Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየአዲስ አበባ ምክር ቤት በሥልጣን ለሚነሱ ባለሥልጣናት ጥቅማ ጥቅም የሚፈቅድ አዋጅ አፀደቀ

  የአዲስ አበባ ምክር ቤት በሥልጣን ለሚነሱ ባለሥልጣናት ጥቅማ ጥቅም የሚፈቅድ አዋጅ አፀደቀ

  ቀን:

  አዋጁ ተቃውሞ ቀርቦበታል

  የአምስት ዓመት የሥራ ጊዜውን አጠናቆ እስከሚቀጥለው ምርጫ ዕድሜው የተራዘመለት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ከሥልጣን የሚነሱ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ስለሚያገኟቸው መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች የሚደነግግ አዋጅ አፀደቀ፡፡

  በከተማው ምክር ቤት ሐሙስ ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀርቦ የፀደቀው አዋጅ ያስፈለገበት ምክንያት በመግቢያው ላይ እንደተቀመጠው የከተማው የበላይ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ በቋሚነት የሚሠሩ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች ለሕዝብ ጥቅም የሚሠሩ ስለሆነ ከኃላፊነት ሲነሱ ከጉስቁልና የራቀ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ፣ ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥበቃና ከለላ ለመስጠት ነው፡፡

  ለከተማው የበላይ ኃላፊ የሚባሉት ከንቲባ፣ ምክትል ከንቲባ ወይም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሚሾሙ ሲሆን፣ ከፍተኛ ኃላፊ የሚባሉት ደግሞ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የፕላን ኮሚሽን፣ የዋና ኦዲተር፣ የገቢዎች ባለሥልጣን፣ የከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅና የክፍላተ ከተሞች ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምክትል ኃላፊዎች፣ ዳኞች፣ አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ ተካተዋል፡፡

  እነዚህ ባለሥልጣናት እንደ ደረጃቸው የመቋቋሚያ ክፍያ፣ የመኖርያ ቤት፣ ተሽከርካሪ፣ የሕክምና አገልግሎትና የግል ደኅንነት ጥበቃ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይደረጋል ተብሏል፡፡

  ይህ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት ግን በምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የምክር ቤት አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ይህ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሥልጣን ዘመኑን ባጠናቀቀበት ወቅት ለራስ የሚያደላ አዋጅ ለምን ያፀድቃል? ትዝብት ላይ አይጥልም ወይ? አዋጅ ከወጣስ ሁሉን ያካተተና በተለይም ሁሉንም የምክር ቤት አባላትና በወረዳና በክፍለ ከተማ የሚገኙትን ለምን አካቶ አይዘጋጅም የሚሉ ይገኙበታል፡፡

  የምክር ቤት አባላቱ እንዳነሱት በወረዳዎችና በክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የምክር ቤት አባላት፣ ‹‹ሥራ ሲሆን ለእኛ፣ ጥቅማ ጥቅም ሲሆን ለእናንተ፤›› የሚል ቅሬታ በየጊዜው ያቀርባሉ፡፡ አሁንም የሆነው ይኼው ነው በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

  ነገር ግን ለእነዚህ ቅሬታ አዘል ጥያቄዎች በሥራ አስፈጻሚው የተሰጠው ምላሽ ይኼ የጥቅማ ጥቅም አዋጅ በፌዴራል፣ በክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር ተግባራዊ የተደረገ መሆኑን፣ እንዲያውም በአዲስ አበባ ተግባራዊ ሳይደረግ ዘግይቷል የሚል ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ምክር ቤት 138 መቀመጫዎች አሉት፡፡ በዕለቱ የተገኙት 75 አባላት ሲሆኑ፣ ለዚህ አዋጅ 69 አባላት የድጋፍ ድምፅ ሲሰጡ፣ ስድስቱ ድምፀ ተዓቅቦ አስመዝግበዋል፡፡   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...