የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2010 ዓ.ም. የሰኔ ወር 1.9 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ከ30 ሺሕ ቶን በላይ ምርቶችን አገበያይቷል፡፡ ይህ የግብይት አፈጻጸም ከሚያዝያና ከግንቦት ወራት ያነሰ ሆኗል፡፡
ምርት ገበያው በሚያዝያ 2010 ዓ.ም. 2.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ያገበያየ ሲሆን፣ ባለፈው ግንቦት ወርም ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ማገበያየቱ ይታወሳል፡፡ የሰኔ ወር ግብይቱ ግን በመጠንም ሆነ በዋጋ ከቀደሙት ወራት ያነሰ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
እንደ ምርት ገበያው መረጃ ከሆነ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ 2010 ዓ.ም. በ20 የግብይት ቀናት 21,347 ቶን ቡና፣ 6,479 ቶን ሰሊጥ፣ 2,285 ቶን ነጭ ቦሎቄና 410 ቶን ማሾ በ1.9 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡
በሰኔ ወር ግብይት ከተፈጸመባቸው ምርቶች ቡና በግብይት መጠን የአጠቃላይ ግብይቱን 70 በመቶ እንዲሁም፣ በግብይት ዋጋ 82 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ከግንቦት ወር ሲነጻጸር የቡና ግብይት በመጠን የ27 በመቶና በዋጋ ደግሞ የአሥር በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ዓመት ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 0.56 በመቶ ቢቀንስም፣ በዋና 24 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡
በቡና ግብይት ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የግብይት መጠኑን 64 በመቶና የግብይት ዋጋውን 66 በመቶ በመሸፈን ቀዳሚ ሲሆን ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ ቡናና ስፔሻሊቲ ቡና ይከተላሉ፡፡ በዚህ መሠረት 13,159 ቶን ያልታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ992 ሚሊዮን ብር የተገበያያ ሲሆን፣ ያልታጠበ የነቀምት ቡና በዘርፉ 34 በመቶ የግብይት መጠን በመያዝ ቀዳሚ ነው፡፡ በወሩ 527 ቶን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የታጠበ ቡና በ37 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ 5,346 ቶን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ቡና 295 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡
በሰኔ 2010 ዓ.ም. 2,342 ቶን ስፔሻሊቲ ቡና በ231 ሚሊዮን ብር ግብይት ተፈጽሞበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 653 ቶን ያልታጠበ ስፔሻሊቲ ቡና በ82 ሚሊዮን ብር እንዲሁም 1,689 ቶን የታጠበ ስፔሻሊቲ ቡና በ149 ሚሊዮን ብር እንደተገበያየም ይኸው መረጃ ያስረዳል፡፡
በወሩ 6,479 ቶን ሰሊጥ በ2,976 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ በዚህም ነጭ የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ የግብይቱ መጠን 79 በመቶና በዋጋ ደግሞ 80 በመቶ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር አማካይ የሰሊጥ የግብይት ዋጋ በ97 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የሰሊጥ ግብይትን የሚያሳዩ የቀዳሚዎቹ ወራት መረጃ በሰኔ ወር የተመዘገበው አነስተኛ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
በሰኔ ወር 2,285 ቶን ነጭ ጠፍጣፋና ድቡልቡል ቦሎቄ በ35 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ድቡልቡል ነጭ ቦሎቄ የግብይቱን መጠንና ዋጋ 99 በመቶ በመሸፈን ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅትም ጋር ሲነጻጸር የግብይት ዋጋው በ23.5 በመቶ፣ የግብይት መጠኑ በስድስት በመቶ ጨምሯል፡፡
እንዲሁም 410 ቶን አረንጓዴ ማሾ ለግብይት ቀርቦ በስምንት ሚሊዮን ብር ተሽጧል፡፡ ካለፈው ወር አማካይ ዋጋ ሲነጻጸር የ33.5 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡
በ2010 ዓ.ም. በተለይ የጥጥ ግብይት ከቀደመው ዓመት የበለጠ ግብይት የተፈጸመበት ከመሆኑ አንፃር፣ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ቢባልም መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን የታሰበውን ያህል አለማስገኘቱን ነው፡፡