Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአቶ ግርማ ብሩ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ሆኑ

አቶ ግርማ ብሩ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ሆኑ

ቀን:

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብንክ ቦርድ ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተሰየሙ፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥን ጨምሮ ሦስት የመንግሥት ኃላፊዎች፣ በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ ከተሰየሙት አቶ ግርማ በተጨማሪ፣ ባንኩን በቦርድ አባላት እንዲያገለግሉ ከተመረጡት ውስጥ የቀድሞ የባንኩ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ይገኙበታል፡፡

አቶ ተክለ ወልድ በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከተተኩ በኋላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡

ብሔራዊ ባንክን ይበልጥ ለማሳደግ እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች አንዱ ማሳያ ነው በተባለለት የአዳዲስ ቦርድ አባላት ስያሜ፣ በቅርቡ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አቶ እዮብ ተካልኝም የቦርድ አባል ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ለብሔራዊ ባንክ የቦርድ አባልነት የተመረጡ ሌላው ሹም ሲሆኑ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው ቦርድ ውስጥ አገልግለዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክን የቦርድ አሰያየምን በተመለከተ በወጣው ድንጋጌ መሠረት፣ የባንኩ ገዥና ምክትል ገዥ ቀጥታ የቦርድ አባል ይሆናሉ፡፡ በዚህም መሠረት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እና ምክትላቸው አቶ በቃሉ ዘለቀ በአዲሱ የቦርድ አባላት ስብስብ ውስጥ ተካተዋል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ብሩ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡

አቶ ግርማ በቅርቡ በጡረታ ከመሰናበታቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ ሰብሳቢ ተደርገው መመደባቸው ይታወሳል፡፡ የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በኋላም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ከነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት በጡረታ ከተገለሉ በኋላ፣ አሁን የብሔራዊ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ መደረጋቸው ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...