የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ሐሙስ፣ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ከተሾሙ የመጀመርያቸውን ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቱም በፋይናንስ አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ለብቻው እንዲመክርበት ማሳሰባቸውን ተከትሎ የተካሄደ ነበር፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ሁለት ወራት ቢዘገይም ሲጠበቅ የነበረው ስብሰባ በዚህ ሳምንት ተካሄዶ በፋይናንስ ዘርፉ የሚጠቀሱ ችግሮች ተነስተውበታል፡፡ ውይይቱ እንዲዘጋጅ ያደረገው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በፋይናንስ አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ ከንግዱ ኅብረተሰብ ያሰባሰባቸውን ቅሬታዎች መሠረት በማድረግ ያጠናቀረውን መረጃ ለገዥው አቅርቧል፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ነጋዴው የሚገጥሙትን የፋይናንስ ችግሮች በሰፊው አቅርበዋል፡፡ በስብሰባው የተሳተፉ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትም ተጨማሪ ጥያቄዎችን አሰምተዋል፡፡ አቶ መላኩ ባቀረቡት ሰፊ ጥያቄ ውስጥ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ቢወስድም፣ በገንዘብ አቅርቦት በኩል የሚታየው ችግር የግሉ ዘርፍ ዋነኛው ማነቆ ሆኖ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳመለከቱት፣ በአሁኑ ወቅት በፋይናንስ ኢንዱስትሪው የሚተገበሩት ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና የአሠራር ሥርዓቶች በገንዘብ አቅርቦት ረገድ ለሚስተዋሉ ችግር ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የገንዘብ ተቋማት የማበደር አቅም መንግሥት ተግባራዊ ባደረጋቸው ሕግጋት ሳቢያ እንዲመናመን ምክንያት መሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ባንኮች የሚከተሉት የብድር ፖሊሲና የተንዛዛ አሠራር ብድር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ ማድረጉ፣ አድሏዊነት የሰፈነበት የውጭ ምንዛሪና የብድር አሰጣጥ መንሰራፋቱን ዘርዝረዋል፡፡
ከመደበኛው አሠራር በተጓዳኝ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚያስችሉ አማራጭ ዘዴዎች አለመተግበራቸው ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ድልድል ችግሮች ሳቢያ በአምራችነት የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ፣ ከብድር ውጭ ያሉ የገንዘብ ምንጮች አለመፈጠራቸው፣ የካፒታል ገበያ አለመጀመሩ፣ የተለየ ባህሪይ ላላቸው ዘርፎች የተለየ የብድር ሥርዓት ወይም ዘርፎቹ ላይ ብቻ በማተኮር የሚሠራ የገንዘብ ተቋም አለመኖር፣ በቅርቡ በገንዘብ ምንዛሪ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ በብድር የወለድ ምጣኔ ላይ የተደረገው ጭማሪ፣ ብድር ለማግኘት ቀድሞም የነበረውን ሁኔታ ይበልጥ አስቸጋሪ እንዳደረገውና ይህም በገንዘብ አቅርቦት ዙሪያ የሚታዩትን ችግሮች እንዳባባሳቸው አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡
የብድር ዕጦትና የወለድ ጫና
ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ባደረጉት ምክክር ወቅት የብድር ጉዳይ ዋነኛው ጉዳይ ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ነጋዴዎች ለሥራ ማስኬጃ ብድር ጥያቄ ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ እንደማያገኙ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ አቶ መላኩም የባንኮች የማበደር አቅም በተለያዩ ምክንያቶች እየተዳከመ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ አማራጭ ፋይናንስ የማግኛ ዘዴ ተግባራዊ ያለመደረጉ አንዱ ችግር እንደሆነም አውስተዋል፡፡ መንግሥት የአምራች ዘርፉ የሚያጋጥመውን የገንዘብ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ብሎም የኢንዱስትሪ ልማትን ለማስፋፋት በማሰብ፣ ባንኮች ከሚያበድሩት ከእያንድንዱ ብድር 27 በመቶ የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ የሚያስገድደው መመርያ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያት መመርያው የአምራች ዘርፉ የሚጋጥመውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ሲጠበቅ፣ በተቃራኒው ባንኮችን ለኪሳራና የማበደር አቅማቸው እንዲመናመን ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት እንደሚቀመጥ ተብራርቷል፡፡
በሌላ በኩል ባንኮች የኤክስፖርት ቅድመ ዕቃ መላኪያ ብድርና የሸቀጥ ንግድ የብድር አገልግሎቶች ከአጠቃላይ የብድር አቅርቦታቸው ከአሥር በመቶ እንዳይበልጥ የሚከለክል መመርያ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ገደብ ላኪዎች ከፍተኛ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት እንዲገጥማቸው ምክንያት ስለመሆኑም ተናግሯል፡፡
ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በምንዛሪ ተመን ላይ የተደረገውን ጭማሪ ተከትሎ በባንኮች የብድር የወለድ ምጣኔ ላይም ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ይሁንና በተደረገው ጭማሪ የተነሳ ባለሀብቶች ለሥራ ማስኬጃ የሚያስፈልጋቸውን ብድር ከባንኮች ለማግኘት አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥውም፣ የባንኮች የማበደርያ ወለድ መጠን ከፍ ማለቱን ያምናሉ፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅሰው የዚህን ያህል መሆኑ አግባብ ነው ብለው አያምኑም፡፡ በዚህ ዙሪያ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ የተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው ወለድ ከፍ ብሏል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት ከውጭ ምንዛሪ ለውጥ ጋር ተያይዞ ለብድር ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የገንዘብ መጠን ምን መሆን አለበት የሚለው ታሳቢ ተደርጐ የተሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አንፃር ከብድር አቅርቦት አኳያ ባንኮች ከዚህ በላይ አትሂዱ የሚለው መመርያ እንዲተገበር የተፈለገበት ዋናውና አንዱ ምክንያት ከዋጋ ግሽበት ጋር የተያያዘው ጉዳይ በተወሰነ መልኩ መልስ ለመስጠት ታስቦ ነው፡፡
በዚያ ውሳኔ መሠረት የብድር ጣሪያ የተቀመጠው በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ካለው ከኑሮ ውድነትና ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ በሰዎች ሕይወት ላይ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ለመቀነስ ታስቦ ነው፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ በብዙ መልኩ ኤክስፓርትን ለማበረታታት ነው፡፡ ይህ የሚባልበት ምክንያት አለው፡፡ አንደኛው ለውጡ እንደተደረገ የወጪ ምርት ከአንድ ወይም ከሁለት ወር በኋላ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡
ዋናው የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ በኤክስፖርት ምርቶች ላይ በሒደት ለውጥ እንዲመጣ ታስቦ መሆኑንም በማስረዳት፣ የወለድ ምጣኔው ከመቀየሩ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ክፍተቶች ዙሪያ ከባንኮች ጋር በስፋት ውይይት መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን የወለድ ተመኑ ከፍ ማለት የምንዛሪ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል በግልጽ የተናገሩት ይናገር (ዶ/ር)፣ የብድር አቅርቦቱ የማበደሪያ የወለድ ተመናቸው እንዲገፉ ያደረጋቸው ይመስለኛል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እስከ 20 በመቶ ድረስ ወለድ የሚከፈበት ብድር መኖሩን በማስታወስ፣ የወለድ መጠኑን ይህንን ያህል አድርጉ በማለት ባንኮች ማስገደድ እንደማይችልም ጠቁመዋል፡፡ ወደዚህ እንዳይገቡ ለማድረግ ግን ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንችላለን ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሌሎች አማራጮች ያሉዋቸውን አልጠቀሱም፡፡ ሆኖም ይህንን የተለጠጠ የብድር ወለድ ምጣኔ ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ዙሪያ ከተሰጠው አስተያየት ዙሪያ ከሚወሰዱ የሪፎርም ሥራዎች አንዱ በዚህ ረገድ ያለውን የወለድ ምጣኔ ለማውረድ የሚሠራ ሥራ ነው ማለታቸውን ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል፡፡ አያይዘውም በ20 በመቶ ወለድ ብድር ወስዶ ቢዝነሱ እንዴት አዋጭ እንደሚሆን የሚያስቸግራቸው መሆኑን የገለጹት ገዥው፣ ይህ የወለድ ዕድገት ዋጋ ኅብረተሰቡ ላይ ጫና መፍጠሩ እንደማይቀርና በኅብረተሰቡ የኑሮ ውድነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አስታውቀው፣ ይህ እንዳይሆን ወደፊት ይፈተሻል በማለት ጥቅል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የብድር አመላለስና ችግሮቹ
አቶ መላኩ ዝርዝር ካቀረቧቸው ችግሮች በተጨማሪ፣ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትም በየፊናቸው ችግሮቻቸውን ለብሔራዊ ባንክ ገዥው አሰምተዋል፡፡ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ከዋና ዋናዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ የወሰዱትን ብድር በወቅቱ ለመክፈል እንደተቸገሩ ያስታወቁ አምራቾች በርካታ ነበሩ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱም ይህንኑ ጉዳይ በጉልህ አንስቶታል፡፡ አምራቾች ብድር በወቅቱ ላለመክፈላቸው አንዱና ትልቁ ምክንያት እንደሆነ የጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቀድሞ በ8.5 በመቶ ወለድ ያቀርብ የነበረውን ብድር ወደ 12 በመቶ ከፍ ማድረጉን ነው፡፡ አደጋ ውስጥ የገባ ወይም ሳይከፈል የቆየ ውዝፍ ብድር ያለባቸው ተበዳሪዎችም የሦስት በመቶ መቀጫ እንዲከፍሉ መገደዳቸው ሌላው መንስዔ ነው፡፡
በተከሰተው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ፋብሪካዎች በቂ ጥሬ ዕቃ ሊያስገቡ ባለመቻላቸው፣ በሙሉ አቅማቸው ማምረት አለመቻላቸው ተዳምሮ ፈተና ላይ መውደቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ የሚያስፈልጋቸውን ያህል የገንዘብ አቅርቦት ባለማግኘታቸውም ጭምር በአግባቡ ማምረትም መሥራትም በተሳናቸው ወቅት፣ ከባንክ የወሰዱት ብድር ላይ የሚታሰበው ወለድ እየጨመረ መሄዱ በተወዳዳሪነታቸው ትልቅ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ፣ በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር በኩል የቀረበውን አቤቱታ በዋቢነት የጠቀሱት አቶ መላኩ፣ በብድር አመላለስ ሒደት የሚያጋጥማቸው ችግር አሳሳቢነቱ እየሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ብድር መመለስን ጋር አስቸጋሪ ያደረገው ሌላው ሰበብ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከባድ ተፅዕኖ ካሳረፈባቸው የኢኮኖሚው ዘርፎች መካከል ቱሪዝም ዋነኛው እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ችግሩ በስፋት ተከስቶ ከነበረባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜኑን የአገሪቱን ክፍል አውስተዋል፡፡ በሆቴልና በቱሪስት አገልግሎት መስጫ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ በተከሱት የፀጥታ ችግሮች ሳቢያ ሥራቸውን በአግባቡ ማካሄድ ተስኗቸው ቆይተዋል፡፡ በዚህም ከተለያዩ የግል ባንኮች የተበደሩትን ገንዘብ በወቅቱ ለመክፈል ተቸግረው ይገኛሉ፡፡ በጎንደርና አካባቢዋ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለንብረቶች ለኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያቀረቡትን ቅሬታ አቶ መላኩ አቅርበዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከነጋዴዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከብድር አመላለስ ጋር ተያይዞ በርካታ አቤቱታዎች እንደሚነሱ ያስታወሱት ይናገር (ዶ/ር)፤ ‹‹ብድር ተበላሽቷል፣ ምሕረት ይደረግልን፤›› የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ባንክ ሙያዊነትን የተከተለ አሠራር እንደሚከተል ጠቅሰው፣ የንግድ ኅብረተሰቡም ብድሩን በአግባቡ የመመለስን ባህል እንዲያዳብር አሳስበዋል፡፡ ከብድር ጋር ተያይዞ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመርመርና ለመፍታት ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የምንመለከታቸው ጉዳዮች ስላሉ ጊዜው ሲደርስ እናሳውቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን የተወሰደውን ብድር በአግባቡ መመለስ እንደማይታለፍ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
የብድር አመላለስና ፍትሐዊነቱ
የብድር አመላለስ ላይ የተነሳው ሌላው ጉዳይ ፍተሐዊነቱን የተመለከተ ቢሆንም፣ ይናገር (ዶ/ር)ም አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ የብድር አመላለስን የሚመለከተው መመርያ ይታያል ካሉ በኋላ፣ ለሁለትና ሦስት ጊዜ መመለስ ያልቻለ በምን አግባብ ይስተናገዳል የሚለው ወደ ፊት በሚወጣ መመርያ ይፈታል ብለዋል፡፡
የባንኩ ገዢ በዚህ መድረክ ደጋግመው የገለጹት ነገር ቢኖር፣ የተለያዩ የማሻሻያ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱና ችግር አለባቸው የተባሉ መመርያዎችም መታየት መጀመራቸውን ነው፡፡ ‹‹በተቻለ መጠን እንደ ባንክ ገዥነቴ የተመቻቸ የፋይናንስ ዘርፉ፣ ሁሉም የሚሮጥበት የተመቻቸ ሜዳ እንዲሆን የማድረግ አሠራር መፍጠር ይኖርብኛል፡፡ ትልልቅ ባንኮችም ሆኑ ትናናሾቹ የማንም ይሁኑ እኩል ሜዳ እንዲኖራቸው በአሠራር ዓይተን የሚፈተሹ ነገሮች ይኖራሉ፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች በጎ አሠራሮችም እንደሚዘረጉ ያስታወቁት ገዥው፣ ባንኮችም ጥንቃቄ ሊያደርጉባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከሕግ ወጣ ያለ ሥራ ካለ ተጠያቂነት እንደሚኖር ጭምር አሳስበዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ቶጎ ጫሌ ላይ ያላቸው ቅርንጫፎች ለምን እንደተከፈቱ ጭምር እናጣራለን በማለት ጭምር ማስጠንቀቂያ የሰጡበትም መድረክ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ለሚፈጠሩ ስህተቶች ምሕረት የሚደረግባቸው እንዳሉ ሁሉ ምሕረት የማይደርግባቸው ጉዳዮች ስለሚኖሩ፣ በንፅህናና በቅንነት መሥራት አዋጭ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምሬት
በንግድ ምክር ቤቱም ሆነ በነጋዴዎች ምሬት ያዘለ አቤቱታ የቀረበበት ሌላው ጉዳይ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከዚሁ ጋር የተያያዘ ችግር ነበር፡፡ ከነጋዴዎች የተሰማው አቤቱታ በውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ላይ ትልቅ ችግር መኖሩን የሚያመላክት ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘታቸው በሥራቸው ላይ የተፈጠረውን ችግር ገልጸዋል፡፡ እጥረት አለ በሚባልበት ወቅት በጎን ምንዛሪ የሚሰጣቸው ኩባንያዎች እንዳሉ የገለጹ ነጋዴዎች እነዚህ ‹‹የጡት አባት›› አላቸው ማለት ነው ወይ በማለት ጭምር ምሬታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ በድልድል የሚሰጥበት አሠራር በተግባር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለማዳን አስተዋጽኦ ለሚያበረክቱ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት አልሰጠም የሚለው ስሞታም ተጠቅሷል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የተጀመሩ ግንባታዎችን ማጠናቀቅ ትልቅ ፈተና ስለመሆኑ ተነስቷል፡፡
በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎችና ምሬት አዘል አቤቱታዎች የብሔራዊ ባንክ ገዥው በሰጡት ምላሽ፣ እጥረቱ የተፈጠረባቸውን ምክንያቶች አብራርዋል፡፡ መንግሥት በተለይ ከግብር ውጤቶች ሊያገኝ ያቀደው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተፈለገው መጠን አለመገኘቱ ለችግሩ አንደኛው ምክንያት ሲሆን፣ ወደ ምርት እንደሚገቡ የሚጠበቁ የስኳር ፕሮጀክቶች መጓተትም ሌላው ምክንያት እንደነበር በሰፊው አብራርተዋል፡፡
ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እስከ አንድ ዓመት ወረፋ ለመጠበቅ ተገደናል ማለታቸውን የተቀበሉት የባንኩ ገዥ፣ አሁንም ቢሆን ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያ በወረፋ መሰጠቱ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የሚተኩ አምራቾች ትኩረት እንደሚጣቸውም ገልጸዋል፡፡
የካፒታልና የአክሲዮን ገበያ
ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አለማቋቋሟን የሚነቅፉ አስተያየቶች ሲደመጡ ቆይተዋል፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥም ይኼው የካፒታል ገበያ ጉዳይ ተካትቶ ነበር፡፡ ከተሳታፊዎችም ጥያቄው ቀርቧል፡፡
በበርካታ አገሮች የካፒታል ገበያ በመኖሩ፣ በገንዘብ አቅርቦት ረገድ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ዕገዛ ቢያበረክትም፣ በኢትዮጵያ ግን የካፒታል ገበያን እስካሁንም ድረስ ማቋቋም አልተቻለም፡፡ ገበያውን የሚመራ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ስለመሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
የአክሲዮን ገበያዎችን በተለይም የቦንድ ገበያን በተመለከተ ጥናት መካሄዱን መጠናቱን ይናገር (ዶ/ር) አስታውቀው፣ አዲሱን የኃላፊነት ቦታ ከተረከቡ ወዲህም ከሦስት ትልልቅ ጥናቶች ውስጥ ሁለቱን እንደተመለከቱና ሐሳቡ ጥሩ ሆኖ እንዳገኙት አመልክተዋል፡፡ ‹‹የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ወደዚያ መሄዳችን የማይቀር ነው፡፡ አጥረን ልንኖር አንችልም፡፡ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አስገዳጅ ሁኔታዎች እየመጡ ነው፡፡ ስለዚህ ወደዚህ የምንገባ ከሆነ አንዳንድ ለውጦች ያስፈልጉናል፡፡ በተለይ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጥ ያስፈልገዋል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹የካፒታል ገበያም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን ግልጽ ሆነን እናያለን፡፡ ይጠቅማል፣ አይጠቅምም የሚለውን በግልጽ እናያለን፡፡ ሐሳቡ እየተነሳ ያለው ለአገር ይጠቅማል ከሚል ነው፤›› በማለት ያብራሩት የብሔራዊ ባንክ ገዥው፣ ‹‹ሐሳቡ ታይቶ የሚጠቅም ከሆነ እንሄድበታለን፤ ካልጠቀመ ግን እንዲቆይ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡
ኮንትሮባንድ
በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርምር ተቋም መረጃ መሠረት፣ ጂቡቲዎች ዓምና ብቻ 2.5 ሚሊዮን የቀንድ ከብት ወደ ውጭ ልከዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን 750 ሺሕ ብቻ ልካለች፡፡ ይህ ግን የኢትዮጵያ የቀንድ ከብቶች በኮንትሮባንድ በመሸጣቸው እንጂ ቁጥሩ ከፍተኛ ይሆን እንደነበር በመጥቀስ፣ አቶ መላኩ ችግሩን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ መንግሥት ኮንትሮባንድና ኮንትሮባንዲስቶችን ለመከላከል መነሳቱን ገዥው ገልጸዋል፡፡
ልማት ባንክ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር አሰጣጥ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና ትችቶች ቀርበው ነበር፡፡ ብድር ማግኘት ከባድ ነው ተብሏል፡፡ ከእነዚህ ባንኮች ብድር አናገኝም መባሉን ትክክል መሆኑን የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ አያይዘውም የተሰጠውም ብድር ቢሆን አላማረበትም በማለት ለእርሻ ተብሎ ተሰጥቶ ሜዳ ላይ የቀረውን ብድር በአስረጅነት አስታውሰዋል፡፡
በቀጣዩም ዕለት 6.2 ቢሊዮን ብር ብድር ለእርሻ ተሰጥቶ እንዴት እንደሚመለስ ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡ በእርሻ ጥሩ የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ በኔትዎርክ ተሳስረው ይህንን ብድር ወስደው ባንኮችን ችግር ላይ የሚጥሉ ሰዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ባለው ተግባር የተሳታፊም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የልማት ባንክ ብድርን በሚመለከት ከአሁን ወዲያ በጣም በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነገር ነው፡፡ በጅምላ በኔትዎርክ የሚኖር የብደር አሰጣጥ በዚህ አገር እንዳይኖር ብሔራዊ ባንክ ያለ ርኅራኄ ይታገላል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሁን መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ እኛ አመራሮች ተነጋግረን ከብድር አሰጣጥ አኳያ እንዴት መሠራት እንዳለበትና ችግሮቹ ተፈተውለት ወደቀደመው አሠራር እንዴት መግባት ይችላል የሚለው ነገር መታየት አለበት፡፡ ‹‹በእኔ እምነት ባንኩ ለውጥ ያስፈልገዋል፤›› ያሉት ገዥው፣ ይኼ ባንክ መንግሥት በሚለግሰው ገንዘብ ሁሌ እንዲህ ሆኖ መቀጠል የለበትም በማለት የባንኩ አሠራር ለውጥ እንደሚደረግበት ተናግዋል፡፡