Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትተስፋን የሰነቀው የፌዴሬሽኑ መግለጫ

ተስፋን የሰነቀው የፌዴሬሽኑ መግለጫ

ቀን:

በቅርቡ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲሱ አመራር፣ በቀጣይ ስለሚያከናውናቸው ዕቅዶችና  አተገባበራቸውን አስመልክቶ የመጀመርያውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ለዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ተብለው የሚታመንባቸው ስትራቴጂካዊ ሰነዶች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት ስለመጠናቀቁ ጭምር የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተናግረዋል፡፡ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቅጥርና ክለቦች ሊጉን በባለቤትነት ስለሚያሰተዳድሩበት ቅድመ ሁኔታም በመግለጫው ተካቷል፡፡

ብሔራዊ ፌዴረሽኑ በየአራት ዓመቱ በሚያደርገው የአመራር ምርጫ በርካቶች ተቋሙን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ምንም እንኳን የምርጫው ሒደት ብዙ ውጣ ውረድና ትርምስ ቢያስተናግድም፣ በአፋር ሰመራ በተደረገው ምርጫ አዳዲስ አመራሮች ወደ ተቋሙ መጥተዋል፡፡ ከነዚህ አመራሮች መካከል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ መድረክ በማብቃት የሚጠቀሱት አቶ ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ አቶ ሰውነት በእግር ኳሱ ባላቸው የጎላ ድርሻ በፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እንዲያገለግሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው ስለመሆኑ ጭምር በፕሬዚዳንቱ ተብራርቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔታል ሆቴል በሰጠው በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ተቋሙን ማዘመን የሚያስችሉ አሠራሮች መዘርጋት ይቻል ዘንድ አደራጀቱን የሚያጠና ገለልተኛ የሆነ የጥናት ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ዕቅዱን ለመተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ የትኩረት አቅጫዎች ተቀምጠዋል፡፡ በዋናነት በተለይም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ይዘትና ቅርፁን እየለወጠ ሌላ መልክ እየያዘ በመምጣት ላይ የሚገኘው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ፣ ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በተለገሰው ሦስት ሚሊዮን ዶላር ላይ ተጨማሪ በማድረግ የፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ግዥ፣ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቅጥር እንዲሁም ፌዴሬሽኑን በተለያዩ ዲፓርትመንቶችን ማጠናከር የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ምንም እንኳን እነዚህን መሰል የዕቅድ ክንውኖች የተለመዱና ቀደም ሲል የነበሩት አመራሮችም ተቋሙን በተረከቡ ማግሥት የሚናገሯቸው እንደመሆናቸው መጠን፣ የተግባራዊነታቸው ጉዳይ አጠያያቂ ቢሆንም አዲሱ አመራር እንደ መነሻ እተገብራቸዋለሁ ብሎ ያሰባቸው ዕቅዶች በተስፋ ሰጪነታቸው ሊወሰዱ እንደሚገባ የሚናገሩ አሉ፡፡

ለዚህም እንደ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው፣ ለወራት ያለ አንዳች አሠልጣኝ ተበትኖ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ጉዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡ ቅጥሩን ለመፈጸምም እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብሏል፡፡ ይሁንና አዲስ አሠልጣኝ ለመመደብ የወጣው የቅጥር ማስታወቂያ ያካተታቸው መሥፈርቶች ግን ከወዲሁ ትችትና ወቀሳ ማስተናገድ ጀምረዋል፡፡ እንደ አንዳንዶቹ ከሆነ ማስታወቂያው በልክ የተሰፋ  ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የወጣው ማስታወቂያ ካካተታቸው መሥፈርቶች ውስጥ ለትችትና ወቀሳ የሚጋብዙት ነጥቦች፣ ብሔራዊ ቡድኑን እንዲያሠለጥን ሊመረጥ የሚፈለገው ባለሙያ በፕሪሜየር ሊጉና ብሔራዊ ሊጉ ከአሥር ዓመት በላይ ያሠለጠነና በማሠልጠን ላይ የሚገኝ ሆኖ የካፍ “ኤ” ላይሰንስ ያለው የሚለው በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ሁሉ ለብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት በመሠረታዊነት የሚያስፈልገው፣ ባለሙያው በብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት ያለው ስኬት እንደ መሥፈርት አልተካተተም፡፡

እንደ አጋጣሚ ሆኖ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው አሁን በሚገኙበት ኃላፊነት ላይ ባይሆኑ ኖሮ መሥፈርቱ የእሳቸውን የብሔራዊ ቡድን አገልግሎት ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው አያከራክርም፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው አሠልጣኝ ሰውነት፣ “በአገሪቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚመጥን ሰው ቢኖር ኖሮ ይህን መሥፈርት ማውጣት ባላስፈለገ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን መሥፈርቱ እንደ መሥፈርት ተቀመጠ እንጅ ተቋሙ የተሻለ አማራጭ ካገኘ ክርክር ውስጥ መግባት ሳያስፈልገው የሚመጠነውን ሰው ከመሾም የሚያግደው አንዳች ነገር የለም፤” ብለዋል፡፡

አዲሱ አመራር አዲሱን ሥራ በዚህ አግባብ መጀመሩ ከወዲሁ ቢያነጋግርም፣ ነገር ግን ደግሞ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰውነት ቢሻው የእሳቸውን የብሔራዊ ቡድን ተሞክሮና ዓለም ላይ ያለውን አሠራር ግምት በማስገባት በመሥፈርቱ ላይ መከራከር ሲገባቸው፣ ስለተገቢነቱ ሲከራከሩ ተደምጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...