Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንገዶች ባለሥልጣንና በኢትዮ ቴሌኮም የአመራሮች ለውጥ አደረጉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንና በኢትዮጵያ ቴሌኮም አመራሮች ላይ ለውጥ አደረጉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲያገለግሉ የሾሙዋቸው አቶ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ አዲሱ ኃላፊነታቸውን ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ይረከባሉ፡፡ በአቶ ሀብታሙ የተተኩት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አርዓያ ግርማይ ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነዋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) ወደ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ሲዛወሩ፣ በምትካቸው ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ተተክተዋል፡፡ ወ/ት ፍሬሕይወት አዲሱን ኃላፊነት ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ይረከባሉ፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች አራተኛውን በጀት በማግኘት የሚታወቀውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ የተሰየሙት አቶ ሀብታሙ፣ ቀደም ብሎ በባለሥልጣኑ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ ካገኙ በኋላ፣ በሙያቸው ከ14 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ አብዛኛውን የሥራ ዘመናቸውን ያሳለፉትም በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንን ከ16 ዓመታት በላይ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ባገለገሉት አቶ ፈቃዱ ኃይሌ (ኢንጂነር) ምትክ ከሁለት ዓመት በፊት የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እስከተሰየሙበት ጊዜ ድረስ፣ የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲቋቋም የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ሦስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በማጣመር እንዲቋቋም የተደረገውን ግዙፉን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ ተመድበው ለአጭር ጊዜ ሠርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙትም በኮርፖሬሽኑ ውስጥ በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ በነበረበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡ አቶ ሀብታሙን በመተካት ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማን እንደሚሾም አልታወቀም፡፡

በአቶ ሀብታሙ የተተኩትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የተሾሙት አቶ አርዓያ ግርማይ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የተሾሙት፣ በቅርቡ ከእስር የተለቀቁትን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልን በመተካት ነበር፡፡ አቶ አርዓያ ከዚህ ኃላፊነታቸው ቀደም ብሎ በሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ የኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት ኃላፊ በመሆን በመሥራት ላይ ነበሩ፡፡ ለባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተርነት የተሾሙትም ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመሥራት ላይ ሳሉ ነበር፡፡

 በ1987 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ በሲቪል ምሕንድስና የተመረቁት አቶ አርዓያ፣ ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀሉት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ በነበሩበት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው፡፡

ለጥቂት ዓመታት በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት በተለያዩ የሥራ መደቦች ከቆዩ በኋላ፣ በግል ኩባንያዎች ውስጥ ሲሠሩ ቆይተው ተመልሰው ባለሥልጣኑን በዋና ዳይሬክተርነት የመምራት ዕድል አግኝተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) ከኃላፊነታቸው ተነስተው፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮምን ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በዋና የውስጥ ኦዲተርነት የተቀላቀሉት አንዷለም (ዶ/ር)፣ ከፍራንስ ቴሌኮም ላይ ማኔጅመንቱን በመረከብ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ድርጅቱን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡

እሳቸውን ተክተው ኢትዮ ቴሌኮምን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት ደግሞ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው፡፡ ወ/ት ፍሬሕይወት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመርያ ዲግሪ እንዳላቸው፣ እንግሊዝ ከሚገኘው ኦፕን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪ ማግኘታቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም ሕዝብ ግንኙነት ክፍል የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ አዲሷ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በቴሌኮም ዘርፍ ለስምንት ዓመታት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂውን ከመምራት አንስቶ፣ እስከ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ድረስ ማገልገላቸውን መረጃው ያመለክታል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ በግሉ ዘርፍ የዳክሳ አይቲ ቴክኖሎጂ ኩባንያ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ በተጨማሪም አዳዲስ ኩባንያዎችን በማቋቋምና ወደ ሥራ በማስገባት አገልግሎት መስጠታቸውን ከመረጃው መረዳት ተችሏል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሽግሽግና ሹምሽር እየተደረገ መሆኑ ይሰማል፡፡ 

በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወሰነው መሠረት ሙሉ ለሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዞታ ከሚዛወሩ የመንግሥት ድርጅቶች መካከል አንዱ ኢትዮ ቴሌኮም መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች