Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርየ50ኛ ዓመታት የደንበኝነት ቁርኝት

የ50ኛ ዓመታት የደንበኝነት ቁርኝት

ቀን:

ወላጅ አባታችን በጥንቃቄ አስቀምጦት የነበረውን የተለያዩ ሰነዶችን ያቀፈውን አሮጌ ቦርሳ አንስቼ በውስጡ ያሉትን ዘመን የጠገቡ ወረቀቶችንና ደረሰኞችን ሳገላብጥ አንድ ወረቅ ትኩረቴን ሳበው፡፡ ወረቀቱ አባታችን አቶ ውብሸት ጀማነህ በ1958 ዓ.ም. ከመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት ጋር መብራት ለማስገባት የተዋዋሉበት ውል ነው፡፡ አባቴና መብራት ኃይል ከተዋዋሉ ከ2008 ዓ.ም. ልክ 50 ዓመት ደፈነ፡፡ የዛሬ 50 ዓመት የተተከለው ቆጣሪያችን እስካሁን ድረስ ቁልጭ ብሎ አገልግሎት እየሰጠን በመገኘቱ አስደንቆኛል፡፡

ዛሬ ላይ መብራት ኃይል እጅግ በርካታ ደንበኞች ያሉት፣ ከፍተኛ ሥራ የሚሠራ ግዙፍ ተቋም በመሆኑ በደንበኞቹ ብዛትና በሚፈለግበት ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ውጥረት ሳቢያ ከደንበኞች ጋር በየጊዜው እሰጥ አገባ ውስጥ ሲዋልል ይስተዋላል፡፡ አልፎ ተርፎም በጣም በርካቶች ድርጅቱን ሲያማርሩት ይሰማል፡፡ ይታያል፡፡ ምንም እንኳ ለዚህ ወቀሳና ምሬት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ቀደም ሲል እኔ የማውቀው የመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት የተመሰገነ፣ በአርዓያት የሚጠቀስ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡

በ50 ዓመታት ደንበኝነታችን ብዙ የማስታውሳቸው ገጠመኞች አሉ፡፡ ትዝ ከሚሉኝ የድርጅቱ አሠራሮች መካከል የመብራት ሒሳብ የሚሰበስቡ ሠራተኞች በየወሩ የምንከፍላትን ሦስት ወይም አራት ብር ወይም 2.50 ብር ባጋጣሚ ለጊዜው ሳይኖር ከቀረና ካልተከፈለ ከገንዘብ ሰብሳቢዎቹ የሚሰጠን አንድ ቀይ የአደጋ ምክልት ያለበት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሚል የተጻፈበት ወረቀት ነበር፡፡ በነጋታው አራት ኪሎ፣ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ ላይ በስተግራ በኩል በነበረው ሕንፃ ሥር የመብራት ኃይል ቢሮ የዛሬው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሄደን እንከፍል ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ እዚያች የመብራት ኃይል ቢሮ ሄጄ መክፈሌን አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬ ያ ቀዩ የመብራት ኃይል ማስጠንቀቂያ አለ እንዴ? አይመስለኝም፡፡ ሌላው ደግሞ በ70ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ይመስለኛል አባታችን ሥራ ሄዶ፣ እናታችን ገበያ ወጣ ብላ ነበር፡፡ እኔም ትምህርት ቤት ሄጄ ስለነበርና ትንሿ እህቴም ከጓደኞቿ ጋር ስትጫወት የመብራት ሒሳብ ሰብሳቢ ይመጣና ቀዩን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷት ይሄዳል፡፡ እህቴ ጠረጴዛ ላይ በሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትከተዋለች፡፡ ያ የማስጠንቀቂያ ወረቀት እዚያው ይረሳና የመብራት ሒሳብ ሳይከፈል ይቀራል፡፡ ከሳምንት በኋላ የመብራት ኃይል ገመድ ቆራጮች ይመጡና መብራታችንን ምሰሶ ላይ ወጥተው ሲያቋርጡት ሁላችንም ደነገጥን፡፡ አባታችን በምን ምንክንያት ነው የሚቆረጥብኝ? በማለት ተቆጣ፡፡ ሠራተኞቹም ከሳምንት በፊት ያንን የአደጋ ምክልት ያለበትን የማስጠንቀቂያ ወረቀት መስጠታቸውን አስረዱ፡፡ ማስጠንቀቂያ ወረቀቱ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ካልተከፈለ ያለተጨማሪ ማስጠንቀቂያ መብራቱን እናቋርጣለን ይላል፡፡ ከዚያም በሕግ እንጠይቃለን የሚልም ተጨምሮበታል የሚለውን ደንብ ተከትለው መምጣታቸውን ተናገሩ፡፡ ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጠን አባታችን ለመከራከር ቢሞክርም፣ እህቴ ወረቀቱን ተቀብላ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማስቀመጧን ተናገረች፡፡ አባታችን ተንደርድሮ ቤት በመግባት መጽሐፍ ቅዱሱን ሲያገላብጥ እውነትም ከሳምንት በፊት የተሰጠን ቀዩ ማስጠንቀቂያ አለ፡፡ እህቴን ከተቆጣት በኋላ በነጋታው የቅጣቱን 15 ብር ከፍሎ መብራታችን ወዲያውኑ ተቀጠለልን፡፡

እንደ ሦስተኛ ገጠመኝ የማስታውሰው በደርግ ጊዜ የውጭ መብራት ማብራት ለሁሉም ነዋሪ ግዴታ ነበር፡፡ የ‹‹አብዮት ጠባቂዎች›› የሕዝቡን አፍንጫ የመያዝ ታላቅ መብት ነበራቸው፡፡ ሆኖም ተንኮለኛ ልጆች ወይም የሌሊት ሌቦች የሳጠራ አጥር ላይ ያንጠለልናትን አምፖል ከሽ ያደርጉብን ነበር፡፡ ጧት ጧት አባታችን ወደ ሥራ ሲሄድ የሚያያት የመጀመርያ ንብረቱ ይህች የውጭ አምፖል ነበረች፡፡ በሰላም ማደር አለማደሯን ያረጋግጣል፡፡ ዛሬ ግን ቤታቸውን በወር በ56 ሺሕ ብር የሚያከራዩ ሰዎች አንዲት የውጭ አምፖል የሚያበሩበት ምክንያት ይገርመኛል፡፡

በተረፈ በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት መብራት በተለያየ ምክንያት ሲቋረጥብን፣ ሌሊት እንኳ ስንደውልላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞች ወዲያው ከተፍ ብለው በጨለማ በእጅ ባትሪ ብቻ እየታገዙ ምሰሶ ላይ በመውጣት መብራታችንን በፍጥነት ያስተካክሉልን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አይ ጊዜ? እነዚያ ከተፎዎቹና የተመሰገኑ የመብራት ኃይል ሰዎች የት ይሆን የገቡት? ጡረታ ወጡ ልበል? ወይስ ለማንኛውም እንኳን ለ50ኛ ዓመት የደንበኝነት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል እኛንም መብራት ኃይልንም አደረሰን እላለሁ፡፡

(ታዬ ይልማ፣ ከአዲስ አበባ)

*********

መንግሥት መብታችንን ያክብር

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉ የሚካድ አይደለም፡፡ ዋና ችግር የሚመስለን ኢሕአዴግ በአንድ ለውጥ የሚረካ በመሀል የሚተኛ፣ በየጊዜው የሚፈጠረውን ክፍተት እየለየ በእውነትና በቀጣይነት የማይፈታ ገዥ ፓርቲ መሆኑ ነው ዋና ችግሩ፡፡ ድርጅቱ የሆነ ድንገተኛ ሁኔታ ሲከሰት ወይም በየጊዜው ራሱን ማንቃት ሲገባው፣ በየአምስት ዓመቱ በድንጋጤ እየባነነ የሚወስደው ዕርምጃ በሰውና በቁሳዊ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ብክነት ጉዳት እያደረሰ ይገኛል የሚል እምነት አለን፡፡

በቅርቡ እያየነው ያለው በገፍ የማገድ፣ የማባረር፣ የማሰር ሁኔታ የዚሁ የድንጋጤ ውጤት ነው፡፡ ዕርምጃ መውሰዱ ተገቢ ቢሆንም፣ ለምን በየጊዜው ወይም በየዓመቱ ክትልልና ቁጥጥር እያደረገ መፍትሔ አይወሰድም የሚለው የኛም ሆነ የዜጎች ጥያቄ ነው፡፡ ድርጅቱ በየጊዜው የተሻለ፣ እውነተኛ ክትትል አይደረግም ብቻ ሳይሆን በመድረክ ሞቅታ ስለሚወስን፣ በየመድረኩ በሚለፋፉ ተናጋሪዎችና አስመሳዮች ስለሚማረክ ወደ ተሳሳተ ውሳኔ ይገባል፡፡ በዚሁ ምክንያት ባልዋሉበት ችግር የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ የመንግሥትና የድርጅት ጉዳይ እዚህ ላይ ምን ያህል እንደሚወሳሰብ፣ አቤቱታ የማዳመጥ ዕድል ጠባብ መሆኑ ሲታይ፣ የዚህ አገር ጉዳይ አስገራሚ ይሆናል፡፡ አንዳንድ አመራሮች ከከፍተኛው አመራር ጋር ስላልተግባቡ ብቻ እነሱ ያቀረቡትን ቡራኬ አብረው ስላልባረኩ ወይም ደግሞ የመድረኩን አቅጣጫ፣ ለመድረኩ በሚያስደስት መልኩ ክርክሩን ስላልቃኙ ብቻ ችግር ውስጥ የሚገቡ መካከለኛ አመራሮች፣ ቀላል አይደሉም፡፡ ይህ በራሱ መንግሥት አላግባብ አኩራፊዎችን በራሱ ላይ እያበዛ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ይህን ካልን ዘንድ ወደ ዋና ጉዳያች ስንገባ፣ መንግሥት ኮንዶሚኒየሞች ለመሥራት ያደረገው ጥረት በጣም የሚመሰገነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በቤቶች ልማት ውስጥ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር በሌሎች ዘርፎች ያሉ የመልካም አስተዳደር ማሳያ ሆኖ የምናየው ነው፡፡

የኮንዶሚኒየም አሠራር ጥራት ቢታይ ስንት ጉድ አለው፡፡ ቤት አገኛለሁ ብሎ የቆጠበ ዜጋ፣ ቤቱን ካገኘ በኋላም ከ15 እስከ 20 ዓመት ያለው የክፍያ ዕዳ ሲታይ ምን ያህል ችግር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምን ጥራቱ ተበላሸ ሲባል ሲሠራ የሚከታተል የመንግሥት አካለ የሌለ በመሆኑ ነው፡፡ ቤቱ ተገንብቶ አልቋል፣ ይመረቅ ሲባልም ሩጫው ለመመረቅ እንጂ ምን እንደጎደለው ቁጥጥር አይደረግለትም፡፡ ለምን ጥራት ጎደለ ሊባል የፕሮጀክቱ ገንዘብ ስለሚሰረቅ ነዋ፡፡ ምርቃቱ እንደተጠቃለለ የሚበላሽ መፀዳጃ ቤት፣ ሻወር፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የጣሪያው ቆርቆሮ በንፋስ የሚወሰድ፣ የቤቱ ግርግዳ የሚሰጠነቅ፣ ከሚመረቁ ብሎኮች ውስጥ በሪፖርት ተሠርተዋል ተብሎ ቢቀርብም በተግባር ሲታይ የሌሉ፣ የማይገኙ ብሎኮች መኖራቸው ሲታይ የሚገርም ነው፡፡ ይህ የብሎክ መሰረቅ ነገር በየካ አያት ቁጥር ሁለት ኮንዶሚኒየም እንደተፈጸመ በስፋት ይወራል፡፡

ሰሞኑን መንግሥት የኮንዶሚኒየም ቆጠራ ሲያካሂድ የታየው ችግር መንግሥትና አገሪቷ የት ደረጃ እንዳሉ የሚያሳይ ነው፡፡ የተገለጸው ችግር እዚያው የተዘረዘረ ስለሆነ ጸሐፊዎች እንዲተነትኑት ብንተውላቸው ይሻላል፡፡ አንደኛ እምነት ግን መንግሥት ኮንዶሚኒየም ለመሥራት እንደጓጓው ሁሉ በአተገባበሩና በአመራሩ ዙሪያ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ለመመልከትና ለማስተካከል የፈለገ አይመስልም፡፡ በኮንዶሚኒየሞች ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ወረዳ ተብለው ከሚጠሩ ምናልባትም ከአንዳንድ ክፍለ ከተሞች የሚበልጥ ቁጥር ያለው ነው፡፡ አስተዳደሩ በርቀት ካልሆነ በቀር እዚህ ያለውን ሕዝብ አያውቀውም፡፡ እነዚህ ሕዝብ የሰፈረባቸው ኮንዶሚኒየሞች በቅርብ የመንግሥት መዋቅር የላቸውም ብቻ ሳይሆን ኮንዶሚኒየም ውስጥ ያለው ኅብረተሰብም እንዴት እንደሚደራጅ የሚገልጽ  ማንዋል የለም፡፡

መንግሥት በኮንዶሚኒየሞች ውስጥ የጋራ መጠቀሚያ ሲሠራ በጋራ መጠቀሚያው ዙሪያ ያለው ሰው እንዲቀራረብ፣ ማኅበራዊ ችግሩ እንዲፈታ ብሎም የፀጥታና የንፅህና እንዲሁም የልማት ጉዳዮች በአግባቡ እንዲመለሱ ለማድረግ አስቦ ይመስላል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ አንድ የጋራ መጠቀሚያ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ብሎኮች የያዘ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እነዚህ የጋራ መጠቀሚያዎች በነዋሪዎች የተገነቡ፣ የተከፈለባቸው እንደመሆናቸው በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፡፡ ሆኖም የክፍለ ከተማ የቤቶች ኤጀንሲ አመራሮች በሕዝቡ የመረዳት መብትና ፍላጎት ውስጥ እየገቡ ከመደገፍ ይልቅ ሲያደናቅፉ ይታያሉ፡፡ ይህ ማለት መንግሥት በኅብረተሰቡ ፍላጎት፣ በገንዘብ እንቅስቃሴ ሒደቶች ላይ አይምራ፣ አቆጣጠር ማለታችን አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት አንቀፅ 31 የመደራጀት መብት በሚለው ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱን የሚነካ ተግባር ሳይፈጸም ማለት ነው፡፡

እኛ በምንገኝበት ኮንዶሚኒየም ውስጥ ኮሚናል ሰባት ብሎኮች የሚገኙ ሲሆን፣ በውስጣቸው 175 አባወራዎች ይገኛሉ፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ለመደራጀት ስንጠይቅ ብቻችሁን አትደራጁም፣ ከዘጠኝ የጋራ መጠቀሚያዎች ጋር ነው የምትደራጁት፣ ከየኮሚናሉ የሚገኘውን ገቢም ለመንግሥት ገቢ ታደርጉና በምታቋቁሙት ኮሚቴ አማካይነት እይጠየቃችሁ ትጠቀማላችሁ ተብለናል፡፡

ዕውቅና ለመጠየቅ ስንመጣም የአባልነት ትከፍላላችሁ ይላሉ፡፡ ዕውቅና ሳይሰጥ ደግሞ መብራትም ውኃም እንዳይገባ ይላሉ፡፡ ይህ በመሆኑ እንደፈለጉት ኅብረተሰቡን እየነዱና መጠቀሚያ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ አንድ የመብራት ኃይል ሠራተኛ ጉዳዩ ወደ መብራት ኃይል ሳይሄድ በመሀል ገብቶ በራሱ መንገድ እንደሚጠቀመው ማለት ነው፡፡

ስለዚህ የእኛ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ጥያቄ የሚከተለው ነው፡-

  • ለምን በመንግሥት ወይም በባለሙያው ፍላጎት ብቻ እንድንደራጅ ይፈለጋል?
  • ለምን የመደራጀት መብታችን አይከበርልንም? የኅብረተሰቡስ ፍላጎት ለምን አይታይም?
  • ለኮሚውናል የከፈልነው ገንዘብ ለምን እንድንጠቀምበት አይደረግም?
  • እንደ ኅብረተሰብ ሊያዩን ሲገባ ለምን እንደ መንግሥት መዋቅር ያዩናል?  ምክንያቱም መንግሥት ለራሱ አስተዳደር እንዲመቸው ምናልባትም ለሕዝብ ለማገልገል እንዲመቸው የሚፈጥረው የአስተዳደር እርከን አመቺነት በራሱ መንገድ ሊደራጅ ይችላል፡፡ ለነዋሪዎቹ ግን ከጋራ መጠቀሚያቸው ውጭ ከፍላጎታቸው ውጭ ሊያደራጃቸው አይገባውም፡፡ ያስተካክል፡፡

(የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...