የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለማዘጋጀት ውድድር ውስጥ ተካቶ መዘጋጀት አቅም እንዳለው የሚያስመሰክርና ከተወዳዳሪዎች ጋር ተፎካክሮ ማሸነፍ የመጀመርያው ፈተና መሆኑ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ ለአዘጋጅነት የሚወዳደረው አገር ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ጎላ ያለ ከሆነ ነገሩን የበለጠ አድካሚ ያደርገዋል፡፡ ድግሱን ለማሰናዳት ከሚጠይቀው የገንዘብ አቅም ባሻገር የሚያስገኘው ትርፍም እነዚህን አገሮች ይበልጥ ውድድር ውስጥ እንዲካተቱ ይገፋፋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ፊፋ በሚል መጠርያ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በተደጋጋሚ ለሙስና ሲጋለጥ ተስተውሏል፡፡ ለሙስና እንዲጋለጡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ደግሞ የቴሌቪዥን ፈቃድ አሳልፎ የመስጠት ሒደት ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በፊፋ ውስጥ የነበረው ሽኩቻ ማሳያም ነው፡፡
21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለማሰናዳት እ.ኤ.አ. 2010 ኃላፊነት የተረከበችው ኃያሏ አገር ሩሲያ ዝግጅቷን በ11 ከተሞችና 12 ስታዲየሞች ማከናወን ከጀመረች ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. እንግዶችዋን መቀበል የጀመረችው ሩሲያ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎችን አጠናቃ 16 አገሮች ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡
እነዚህ 16 ብሔራዊ ቡድኖች በተለያዩ የሩሲያ ከተሞች ጨዋታቸውን ማከናወን የቻሉ ሲሆን በየስታዲየሙም ከፍተኛ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡
አዘጋጇ አገር ተመልካቾችን ያለ ምንም ቪዛ በደጋፊ መታወቂያ እንዲገቡ ማድረጓ ትልቅ ድምቀት እንዲሰጥ አስችሎታል፡፡
ቀደም ብሎ ሩሲያ ከነበራት የፖለቲካ ውዝግብ በመነሳት ተመልካቾች አስፈሪና አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥመናል የሚል ጥርጣሬ እያደረባቸው እንደነበር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተቃራኒው ግን አዘጋጇ አገር እንግዶችን ለማስደሰት በየባቡር ጣቢያዎች፣ ስታዲየሞች ውስጥ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች ላይ ሳይቀር ለእንግዶች ድጋፍ የሚሰጡ በጎ ፈቃደኞችን አሰማርታለች፡፡ ኅብረተሰቡም ቢሆን በቅድሚያ እንደተባለው ዓይነት አስፈሪ ለተመልካቾች ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ደስተኛና አብሮ የሚካፈል ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በተለይ ደግሞ በአውሮፕላንና በባቡር እንዲሁም በፈጣን መንገድ ትራንስፖርቷ ተመልካቾቹ ከቦታ ቦታ እንዳሻው እንዲዘዋወሩ አድርጓታል፡፡
ላለፉት አራት ዓመታት በቂ ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው ሩሲያ 14.2 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት እስከዛሬ ያልተደፈረ ወጪ አውጥታለች፡፡ ይሄም ወጪ ሙሉ በሙሉ መልሳ ታተርፍበታለች የሚለው በባለሙያዎች ያልታመነበት ሆኗል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ከሆነም ሩሲያ ከትርፍ ይልቅ አገሪቷ ኃያል መሆኑዋን ለማሳየት ያሰናዳችው ነው የሚሉም አልታጡም፡፡
በምድብ ማጣሪያው ጨዋታቸውን ያደረጉ 16 አገሮች በሽንፈት ወደየቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የ2014 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ጀርመን መውደቅና ከአምስት አፍሪካ አገሮች አንዱ እንኳን ወደ ቀሪ 16 ውስጥ አለመካተቱ አግራሞትን የጫረ ሆኗል፡፡
በተለይ ሴኔጋል በኮሎምቢያ 1ለ0 ተሸንፋ ከውድድር ውጪ የሆነችበት በብዙ የአፍሪካ አገሮችና ተሳታፊዎች ያስቆጨ አጋጣሚ ሆኗል፡፡
ባለፉት 48 ጨዋታዎቹ 2.1 ሚሊዮን ተመልካቾች ስታደሙ በየስታዲየሙ በአማካይ 45,394 ተመልካቾች ጨዋታዎቹን መመልከት ችለዋል፡፡
በአጠቃላይ 122 ጎሎች ሲቆጠሩ በየጫዋታው በአማካይ 2.54 ተቆጥሮበታል፡፡ የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ በርካታ ፍጹም ቅጣት ምት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ አዲሱ የዳኝነት መሣሪያ ቫር ለዚህ እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
ከ24 ፍጹም ቅጣት ምቶች 18ቱ ሲቆጠሩ ስድስቱ ተስተዋል፡፡ በራስ የግብ ክልል ላይ የተቆጠሩ ግቦች ዘጠኝ ሲሆኑ፣ በመጀመርያ አጋማሽ 47 ግቦች በሁለተኛ አጋማሽ ደግሞ 75 ጎሎች መቆጠራቸው ፊፋ ያወጣው መረጃ ያስረዳል፡፡
የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አዲስ የዳኝነት ቴክኖሎጂ መጠቀሙ በተመልካች መካከል ሁለት ዓይነት ስሜት ፈጥሯል፡፡ አንደኛው ወገን ዳኝነቱን ያጠናክራል ሲል ሌላኛው ደግሞ የኳስን ውበት ያጠፋል እያለ ነው፡፡
የደጋፊዎች ጥግ
በስታዲየም ከሚከናወኑ ጨዋታዎች በላይ ፊፋ ከአዘጋጅ አገር የውድድር ዝግጅት አካል ጋር በመነጋገር በየስታዲየሙ አካባቢዎች ተመልካቾች ከስታዲየም ውጪ ሆነው ጨዋታ እንዲመለከቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
ፊፋ፣ በሩሲያ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ ለእንግዶች በተዘጋጀ ምቹ ቦታ ላይ ‹‹ፈን ፌስት›› ከፍቶ ይገኛል፡፡ ሞስኮ ሉዝንኪ ስታዲየም የሚገኘውና የሞስኮ ሎሞኖስቭ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ፈን ፌስት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ያለምንም ክፍያ ክፍት የሚደረገው ይህ ሥፍራ ፓርኪንግ፣ የመዝናኛ፣ የመጠጥ፣ የምግብና የሕፃናት ማረፊያን ያካተተ ነው፡፡ በአራቱም አቅጣጫ በተተከሉት ትልልቅ ስክሪኖች አማካይነት ጨዋታዎቹን የሚያዩት ደጋፊዎች እየጠጡና እየተዝናኑ ነው፡፡ በቂ የፀጥታ ጥበቃ ያለው ሲሆን፣ ቤተሰብ በቡድን ሆኖ ጋደም ብሎም ጨዋታን መመልከት ያስችለዋል፡፡ በቅርቡ ፊፋ ባሳወቀው መረጃ መሠረት እስካሁን 2.5 ሚሊዮን ተመልካቾች ወደ ፈን ፌስት ማምራታቸውን አስታውቋል፡፡
በእነዚህ ሥፍራዎች ጨዋታ ሲመለከቱ በነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች አስተያየት ከሆነ ይኼ ዓለም ዋንጫ ሩሲያውያን ምን ያክል አቅም እንዳላቸውና እንግዳ ማስተናገድ እንደሚችሉ ያሳየ ነው በማለት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
21ኛውን ዓለም ዋንጫ አሸናፊ በቀላሉ መገመት ከባድ ቢሆንም ቤልጂየምና ፈረንሣይ በብዙ ተመልካቾች ከወዲሁ ከፍተኛ ተመልካች ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዳዊት ቶሎሳ፣ ከሩሲያ