Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዶላር ምንዛሪ በባንክና በጥቁር ገበያው መሳለመሳ እየሆነ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወደ ውጭ የሚሸሽ ገንዘብም እየታየዘ ነው

በባንኮችና በጥቁር ገበያው መካከል የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት እየወረደ በመምጣት በአሁኑ ወቅት በሳንቲሞች ደረጃ ተወስኗል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በጥቁር ገበያውና በመደበኛ ባንኮች በኩል የአንድ ዶላር ምንዛሪ ልዩነት ከሰባት እስከ አሥር ብር ልዩነት እንደነበረው ይታወሳል፡፡  

በቅርቡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጫን ያለ ማስጠንቀቂያ ከሰጡበት ቀን ጀምሮ፣ በጥቁር ገበያውና በባንኮች መካከል የነበረው የምንዛሪ ልዩነት እየጠበበ መጥቶ በዚህ ሳምንት አጋማሽ፣ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ ከ28 ብር በታች መመንዘሩ ታውቋል፡፡ የምንዛሪው ይበልጥ እየወረደ በመምጣቱ እስከ 20 ሳንቲም ዝቅ ብሎ መታየቱም ተሰምቷል፡፡

ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በአብዛኛው በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ እስከ 27.80 ብር ጭምር እየተመነዘረ መሆኑ፣ ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ ልዩነትን በከፍተኛ ሁኔታ አጥብቦታል፡፡

ባለፈው ረቡዕ ባንኮች አንድ ዶላር እየመነዘሩ ያሉት 27.23 ብር ነው፡፡ በዘርፉ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የተለያዩ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች በተለይ ባለፉት ሁለት ቀናት ከዕለታዊ በተለየ ሁኔታ ወደ ባንክ መጥተው የሚመነዝሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጠውልናል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በሳምንቱ ቀናት ውስጥ ወደ ባንኮች የገባው የውጭ ገንዘብ ብዛት ይበልጥ እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጠዋል፡፡ መንግሥትም ኅብረተሰቡ እያሳየ ላለው ቀናነት ምሥጋና አቅርቧል፡፡ ከሰሞኑ በጥቁር ገበያ የዶላር የምንዛሪ ዋጋ እየወረደ መምጣቱ ያለውን አንደምታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎችና ኢኮኖሚስቶች እንደገለጹት፣ የምንዛሪው ልዩነት ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ መምጣቱ ዜጎች በእጃቸው የሚገኙ የውጭ ገንዘቦችን ወደ ባንክ እንዲያመጡ ገፋፍቷቸዋል፡፡

በተለይ ከየት አመጣችሁ የሚል ጥያቄ የሌለባቸውና በነፃነት ወደ ባንክ እንዲያስገቡ መፈቀዱም፣ በነፃነትና በሕጋዊ መንገድ የውጭ ገንዘቦችን በባንክ በኩል እንዲመነዝሩ አስችሏቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከውጭ ሕጋዊ መንገድ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ እየጨመረ እንደሚመጣ እምነት ያለ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሰጡትን ማሳሰቢያን በመሥጋት እያስገቡ ያሉ እንደሚኖሩም ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም በዚህ ሳምንት በርካታ ሰዎች ወደ ባንክ በመምጣት ዶላርና ሌሎች የውጭ ገንዘቦችን በባንክ እየመነዘሩ ስለመሆኑ የገለጹት ያነጋገርናቸው አንድ የግል ባንክ የሥራ ኃላፊ፣ እስከ ዛሬ በዚህን ያህል ደረጃ የውጭ ምንዛሪ የመነዘሩበት ጊዜ እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ዕርምጃ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን ከፍ እንደሚያደርገው የጠቀሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዓውት ተክሌ፣ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን ለማሟላት ዕገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ አሁን ወደ ባንክ እየሄዱ ያሉ ሰዎች ጥቁር ገበያው ስለቀነሰ ብቻ ሳይሆን በባንክ መመንዘር አገርን እንደሚጠቅም በማሰብ ጭምር ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማሟላት ዜጎች ባንክ በመሄድ መመንዘር፣ ከውጭ ያሉ ዜጎችም በባንክ በኩል በመላክ ለውጭ ምንዛሪ ዕድገቱ አስተዋጽኦ ቀላል ባይሆንም ዘላቂ መፍትሔ ያለመሆኑንም ሳይጠቀሙ አላለፉም፡፡

ለዘላቂ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በዋናነት መታሰብ ያለበት የውጭ ንግድ ዕድገትና ከተለያዩ ዘርፎች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሳደግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ከአንዳንድ ባንኮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሥር ሺዎች የሚገመት ዶላር መመንዘራቸውን ነው፡፡ የውጭ ገንዘቦች ብቻም ሳይሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገር ውስጥ ገንዘብም ወደ ባንኮች ካዝና እየጎረፈ ስለመሆኑ ቢነገርም፣ በዚያው ልክ በጠረፍ አካባቢዎች ገንዘብ የማሸሽ እንቅስቃሴው መበራከቱን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

በሳምንቱ ማገባደጃ ወቅት የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ መሠረት፣ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ብቻ ከ20,800 ዶላር፣ 9000 ድራሃም፣ 800 ዩሮ፣ 1800 ሳዑዲ ሪያል መያዙን አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በድንበር አካባቢ በምትገኘው ቶጎ ውጫሌ አካባቢ 100 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር፣ በኤርፖርት በኩልም 35 ሺሕ ብር ወደ ውጭ ሊወጣ ሲል መያዙን አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ወደ ውጭ ሊሸሽ የነበረ የአገር ውስጥና የውጭ ገንዘብ እየተያዘ ቢሆንም፣ የማሸሹ ተግባር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ሳትነግሩን እንዳትሉ›› በማለት በቅርቡ የሚከናወን ኦፕሬሽን አለ በማለት በቤት ውስጥ የተከማቸ ገንዘብ ያላቸው ዜጎች በቶሎ ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ከማስጠንቀቃቸው ጋር ስለመያያዙ የሚያረጋግጡ ፍንጮች አልተገኙም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች