ኔክሰስ ሆቴል በ410 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ 85 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሕንፃ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃቱን አስታወቀ፡፡ ሆቴሉ በሁለት ምዕራፍ ያካሄደው ኢንቨስትመንት ከ560 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነና የመኝታ ክፍሎቹንም ወደ 115 እንዳደረሰ አስታውቋል፡፡
ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በተሰጠ መግለጫ ወቅት እንደተገለጸው፣ የሆቴሉ የማስፋፊያ ግንባታ ነባሩን ባለአራት ኮከብ ሆቴል ወደ አምስት ኮከብ ለማሳደግ እንደሚያግዘው ተጠቅሷል፡፡
የሆቴሉ አማካሪና አደራጅ፣ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች የዘርፍ ማኅበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዜናዊ መስፍን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹የቀድሞው ሆቴል በባለአራት ኮከብ ደረጃ የነበረ ሲሆን፣ አዲሱ ማስፋፊያ ግን ወደ አምስት ኮከብ ያደርሰዋል፤›› ብለዋል፡፡ ሆቴሉ በጠቅላላው 85 የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት፣ ከ15 እስከ 450 ታዳሚዎችን የሚያስተናግዱ የስብሰባ አዳራሾች አሉት፡፡ በተጨማሪም ሆቴሉ እንደ እንግዶቹ ፍላጎት የሚከፈትና የሚዘጋ መዋኛ ገንዳ በመገንባት ለሆቴል ኢንዱስትሪው ለየት ያለ አገልግሎት ማስተዋወቁን አቶ ዜናዊ ገልጸዋል፡፡
የኔክሰስ ሆቴል ባለቤት አቶ ዳዊት ገብረ ጻዲቅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሆቴሉ ግንባታ በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ሳቢያ መጠናቀቅ ከሚገባው ጊዜ ተጓትቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ችግር ሆኖ የሚገኘው የሠራተኞች ፍልሰት ለሆቴላቸው ፈተና እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የተሰፋላቸውን የደንብ ልብስ እንኳ ሳይለብሱ በመጡበት እግራቸው የሚለቁ ሠራተኞች እንደተበራከቱ ጠቅሰው፣ ይህ ችግር መላ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኔክሰስ ሆቴል በአንበሳ ጋራዥ ፊት ለፊት በሚገኘው ቦታ የመጀመርያ ግንባታውን በ150 ሚሊዮን ብር በማካሄድ፣ በ2004 ዓ.ም. ለአገልግሎት ማብቃቱን አስታውሷል፡፡ ሁለተኛውን የማስፋፊያ ግንባታ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያካሄድ እንደቆየና በ2010 ዓ.ም. እንዳጠናቀቀ አስታወቆ፣ በጠቅላላው ከ560 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ባደረገበት የሆቴል ፕሮጀክቱ 115 የመኝታ ክፍሎች ያሉትን የሕንፃ ግንባታ ከእነሙሉ የሆቴል መገልገያዎቹ አሟልቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን አስታውቋል፡፡