዕቅድ በማይነካ መልኩ ማካሄድ ነው፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ አዳዲስ መሬቶችን የማመቻቸት ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን እየሠራን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአበባ አልሚዎች የተያዘው መሬት እንዳለ ሆኖ አንዳንዶቹ መሬቶች ግን ከአበባ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ባሻገር ገበሬው የሚያመርታቸውን ምርቶች በማምረት ሥራ ላይ የተሠማሩ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይህንን ነገር ትከታተላላችሁ? የተሰጠው መሬት ሙሉ ለሙሉ ለተሰጠበት ዓላማ መዋሉን በምን መልኩ ትከታተላላችሁ?

አቶ ዓለም፡- መሬት በማመቻቸት ሥራ ውስጥ አንዱ ይህንን የሚመለከት ነው፡፡ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከመሬት ኃላፊዎች ጋር በመተባበር ሰፊ ጥናት አካሂደናል፡፡ 90 ባለሀብቶች ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ ማን እንዳለማና እንዳላለማ፣ ምን ያህል መሬት በእያንዳንዱ ባለሀብት እጅ እንደሚገኝ ተጠንቷል፡፡ በዚህም ለ25 ባለሀብቶች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሰጥተናል፡፡ ጥብቅ ክትትል ይኖረናል፡፡ ይህንን ስናደርግ በመጀመሪያ ያላለሙበት ምክንያት ምን እንደሆነ እናጣራለን፡፡ ከመንግሥት የጎደለ ነገር ካለ ወይም እነሱ ስላልፈለጉ ነው የሚለውን እናያለን፡፡ በመንግሥት በኩል ማሟላት የነበረብንና ያላሟላነው ነገር ካለ ማየት አለብን፡፡ ደግፈን እንዲያመርቱ ማድረግ ኃላፊነታችን ስለሆነም ነው፡፡ ይህንን ካደረግን በኋላ የድርጊት መርሐ ግብራቸውን እንዲያመጡ አድርገናል፡፡ መቼ ምን እንደሚያለሙ፣ መሬቱን እንዴት እንደሚጠቀሙና ምን ችግር እንዳለባቸው የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ የመንገድ ችግር በመርቲ አካባቢ እንዳለ አይተናል፡፡ ይህንን ለመንግሥት አሳውቀን 11 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዲሠራ ታቅዷል፡፡ የበጀት ጥያቄ ለመንግሥት ቀርቧል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ፍትሐዊ የመስኖ አጠቃቀም ችግር ታይቷል፡፡ እኛ ይህንን እየፈታን እነሱም ራሳቸውን እያስተካከሉ ይሄዳሉ፡፡ እኛ ባላሟላነው ነገር ምክንያት ዕርምጃ አንወስድም፡፡ ምንም ያላለሙት ላይ ግን የመንጠቅ ዕርምጃ በመውሰድ መሬቱን ወደ መንግሥት መልሰናል፡፡ አንዳንዱ ያልተመቸ መሬት፣ አንዳንዱ ለሆርቲካልቸር የማይመች አዋጭ ያልሆነ ቁርጥራጭ መሬት ተሰጥቶት ይሆናል፡፡ ይህንን በማስተካከልና በመደገፍ የተሻለ እንዲያለማ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ ባለሀብቱ የማይሠራበት ከሆነ ግን መሬቱን መረከብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ እየደገፍነው የማያለማ ከሆነ እንደምትነጥቀው ማወቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፋይናንስ ድጋፍ ጋር በተገናኘ ኤጀንሲው ከልማት ባንክ ጋር በመሆን ዘርፉ ፋይናንስ እንዲያገኝ እያደረገ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 ገደማ በተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት ዘርፉ ከባድ የፋይናንስ ችግር ውስጥ በመግባቱ ብድር የነበረባቸው 42 ያህል እርሻዎች የብድር መክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘም ተደርጎ ነበር፡፡ ግማሾቹም በልማት ባንክ ለመተዳደር የተገደዱበት ጊዜ ነበር፡፡ እነዚህ እርሻዎች አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?

አቶ ዓለም፡- እኔ በዚያን ጊዜ ስላልነበርኩ አላውቀውም፡፡ የሆርቲካልቸር ኤጀንሲ ሥራ እንደሠራ መረጃው አለኝ፡፡ በፋይናንስ ቀውሱ ሳቢያ ሊወድቁ የደረሱ 42 እርሻዎችን ታድጓል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኛ ባለሙያዎች ጋር በነበረኝ ውይይት ከእነዚህ እርሻዎች ብዙዎቹ ውጤታማ ሆነው መዝለቃቸውን ተረድቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ልማት ባንክ አስተዳደራቸውን ተረክቦ ሲሠሩ የነበሩ እርሻዎች ከዚህ ተላቀው በራሳቸው እየሠሩ ነው ማለት ነው?

አቶ ዓለም፡- ልማት ባንክ ይዟቸው የነበሩት ቀንሰዋል፡፡ የደከሙ ባለሀብቶች እርሻቸውን ወደ ሌሎች አዛውረዋል፡፡ አሁን በልማት ባንክ እጅ የሚገኙ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ቦታ እየጠየቁ ያሉ ባለሀብቶች ምናልባት ከዚህ ቀደም መክፈል ሳይችሉ ቀርተው የሚሸጡ ካሉ ብለን ልማት ባንክን ጠይቀናል፡፡ ከባንኩ ፕሬዚዳንት ጋርም ተነጋግረናል፡፡ ሆኖም በዕዳ የተያዙ እርሻዎች እንደሌሉ ተረድተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የቴክኖሎጂ ሽግግርም ኤጀንሲው ድጋፍ ከሚሰጥባቸው መስኮች አንዱ ነው፡፡ የተግባር ሥልጠና የሚሰጥበት ማዕከል መልካሳ ላይ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ይህ ማዕከል በአበባ መስክ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን ታስቦ የተከፈተ ቢሆንም እየሠራ አይደለም፡፡ ማዕከሉ ተደራጅቶ ሳለ የማይሠራበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዓለም፡- የመልካሳ ማሠልጠኛ ማዕከል ብዙም እንቅስቃሴ የለውም፡፡ ባለፈው ዓመት እንዲህ ያሉትን ሥራዎች ለመሥራት በጀት ጠይቀን ስላልተፈቀደልን ብዙም አልሄድንበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ ያልተሟሉለት ነገሮች ነበሩ ማለት ነው?

አቶ ዓለም፡- በታሰበው መንገድ ማዕከሉ አልተዘጋጀም ነበር፡፡ አደረጃጀቱ፣ የሕንፃው አሠራርና የመሳሰሉት ነገሮች በታሰበው መንገድ ለሥልጠና በሚያመች መልኩ አልነበረም የተሠራው፡፡ እንደገና መልሶ ማደረጃጀት፣ ፕሮግራም ማዘጋጀትና ሌሎችም ሥራዎችን መሥራት ይፈልግ ነበር፡፡ እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን በጀት ስላላገኘን አልሠራንም፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር በተያያዘ የተሠሩ ነገሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ዓለም፡- አቅም ግንባታ አንዱ ነው፡፡ የተጣመረ የአቅም ግንባታ ማኑዋሎች ከዚህ ቀደም ቢዘጋጁም እነዚህን ለማሻሻል ፈልገን ነበር፡፡ በተለይ በአትክልትና በፍራፍሬ መስክ ነው፡፡ ከመንግሥት በጀት ተፈቅዶልናል፡፡ የተቸገርነው አማካሪ ድርጅቶችን በሚፈለገው የሥራ ደረጃ እንዲሠሩ ለማድረግ ሁለት ዓመት ሞክረን ልናገኝ ግን አልቻልንም፡፡ ዓለም አቀፍ ጨረታም አውጥተን ሊሆን አልቻለም፡፡ የሚመጣው አንድ የውጭ ኩባንያ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሠርቶ የነበረ ዲኤልቪ የሚባል ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ግን እኛ የምንፈልገውን መሥፈርት ሊያሟላ አልቻለም፡፡ እኛ ቢሮ እየሠሩ ወደ መስክ እየወጡ እንዲሠሩ ነው የምንፈልገው፡፡ አንደኛ ልምድና ብቃት ያለው ባለሙያ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ጀማሪዎችን ነው የሚያመጡት፡፡ ሁለተኛ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በመገኘት መሥራት የሚጠበቅባቸውን ጊዜ በአጭር እየገደቡ ለእኛ አልጠቅም ስላለ ለጊዜው አቆይተነዋል፡፡ ሥልጠናው በተግባር በመስክ ላይ እንዲሰጥና በቢሯችንም እየተገኙ እንዲያሠለጥኑ፣ በተለይ በምርት ዘመን እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ባለመሆኑ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በጀቱን ወደሚቀጥለው ዓመት እንዲያዞሩልን ተነጋግረናል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪን ከማምጣት ጋር በተያያዘ ከሦስት ዓመት ወዲህ ወደ ሥራ የገባ መመርያ አለ፡፡ መመርያው አበባዎች ወደ ውጭ ሲላኩ ከዚህ ቀደም በዘንግ የነበረውን በማስቀረት በኪሎ ግራም እንዲሆን አድርጓል፡፡ ብዙ አነጋጋሪ የሆነ መመርያ ነው፡፡ ይህንን መመርያ ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው? ሲወጣስ ከባለድርሻዎች ጋር ያደረጋችሁት ምክክር ምን ይመስላል?

አቶ ዓለም፡- በራሴ ግምት እንደሚመስለኝ አበባን በዘንግ እንዲላክ ማድረጉ አዋጭ አይደለም፡፡ መቁጠር ስለማይቻል በላኪው መልካም ፈቃድ ላይ የሚወሰን ነው፡፡ መቶ ዘንግ እልካለሁ ካለህ መቶውንም መቁጠር ይጠበቅብሃል፡፡ ይኼ አበባው የታሸገበትን ካርቶን ከፍተህ መቁጠር ያስከትላል፡፡ አለበለዚያ በእምነት መሥራት ሊኖርብህ ነው፡፡ ስለዚህ አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልከውን አበባ በሙሉ በዘንግ እንቁጠር ቢባል ከጊዜና ከአሠራር አኳያ አይመችም፡፡ ከዚህ በፊት እየተቆጠረ ይሠራ ነበር ለማለትም ቀድሞ የነበረውን ነገር በዚህ ደረጃ ተከታትዬው ባላውቅም አበባ ይቆጠር ነበር ለማለት አልችልም፡፡ መቶ ዘንግ ነው ተብሎ ከመጣ አዎ መቶ ነው ብለህ ከመቀበል ውጪ ምንም አማራጭ የለህም፡፡ ስለዚህ በአመኔታ ላይ በሚሠራ ሥራ ላይ ተመርኩዘን አገሪቱ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሪ እናገኛለን ብዬ አላስብም፡፡ በዚያም ላይ ጥራቱ ይጎዳል፡፡ በካርቶን የታሸገ አበባን እየቀደድን እንቁጠር ማለት ከአሠራር አስቸጋሪነቱ ባሻገር ለሌላ ነገር በር ይከፍታል፡፡ ኬንያዎች አበባውን የሚለካ መሣሪያ አላቸው፡፡ እኔ በሄድኩባቸው አገሮች ዘንግ በመቁጠር የአበባ መጠን የሚለካበትን አሠራር አላየሁም፡፡ አበባው በስክሪን ውስጥ ሲያልፍ ምን ያህል መጠን እንደተላከ በሚዛን ይታያል፡፡ በሚዛን የሚሠራ ነገር ግልጽነት ያለው ነው፡፡ በሚዛን የሚሠራ ከሆነ ለአገራችን ያዋጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌላ ጊዜ በዘንግ የሚሠራበት አሠራር የተሻለ ነበር የሚሉ ሰዎች እንዴት ተቆጥሮ ይሻላል አይሻልም የሚለውን ነገር በማስረጃ ቢያቀርቡት ጥሩ ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ከባለድርሻዎቹ ጋር መነጋገር ይቻላል፡፡ ዝም ብዬ ግን ይሻል ነበር አይሻልም ልል አልችልም፡፡ በምክንያታዊት መነጋገር አለብን፡፡ ከዚህ በፊት ሲላክ የነበረውን የአበባ ዘንግ ማን ነው የቆጠረው ለሚለው ማንም መልስ የለውም፡፡ እንዴት ተደርጎ ይቆጠር ነበር? ጉምሩክ ይህንን ያደርግ ነበር ወይ? ለሚለው ከጉምሩክ መረጃ ማግኘት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ እኔ በኪሎ መሥራቱ ግልጽነት የሰፈነበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እያንዳንዱን ዘንግ የሚቆጥር ማሽን ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ ስክሪኑ ለደኅንነት ካልሆነ በቀር ዘንግ የሚቆጥር ስለመሆኑ መረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ አብዛኞቹ በኪሎ ነው የሚሠሩት፡፡ በኬንያ ያየሁት ይኼንኑ ነው፡፡ ሚዛኑ ትክክል እስከሆነ ድረስ ግልጽነቱ አያሻማም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያታዊነቱ እንዳለ ሆኖ በደች ገበያ አበባው በዘንግ መሸጡ ግን እርግጥ ነው፡፡ እዚህ በኪሎ ይሸጥ ከተባለ አበባዎቹ የተለያየ የክብደት መጠን ስለሚኖራቸው በአንድ ኪሎ ግራም አበባ ውስጥ የሚኖረው የዘንግ ብዛት የተለያየ ይሆናል፡፡

አቶ ዓለም፡- በተገመተው መሠረት አማካይ ዋጋ ተወስዶ፣ የተጣራ ዝቅተኛው የመሸጫ ዋጋ ነው የተቀመጠው፡፡ በኪሎ ግራም ሲቀመጥ ከፍተኛው ዋጋ ሳይሆን ዝቅተኛው የተጣራ መሸጫ ዋጋ ስለሚቀመጥ በተለያየ መንገድ ምርመራ ተደርጎ ዋጋው ሌላ ሆኖ ቢገኝ ላኪው ተጠያቂ ነው፡፡ ይህ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ብክነቱን፣ የኮሚሽን ክፍያውን ሌሎችም ማንኛውንም ወጪ ሁሉ የሚሸፍን ወጪ ነው፡፡ ይህንን ከተሞክሮ በማየት የተሠራ ይመስለኛል፡፡ ከፍተኛ ኃላፊዎች ባሉበት ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች የቦርድ አባላት ጋር ተነጋግረን መጀመሪያ ላይ በኪሎ 3.68 ዶላር የነበረው ዋጋ ወደ 3.864 ዶላር ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህንን ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ ጋር እየተከታተልን ነው፡፡ እርግጥ ሽያጫቸውን በዝርዝር ለመግለጽ ከቢዝነስ ሚስጢር አጠባበቅ አኳያ ፈቃደኛ ባይሆኑም ያን ያህል ሰፊ ልዩነት አይታይም፡፡ ከዚያ በላይ ዋጋ የሚገኝበት ጊዜም አለ፡፡ ነገር ግን የዩሮ መዳከም የሚፈታተናቸው ባለሀብቶች አሉ፡፡ እኔ ማወቅ የምፈልገው በዘንግ መላክ ይሻል ነበር ካሉ ማስረጃቸው ምን እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስለነበረው ነገር ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቢጠየቅና ዘንግ ይቆጠር እንደነበር ቢገልጽ ጥሩ ነው፡፡ ወደኋላ መመለስ ከተፈለገ እንዴት ይሠራበት እንደነበር ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ ገበያው ጥራት ይፈልጋል፡፡ እያንዳንዷ ካርቶን ተቆጥራ ይሠራ ቢባል አስቸጋሪ አይሆንም ወይ? ተግባራዊነቱ እንዴት ነው? መቶ ነው ያልከው ዘንግ 150 ስላለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድነው? በኪሎ ግን ሁለቱም ወገን ይተማመናል፡፡ የዘንግ አሠራር ሰዎችን ወደ ግላዊ አሠራርና ወዳልተገባ ጥቅም ውስጥ የሚከት ነው፡፡ በደመነፍስ ይሁን ከማለት ይልቅ ማስረጃውና መለኪያው ይቅረብ፡፡ ቁጥጥር ማድረግና መከታተል እንጂ ስለሽያጭ መጠን መረጃ ማግኘት በራሱ ከባድ ነው፡፡ ሚስጢራዊነት አለ፡፡ ከደች የሽያጭ መረጃ ለማግኘት ብንጠይቅም ማግኘቱ ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የደች ገበያ ለሁሉም ክፍትና የጨረታ ገበያ ነው፡፡ እያንዳንዱ ኩባንያ የሸጠው መጠን ምን ያህል እንደሆነ የግብይቱ መረጃ አለ፡፡

አቶ ዓለም፡- ይኼ ድሮ ነበር፡፡ የይለፍ ቃል በማስገባት ብቻ መረጃውን ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ አሁን የይለፍ ቃሉ አልሠራ ብሏል፡፡ በዚያም ላይ ሁሉም በጨረታ ገበያው ይሸጣል ማለት አይደለም፡፡ በሌሎች የሽያጭ መንገዶችም ይወጣል፡፡ ለጨረታ ገበያ የወጣው ሁሉ በዚያው ገበያ ይሸጣል ማለት እንዳልሆነ በጥናት ታይቷል፡፡ የተወሰነው በሌላ መንገድ እንደሚሸጥ ይታወቃል፡፡ ይህንን ሁሉ ተቆጣጥረህና ተከታትለህ ስለማይሆን ሁሉንም የሚያስማማ የተሻለ ዋጋ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ በርካቶቹ ጥሩ ዋጋ እያገኙና እያመጡ ነው፡፡ በአቅም ማነስ፣ በአበባ አመራረትና በጥራት ችግር ጥሩ ዋጋ የማያገኙ አሉ፡፡ የመሸጫ ወቅትና ሌሎችም ምክንያቶች ዋጋውን ሊወስኑት ይችላሉ፡፡ አሁን ወቅቱ በጣም ፈታኝ እንደሆነ ነው የማስበው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረ የሚመስለን ዋጋ አሁን ባለው የምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ወርዷል፡፡ በዩሮ ብናወራ ምንም ችግር አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን ወደ ዶላር ቀይረን ስንነጋገር ችግር አለ፡፡ በእኔ የግል አመለካከት የዘንግ አሠራር ከኪሎ የሚሻል መመዘኛ ሥርዓት ስለሌለው ኪሎ ለግልጽነትና ለአሠራር የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በአሠራር ጉድለት ምክንያት ባንክ ፈቃድ በመስጠት ያለበትን የኤክስፖርት ፈቃድ ላለማጣትና ከገበያውም እንዳንወጣ ግልጽነት ያለውን ሥርዓት መከተል ይገባል፡፡ የሚዛን አሠራር ለጉምሩክ፣ ለባንክ፣ ለቆጠራም ሆነ ለየትኛውም አካል የሚመች ቀላል አሠራር አስቀምጠናል፡፡ ድሮ ብሔራዊ ባንክ ነበር የሚቆጣጠረው፡፡ መረጃው ከሌሎች ባንኮች መረጃው ተጠናቅሮ እስኪመጣ ድረስ ባለው መጓተት ምክንያት ላኪው አላወራረድክም ተብሎ ቀጣይ የኤክስፖርት ፈቃድ ይከለከል ነበር፡፡ አሁን ግን የኤክስፖርት ፈቃድ ምርቱ ከተጫነ በኋላ ቁጥጥር እንዲያደርግ ተደርጓል፡፡ የማወራረድ ሥርዓቱ በየባንኩ ተደርጓል፡፡ ይህም የዋጋ ከፍና ዝቅን ለማስተካከልና አማካይ ዋጋ ለመያዝ ረድቷል፡፡ ድሮ ከነበረው አሠራር አሁን ትንሽ የተሻለ ነገር አለ፡፡ 

ሪፖርተር፡- መመርያው መነሻውን እንዲህ በማድረግ ዘንግን በኪሎ መተካቱ ግልጽ ሆኖ ተብራርቷል፡፡ ነገር ግን ከገቢና ከገበያው ተፅዕኖ አኳያ መመርያው እንዴት ታይቷል? ይህንን የማነሳበት ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ዋጋው ሲሰላ በዘንግ ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረው ገቢ መመርያው በኪሎ በማለቱ ምክንያት ቀንሷል ስለሚሉ ነው፡፡

አቶ ዓለም፡- ይህንን በምን ልታረጋግጥ ትችላለህ? ይህንን የሚሉ ሰዎች ከምን ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተው ነው የሚናገሩት? ምን ያህል ዘንግ እንደሚላክ ተቆጥሮ ባልተረጋገጠበት መንገድ የተሻለ ገቢ ይገኝ ነበር የሚባለው እንዴት ነው? ድሮ እኮ የዘንጉ ብዛት ስንት እንደሆነ አይቆጠርም ነበር፡፡ ጉምሩክ ይቆጥረው ነበር ማለት ይከብዳል፡፡ አሁን ግን በኪሎ መጠኑ እየታወቀ ነው የሚላከው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አገሪቱ ተጠቃሚ ነበረች አልነበረችም የሚሉት? ከምንስ ተነስተው ነው? ማስረጃቸው ምንድነው? እርግጥ በእኛ በኩል አነስተኛ ጥናት አድርገን ነበር፡፡ ባለሙያዎች በሚዛን መሆኑ ጉዳት እንደሌለው አጥተነዋል፡፡ ዘንግ ይሻል ነበር የሚሉት ሰዎች ማረጋገጫቸውና መነሻቸው ምንድነው? እኛንም እንዲመክሩን እንፈልጋለን፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ይህንን አይታችሁታል ወይ ቢሉን እንፈልገዋለን፡፡ ምክንያቱም እኛም የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ነው እዚህ የተቀመጥነው፡፡ የባለሀብቶችንም ሞራል የማይነካና ጉዳት ላይ የማይጥላቸው መሆንም አለበት፡፡ የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁመው፣ ገበያ ፈልገው የሚልኩ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ስለምንወስነው ውሳኔ መጠንቀቅም አለብን፡፡ ከመሬት ተነስተን ለማየት ብቻ ሳይሆን ጥናት አካሂደን መሆን አለበት፡፡ ጥናት ሲጠና ችግሮች ሊኖሩበት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ካጠናነው ጥናት ለመረዳት እንደቻልነው ከሆነ በኪሎ መሆኑ አነስተኛ ዋጋ የሚሰጡ ገበያዎችንም ጭምር ለማዳረስ አስችሏታል የሚል ነው፡፡ በርከት አድርገህ ለመላክ የሚያስችል ዕድል አለ ማለት ነው፡፡ አሁን ጊዜው ፈታኝ ነው፡፡ የምንዛሪ ለውጥ ችግር አለ፡፡ በዩሮና በዶላር መካከል ከስድስት ዶላር በላይ የነበረው የምንዛሪ ልዩነት አሁን ግን እኩል በመሆኑ የላኪዎች የገንዘብ ፍሰት ላይ ጉዳት አለው፡፡ በአገራችን ገቢም ላይ የሚታይ ጫና አለው፡፡ በዩሮ ብንጠቀም ኑሮ ትልቅ ለውጥ ነበረው፡፡ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ስናየው አንድ ዩሮ በብር የሚመነዘርበት ዋጋ ከ27 ወደ 23 ወርዷል፡፡ ከዶላር ጋር በጣም ተጠጋግቷል፡፡ ላኪዎቹ ወደ አውሮፓ በዩሮ ይልካሉ፡፡

ገንዘቡ በብር ተመንዝሮ የሚሰጠው ግን በዶላር ምንዛሪ ልክ ነው፡፡ ስለዚህ በዘንግ ይሻል ነበር የሚሉ ሰዎች መረጃውን ይዘው መጥተው ቢመክሩን ሁላችንም የአንድ አገር ዜጎች ስለሆንና ለአንድ አገር ጥቅም የቆምን ስለሆንን ስህተት ካለም ለመታረም ዝግጁ ነን፡፡ መረጃውን ግን እንፈልጋለን፡፡ አስተማማኝና አሳማኝ ከሆነ እንቀበላለን፡፡ ማስረጃው ይምጣና በጋራ እንመርምረው፡፡ በጥርጣሬ ብቻ መመራት ግን ጉዳት ላይ ይጥላል፡፡ ይህ ዘርፍ በጣም እያደገ ያለ ነው፡፡ ለብዙ ሺዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ አበባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቡና የሚገኘውን ገቢ መተካት ይችላል፡፡ አፈጻጸሙን ብናይ በዚህ ዓመት በተለይ በዓመት በ17 በመቶ እያደገ ያለ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተነስቶ እዚህ የደረሰ የሚጠቅም ዘርፍ ነው፡፡ እኛ የሚሰማንን ገልጸናል፡፡ ማየት ያለብንና የተሻለ ነገር የሚቀርብ ከሆነ ከባለድርሻውም ከሚዲያም እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመሪያው የአምስት ዓመት ዕቅድ ከአበባ ዘርፍ የሚጠበቀው የወጪ ንግድ ገቢ እስከ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ የተቀመጠው ግን አነስተኛ ነው፡፡ ይኼ ከምን መነሻ ነው? ለእውነታው የቀረበ ዕቅድ ለማስቀመጥ ተፈልጎ ነው? ወይስ ምንድነው ታሳቢ የተደረገው?

አቶ ዓለም፡- ከሌሎች አገሮች አኳያ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከት ጂኦግራፊያዊ መገኛዋ በምድር ወገብ አካባቢ ነው፡፡ የደጋ አገሮች ከዚህ ዘርፍ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ መሬት እንደ ልብ ብንፈቅድ ሌሎች አገሮች የሚያገኙትን ጥቅም እናገኝ ነበር፡፡ አግሮኢኮሎጂውና የገበያ ቅርበቱ ብቻ አይበቃም፡፡ በዕቅዱ ለማስፋፊያውም ለሌላውም ሥራ መሬቱን ብናቀርብና አስፈላጊውን ነገር ታሳቢ ስለሚደረጉ ነው እንጂ፣ ዕቅዱ ከዚህም በላይ መሆን ይችል ነበር፡፡ ሌላ ተጨማሪ ግብዓት ሳይሟላ ሰፊ መሬት በማቅረብ ብቻ ወዲያውኑ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ነባራዊው ሁኔታን ማንፀበረቁ ግን ጥሩ ስለሆነ እንጂ መሥራት ይገባናል፡፡ እንደ ኤጀንሲ ክልሎች መሬት እንዲያቀርቡ የማሳመን ሥራ መሥራት አለብን፡፡ የማስፋፊያ መሬቶች እንዲፈቀዱ ማድረግ ይገባል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚመጡ ባለሀብቶች ምልመላ ላይም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ የፋይናንስ ችግር የገጠማቸው፣ አልፎ አልፎም የወደቁ፣ ወደ ሌላ ባለሀብት የተዛወሩም ይኖራሉ፡፡ ሒደት ነው፡፡ እንደ ካሩቱሪ ያሉም አሉ፡፡ እስከ 400 ሔክታር መሬት [ለአበባ] ተሰጥቷቸው በተለያየ ምክንያት ከስረውም ጭምር ሳያመርቱ የኖሩ አሉ፡፡ ስለዚህ ዕቅዱ ታሳቢ የሚያደርገው የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ፣ አሁን ያለንን የመሬት አቅርቦትና መሰል ነገሮችን ነው፡፡ ለጥጦ ማቀድ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በየጊዜው እንገመገማለን፡፡ እኛ ብቻም ሳንሆን ሁሉም የወጪ ንግድ ዘርፍን የሚመራ ኃላፊም ሆነ ላኪ ይገመገማል፡፡ በቋሚነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ስብሰባ አለ፡፡ ሁሉም ሚኒስቴር በየወሩ እየተሰበሰበ የታቀደውና የተሠራው ምን እንደሆነ፣ እንደ አፈጻጸማችን ሁላችንም እንገመገማለን፡፡ ዘርፉ እንዲያድግ ቁጭት ይዞን እየሠራን ነው፡፡ የሚፈለገውን ያህል ሠርተናል አልልም፡፡ እያደገና መታገዝ ያለበት ዘርፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመሬት ይዞታም በወጪ ንግድ ገቢ ደረጃም ስንመለከት የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ ያላቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ሚዛን ለማስተካከል ኤጀንሲው ምን እየሠራ ነው?

አቶ ዓለም፡- እንደ ፖሊሲ ዕድገቱ ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ የትኛውም ዘርፍ ላይ ስብጥሩ ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ የግድ ሆርቲካልቸር ብቻ አይደለም፡፡ በየትኛውም ዘርፍ በራሳችን መተማመን አለብን፡፡ በራሳችን ላይ መሠረት ያደረገ ነገር ዘለቄታዊ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ ግን ይህ ዘርፍ አስቸጋሪ ነው፡፡ የሚፈልገው ቴክኖሎጂ፣ ካፒታልና ገበያው ሁሉ አስቸጋሪ ነው፡፡ ዕውቀትም መሰጠትም ይፈልጋል፡፡ በርካታ ባለሀብቶች ገብተውበት ነበር፡፡ ከገቡት በርካቶቹ ስኬታማ አልሆኑም፡፡ የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሀብት እያልን አንመርጥም፡፡ ለሁሉም እኩል ዕድል እንሰጣለን፡፡ የውጭ ስለሆነ አንመርጥም፡፡ የአገር ውስጥ ስለሆነም አንከለክልም፡፡ በአትክልና ፍራፈሬ ዘርፍ በርካታ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እየገነቡ ቢሆንም በአበባ ውስጥ ግን ጥቂት ናቸው ያሉት፡፡ በአብዛኛው የውጭ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ለማስፋፋት ፍላጎት ያላቸው በርካታ የአገር ወስጥ ባለሀብቶች ግን አሉ፡፡ መሬቱ ስለሌለ ግን ማስፋፋት አልቻሉም፡፡ ሆለታ፣ ቢሾፍቱና ወልቂጤ አካባቢ ድጋፍ ያገኙ ጥቂት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ማስፋፋት ችለዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...