Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ለ40/60 ግንባታ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ከማቅረብ ራሱን አገለለ

  የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ለ40/60 ግንባታ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ከማቅረብ ራሱን አገለለ

  ቀን:

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለሚገነባቸው የ40/60 ቤቶች የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ማቅረብ ፈተና ሆኖብኛል በሚል ምክንያት፣ ራሱን በማግለል ኃላፊነቱን ለኮንትራክተሮች ሰጠ፡፡

  የ40/60 ቤቶች ግንባታ እየተጓተተ ከሚገኝባቸው ምክንያቶች አንዱ 529 ያህል የግንባታ ዕቃዎችን ማቅረብ አለመቻል መሆኑ በምክንያትነት የቀረበ ሲሆን፣ ኢንተርፕራይዙ ዕቃ ከማቅረብ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን አምባዬ እንደገለጹት፣ የ40/60 ቤቶችን ለማግኘት የተመዘገቡ 161 ሺሕ ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 130 ሺሕ ሰዎች ሳያቋርጡ እየቆጠቡ ናቸው፡፡ 19 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ሙሉ ክፍያ ፈጽመዋል፡፡

  ‹‹ኢንተርፕራይዙ 529 የግንባታ ዕቃዎችን እያቀረበ እየቆጠቡ የሚጠባበቁ 130 ሺሕ ሰዎችን ፍላጎት ማርካት አይችልም፤›› በማለት ኢንተርፕራይዙ የደረሰበትን ውሳኔ አቶ መኮንን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መሠረት ኢንተርፕራይዙ በተያዘው በጀት ዓመት ለሚገነባቸው አሥር ሺሕ 40/60 ቤቶች የግንባታ ዕቃ እንደማያቀርብ አስታውቋል፡፡

  ኢንተርፕራይዙ የ40/60 ቤቶችን መገንባት ከጀመረ አምስት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ የቻለው ግን 1,292 ቤቶችን ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንተርፕራይዙ 38,500 ቤቶችን እየገነባ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 17,737 ቤቶች በማጠናቀቂያ ግንባታ ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

  በቅርቡ አሥር ሺሕ ቤቶችን ለመጀመር እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ሰሞኑን ባስቀመጠው ሰነድ ላይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ አራብሳ አካባቢ 8,428 ቤቶችን ለመጀመር 38 ሔክታር መሬት ተረክቧል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የተለያዩ ከፍታ ያላቸውን  54 ሕንፃዎችን ለመገንባት ኮንትራክተሮችንና አማካሪ ድርጅቶችን ለመምረጥ የጨረታ ሒደት ውስጥ ገብቷል፡፡

  አሸናፊ ሆነው ሥራውን የሚረከቡ ኮንትራክተሮች ራሳቸውን ችለው ዕቃ አቅርበው የመገንባት ጉዳይ ጠቀሜታው፣ ወይም የሚያመጣው ችግር ላይ የተባለ ነገር የለም፡፡

  ኢንተርፕራይዙ በሰነዱ ላይ ያስቀመጠው ዕቅድ እንደሚያስረዳውም አዲስ በሚጀምረው የግንባታ ሳይት ቀደም ሲል ተግባራዊ በተደረጉ ሳይቶች ያጋጠሙ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ከብረትና ከሊፍት በስተቀር ኢንተርፕራይዙ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከግንባታ ግብዓት አቅርቦት ውጪ የሚሆንበት የኮንትራት አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

  አቶ መኮንን እንደሚሉት በአጠቃላይ ከሚቀርቡ 529 ዕቃዎች ውስጥ በተለይ ስድስት የሚሆኑ የግንባታ ማጠናቀቂያ ዕቃዎች የቤት ዕድለኞች እንዲያሟሉት ይደረጋል፡፡

  ‹‹ኢንተርፕራይዙ በተለይ በክራውንና በሰንጋ ተራ ሳይቶች ሙሉ በሙሉ የማጠናቀቂያ ዕቃዎችን  ገጥሞ ቢያስረክብም፣ የቤቶቹ ዕድለኞች እነዚህን ስድስት ዓይነት ዕቃዎች ነቃቅለው በአዲስ ተክተዋል፡፡ ስለዚህ የአገር ሀብት ከማባከን እነዚህን ዕቃዎች የመምረጥና የመግጠም ሥራውን ለዕድለኞች ተትቷል፤›› ሲሉ የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...