Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተሰናባቾቹና ተተኪዎቹ የብሔራዊ ባንክ ሹማምንት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የአመራር ለውጥና ሽግሽግ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥና ምክትላቸው በአዳዲስ ተሿሚዎች ተተክተዋል፡፡ የቀድሞዎቹም በሌላ የኃላፊነት ቦታ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርም የቀድሞዎቹን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ለአቶ ተክለ ወልድ አጥናፉና ምክትል ገዥና ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያ ለነበሩት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ለተሰናባቾቹ አስተዋጽኦ የዕውቅና ሽኝት፣ ለአዲሶቹ ተሿሚዎችም መልካም የሥራ ጊዜ እንዲሆንላቸው ማኅበሩ ያሰደናዳው ፕሮግራም  ሐሙስ፣ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ተካሂዶ ነበር፡፡

ፕሮግራሙን በማስመልከት የባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ፣ ተሰናባቾቹ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች፣ ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው ያበረከቷቸውን ተግባራት በመጥቀስ ዕውቅናና ምሥጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ በአቶ ተክለ ወልድና በምክትላቸው ዮሐንስ (ዶ/ር) አመራር ዘመን የፋይናንስ ዘርፉ ከየት ተነስቶ የት እንዳደረሰ አቶ አዲሱ አኃዛዊ መረጃዎችን አጣቅሰው ነበር፡፡  

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ እንዲህ ያለው የምሥጋናና የዕውቅና ፕሮግራም መልካም ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ካገለገሉ ስምንት ገዥዎች ውስጥ ለረዥም ዓመታት ባንኩን በመምራት ቀዳሚ መሆናቸው የተነገረላቸው አቶ ተክለ ወልድ፣ ላከናወኗቸው ተግባራት ምሥጋና እንደሚገባቸውም አዲሱ ገዥ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞዎቹ የብሔራዊ ባንክ ገዥዎች ለ20 ዓመታት በቆዩባቸው የኃላፊነት ዘመናት ምን እንደሠሩና ረዥሙን የኃላፊነት ቆይታቸውን እንዴት እንደተወጡት እንዲሁም ስላጋጠማቸው ፈተናና ስኬቶቻቸው ገለጻ አቅርበው ነበር፡፡ ይህም ፕሮግራሙን ለየት አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው የቀደሙ ሥራዎቻቸውን ያስታወሱት አቶ ተክለ ወልድ፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ለማሳደግ ተሠርተዋል ያሏቸውን ተግባራት በአኃዝ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡

ከ2002 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ስኬታማ እንዳደረጉት የጠቀሱት የቀድሞው ገዥ፣ ዘርፉ ስኬታማ ቢሆንም ሁሉ ነገር ግን አልጋ በአልጋ እንዳልነበርም ገልጸዋል፡፡ በተለይ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር አብሮ እንዲተገበር የተደረገው የፋይናንስ ፖሊሲ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሥጋቶች የነበሩበት ቢሆንም፣ ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የአምስት ዓመቱን ዕቅድ ከማሳካት አኳያ እንደ ትልቅ ስኬት የሚወሳው የአገር ውስጥ ቁጠባን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ በዋቢነት ተገልጿል፡፡

‹‹በዚህ ረገድ አንደኛውና ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረግነው የግል መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች የቁጠባ ነው፡፡ የረዥም ጊዜ ቁጠባና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የቁጠባ ሥርዓት እንዲሻሻል መደረጉ ነው፤›› በማለት አገሪቱ የቁጠባ መጠን በአሁኑ ወቅት ከ24 በመቶ በላይ ሊደርስ ስለቻለባቸው ሥራዎች አብራርተዋል፡፡

ቁጠባን ከፍ ለማድረግ ሌሎች በርካታ ተግባራት ስለመሥራታቸው ያወሱት አቶ ተክለ ወልድ፣ በኢትየጵያ የመጀመርያውን የቁጠባ ቦንድ ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት ተደርጎ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ በህዳሴ ቦንድ መተካቱን አስታውሰዋል፡፡ የህዳሴ ቦንድ ለህዳሴ ግድብ ፋይናንስ ለማሰባሰብ ተብሎ እንዳልተጠና አስታውሰዋል፡፡ ከቤቶች ግንባታ ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የተደረገው የቁጠባ ሥርዓትና ባንኮች ቅር ተሰኙበት ያሉት የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ ቁጠባን ለማሳደግ ብሔራዊ ባንክ ያስተዋወቃቸው ዕርምጃዎች ናቸው፡፡

እንዲህ ያሉት ተግባራት የአገር ውስጥ ቁጠባን ቢያሻሽሉም፣ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት የሚሆንና ለከፍተኛ ኢንቨስትመንት ግኝት ዋናውና አስኳል ሆኖ የተያዘው ግን የባንኮች ቁጠባ እንደነበር አቶ ተክለወልድ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በምን ዓይነት መንገድ ገንዘብ ሰብስበን ለኢንቨስትመንት ማዋል ይቻላል? የሚለው ላይ ብዙ ጥናት ከተደረገ በኋላ በቁርጠኝነት የተያዘው ቢያንስ እያንዳንዱ ባንክ የ25 በመቶ ቅርንጫፉን ማሳደግ አለበት በሚል ነው፤›› ያሉት ተሰናባቹ ገዥ፣ በዚህ ረገድ የተቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካት ባንኮች እንደተባበሩና እንዳላሳፈሯቸው በመግለጽ ለውጤቱ አወድሰዋቸዋል፡፡ ‹‹በ2002 ዓ.ም. 680 ብቻ የነበረው የባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 4,280 ደርሷል፡፡ የቁጠባ ሒሳብ ቁጥር በ2002 ዓ.ም. ከነበረበት አራት ሚሊዮን አሁን 28 ሚሊዮን እንዲደርስ አስችሏል፤›› ብለዋል፡፡

የባንኮች ሀብትና ትርፋማነት እየተስፋፋ መቀጠሉም ሲተገበሩ የቆዩ ፖሊሲዎች አስተዋጽኦን እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ሲያስመዘግቡ የቆዩት  ውጤት ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ለማስረዳትም፣ የአፍሪካ ባንኮችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በአፍሪካና በታዳጊ አገሮች በዓመት በአማካይ እስከ አምስት ባንኮች ከስረው ከገበያ ይወጣሉ፡፡ በኬንያንም አራትና አምስት ባንኮች በየዓመቱ ይወጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህ አልተከሰተም፤›› በማለት የቁጥጥርና የአስተዳደር ሥራዎች መናበብ ባንኮች ጤናማ ሆነው እንዲዘልቁ ማስቻላቸውን አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባንኮች እንቅስቃሴ ውስጥ በስኬት የሚጠቀሰው ሌላው ዓብይ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት ብቻ እንዲያዙ መደረጉን ነው፡፡ ‹‹በከፊል ከደቡብ አፍሪካና ከናይጄሪያ በስተቀር፣ በአፍሪካ የባንኮች ባለቤቶች በአብዛኛው የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡ አንድም የአገሬው ዜጋ ጭራሹን ባለቤት ያልሆነባቸው አገሮችም አሉ፤›› በማለትም እንደ ሞዛምቢክ ያሉ አገሮችን ዋቢ አድርገዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የወደፊቱን ባላውቅም እስካሁን ድረስ ባለው ፖሊሲ ግን ዘርፉ የውጭ ዜጎች የሌሉበት በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ መንግሥት ባለቤትነት የተያዘ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ከ3,400 በላይ የሚሆኑ ቅርንጫፎች ያሏቸው የግል ባንኮች፣ የ110 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ንብረቶች ናቸው ማለት ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በአማካይ ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ የፋይናንስ ዘርፉ የተጫወተው ሚና ትልቅ መሆኑና ዘርፉ የአንበሳውን ድርሻ  ስለመጫወቱ እምነታቸው መሆኑን አቶ ተክለ ወልድ አስረድተዋል፡፡ ምክትል ገዥ የነበሩት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) የአቶ ተክለ ወልድን ሐሳብ እንደሚጋሩ ገልጸው፣ በኃላፊነት ቦታቸው በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የዕድገት ጉዞ በሦስት ምዕራፎች እንዳለፈ ገልጸዋል፡፡ አንደኛው በሌላኛው ላይ ተመርኩዞና ፖሊሲ ተቀርጾለት እንዲተገበር ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በመጀመርያው ምዕራፍ በርካታ ባንኮች ገብተውና አዳዲስ ባንኮች ተከፍተው በርካታ ብድሮችን በማቅረባቸው በርካታ የተበላሹ ብድሮች ተፈጥረው ነበር፡፡ ‹‹ስለዚህ ያንን የማስመለስና የማጣጣም ሥራም ይሠራ ነበር፤›› ምክትል ገዥ ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ በሁለተኛው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ውስጥ ባንኩ በገንዘብ ፖሊሲ በኩል የተከተለው አካሄድ ግን ወግ አጥባቂ የሚባለውን ዓይነት አካሄድ ገዥው ባንክ እንደመረጠ ይህም ሆኖ፣ በዚህ ምዕራፍ የነበረው ወግ አጥባቂ የገንዘብ ፖሊሲ የኢኮኖሚ ዕድገቱን እንዳልገታው አስታውቀዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ዕድገታችን በአብዛኛው ከግብርና አካባቢ የመጣ ስለነበር ነው፤›› ብለውታል፡፡

ሦስተኛው የኢኮኖሚው ምዕራፍ ከስምንት ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ያለው ምዕራፍ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ በዚህ ወቅት ዕድገትን ለማምጣት የግድ ኢንቨስትመንት መምጣት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት፣ ለዚህ የሚስማማ የገንዘብ  ፖሊሲ መቀረፁንም አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዚህ የገንዘብ ፖሊሲያችን ላይ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ማተም ነው ሥራው የሚሉ አስተያየቶች ጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ወይም እውነታውን ያላዩ፤›› ናቸው በማለት፣ ብሔራዊ ባንክ ዋና ሥራው ገንዘብ ማተም ሆኖ ቆይቷል በማለት ከቀድሞ የባንኩ ባልደረቦች ሲሰነዘሩ የነበሩ ትችቶችን ኮንነዋል፡፡

‹‹እንዲያውም ይኼ ፖሊሲ በዚህ መልኩ ባይቀረፅ ኖሮ ዕድገቱ አይመጣም ነበር፤›› በማለት ዮሐንስ (ዶ/ር) ሞግተዋል፡፡ ‹ኢንቨስትመንትን ፋይናንስ ለማድረግ የገንዘብ ፖሊሲያችን በዚያው መልክ መቀረፅ ነበረበት፤›› ያሉት ተሰናባቹ ምክትል ገዥ፣ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ማደግ ያልቻሉበት ዋናው ሚስጥር ከገንዘብ ፖሊሲያቸው ይዘት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመዋቅራዊ ለውጥ ችግር እንዳለበት ማስታወስ እንደሚገባ የጠቀሱት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ በተለይ በወጪ ንግዱ በኩል ከታየ፣ በዚህ ዘርፍ ላይ የሚተገበሩ ፖሊሲዎች መስተካከል እንደነበረባቸው የራሳቸውን ምልክታ አስቀምጠዋል፡፡ በዘርፉ ሲተገበር የቆየው የባንኩ የወጪ ንግድ ፖሊሲ ሊታይ እንደሚገባው የሚጠቁም አስተያየት ነበር፡፡

አቶ ተክለ ወልድ የፋይናንስ ዘርፉ ቢያድግም፣ የወደፊቱ አካሄዱ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያመላከቱበትን ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ የባንክ ዘርፉ በተለይ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ወደኋላ ስለመቅረቱ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች በካፒታል አቅም፣ ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ በተደራሽነትና በሌሎችም መለኪያዎች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለሚገኙ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ጥሩ ውጤት አሳይቷል በተባለው የቁጠባ መጠን ላይ ብቻም ሳይሆን ኢኮኖሚው ዕድገቱን መቀጠል እንደሚጠበቅበትና ለዚህ ሁሉ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ የቀድሞው ገዥ  ምሳሌ በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡

‹‹አሁን 680 ቢሊዮን ብር ሰብስበናል፡፡ 670 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥተናል፡፡ ኢኮኖሚው ወደቀ ማለት ይኼ ገንዘብ አይመልስም ማለት ነው፡፡ ይህ ገንዘብ አይመለስም ማለት ከ28 ሚሊዮን አስቀማጮች ጋር መፋጠጥ ማለት ነው፡፡ የ110 ሺሕ ባለአክሲዮኖች ገንዘብ ቀለጠ ማለት ነው፤›› በማለት አሳሳቢ ጉዳይ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ሲባል ደግሞ መንግሥት የሚያወጣቸውን ማንኛውንም የፋይናንስ መሣሪያዎች ያለ ምንም ማቅማማት ‹‹የዛሬውን እንቁላል ሳይሆን የነገዋን ዶሮ በማሰብ፤›› ተግባራዊ ማድረግን እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ የሚፈልገው የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት በመሆኑና የረዥም ጊዜ አንቨስትመንት ደግሞ ገንዘብ ስለሚፈልግ፣ የሚፈለገውን ገንዘብ ባንኮች ቅድሚያ ለሚሰጠው ተግባር የውጭ ምንዛሪ አምኖ በመስጠት የኢኮኖሚው ዕድገት እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባ ወይም ይህን ባለማድረግ ኢኮኖሚው ከወደቀ የመጀመርያው ተጎጂ የፋይናንስ ዘርፉ እንደሚሆን አቶ ተክለ ወልድ አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራሙ የቀድሞዎቹ ገዥዎች የነበራቸውን የእርስ በርስ የሥራ ግንኙነት ያንፀባረቁበትም ነበር፡፡ ‹‹ላለፉት 27 ዓመታት በምወደው ዘርፍ ውስጥ በማገልገሌ በጣም ዕድለኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ተነስቶ አሁን የደረሰበት ደረጃ ለመድረሱ እንደ አንድ ተዋናይ በመሳተፌ፣ ለዚህም የራሴን አስተዋጽኦ በማድረጌ  ዕድለኛ ነኝ፡፡ ኢኮኖሚስት መሆኔንም የማመሠግንበት ነው፤›› በማለት ዮሐንስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ‹‹አቶ ተክለ ወልድ የሚጨነቅልኝ አለቃዬ ነበር፤›› ያሉት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ‹‹በየጊዜው በሚነሱ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ክርክር እናደርጋለን፡፡ በምንስማማው እንስማማለን፡፡ በማንስማማበት ደግሞ እንከራከራለን፡፡ ተከራክረን እንደ አለቃ የሚቀበለኝ ከሆነ ይቀበለኛል፡፡ የማይቀበለኝ ከሆነ የራሴን ይዤ እወጣለሁ፤›› በማለት በኃላፊነት ዘመናቸው እንዴት ይሠሩ እንደነበር ለማመላከት ሞክረዋል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ በቃሉ ዘለቀም ከአቶ ተክለ ወልድ ብዙ መማራቸውንና አሁን ለደረሱበት ደረጃ የአቶ ተክለ ወልድ አስተዋጽኦ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ከዮሐንስ (ዶ/ር) ጋር ብዙውን ጊዜ በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸውንና ከእሳቸውም ብዙ መማራቸውን አቶ በቃሉ አስታውሰዋል፡፡ ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚጨቃጨቁበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህም ለሚሠሩት ሥራ መልካም ውጤት ከማምጣት የተነሳ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

የፋይናንስ ኢንዱስትሪውም ሆነ ኢኮኖሚው ባለፉት 16 ዓመታት ውስጥ ትልቅ እመርታ ስለማሳየቱ የገለጹት አዲሱ ገዥ ይናገር (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የበርካታ አካላት አስተዋጽኦና ፖሊሲዎች ተደማምረው ያበረከቱ ውጤት እንደሆነ፣ ለመጣው ዕድገትና ለውጥም የባንክ ዘርፉ ትልቅ ሚና ስለተጫወተ ሊኮራ ይገባል ብለዋል፡፡ ስለዚህም የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ አመራሮች ትልቁን ድርሻ ተጫውተዋል በማለትም አሞካሽተዋቸዋል፡፡

አያይዘውም ለተገኘው ውጤት ዕውቅና ከሰጡ በኋላ፣ ኢኮኖሚው ግን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥሞታል ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ኢኮኖሚው የሚጠይቀውን አዳዲስ አሠራሮችን ታሳቢ ያደረጉ የሪፎርም ሥራዎችን በመሥራት ችግሮቹን መሻገር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹በየጊዜው በደረስንበት የዕድገት ምዕራፍ ውስጥ ችግሮች ማጋጠማቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ችግርች ለምን ተፈጠሩ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል፤›› በማለት አሳሳቢ ችግሮች እንደተደቀኑ አስታውሰው፣ ለሚታዩት ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚበጁ መፍትሔዎችን የማስመቀጥ ተግባር የአዲሱ አመራር ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነና ችግሮቹን በጋራ መፈታት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ጥሩም ‹‹አሁንም ከኢኮኖሚው ያልወጣን በመሆኑ፣ ባለንበት የበኩላችንን እናደርጋለን፤›› በማለት ዮሐንስ (ዶ/ር) ለአዲሱ ገዥ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች