Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት በወንጀል ለሚፈለጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የምሕረት ጥያቄ ለፓርላማ እንደሚያቀርብ ተሰማ

መንግሥት በወንጀል ለሚፈለጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የምሕረት ጥያቄ ለፓርላማ እንደሚያቀርብ ተሰማ

ቀን:

ምሕረት የሚሰጥበትን ሥነ ሥርዓት ፓርላማው አፀደቀ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለአገራዊ መግባባት ሲባል ምሕረት ሊደረግላቸው ይገባል ያላቸውን በወንጀል የሚፈለጉ ድርጅቶችና ግለሰቦችን በመዘርዘር የምሕረት ጥያቄ በቅርቡ ለፓርላማ እንደሚያቀርብ ታወቀ።

ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘውምሕረት ቦርድ ምሕረት እንዲደረግላቸው በመለየት የዘረዘራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን የያዘ የሕግ ሰነድ በረቂቅ አዋጅነት ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተወሰነበት በኃላ ለፓርላማ እንደሚቀርብ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምሕረት እንዲያገኙና ከሚካተቱት መካከል ከዚህ ቀደም በፓርላማው በሽብርተኝነት የተፈረጁ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚገኙበት ታውቋል። በተጨማሪም በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ተሳታፊ በመሆናቸውና ግንኙነት በመመሥረታቸው በወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ ግለሰቦችም፣ የምሕረቱ አካል እንደሚሆኑ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የበርካታ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ምሕረት የሚሰጠው መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ ከሚደረግ የወንጀል ድርጊት በኋላ፣ ከእርስ በርስና ከውጭ ኃይሎች ጋር ከተደረገ ጦርነት በኋላ የሚኖሩ ፖለቲካዊ ብጥብጦችንና አለመግባባቶች ለማርገብ፣ በብጥብጡ ምክንያት በተከፋፈለ ማኅበረሰብ የአገር ሰላም የማደፍረስ ድርጊት ለፈጸሙና ወደ ሰላማዊ አኗኗር ለሚገቡ ሰዎች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የአገርን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በተወሰኑ የወንጀል ዓይነቶችና በአንድ ደረጃ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወይም ወንጀለኞች ላይ ምርመራ ወይም የክስ ሒደት ከማስቀጠል ወይም ቅጣትን ከማስፈጸም ይልቅ፣ ምሕረት የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ሲታሰብ የሚሰጥ መሆኑን የምሕረት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓትን የሚያቋቁመው አዋጅ ይገልጻል። ይህ አዋጅ ሐሙስ ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማው ፀድቋል።

የፀደቀው የምሕረት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት አዋጅም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ወቅት ለማኅበረሰቡ ሰላምና ደኅንነትፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማረጋገጥ ምሕረት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ምሕረት የሚሰጥበትን ሥነ ሥርዓት በሕግ መደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ መታወጁን በመግቢያው ይገልጻል፡፡

በአዋጁ መሠረት የምሕረት ቦርድ የሚቋቋም ሲሆን፣ የቦርዱ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይሆናሉ። የቦርዱ አባላት ደግሞ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚወከል አንድ ዳኛ፣ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰየሙ ሁለት ሰዎች የቦርዱ አባላት እንደሚሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

የቦርዱ ሥልጣንና ተግባርም የምሕረት ጥያቄን መቀበል፣ መመርመርና የውሳኔ ሐሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅሞችን መሠረት በማድረግ በራሱ ተነሳሽነት ወይም ከክልሎች በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት ምሕረት የሚሰጥባቸውን ወንጀሎች፣ በወንጀል የተጠረጠሩ፣ የተከሰሱ ወይም ፍርድ የተላለፈባቸውን ሰዎች ለይቶ ለምሕረት ቦርድ የማቅረብ ኃላፊነትን አዋጁ ይሰጠዋል፡፡ የወንጀል ድርጊቱ በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚያስከትለው ወይም ያስከተለው ተፅዕኖ፣ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ምሕረት የተሻለ አማራጭ ስለመሆኑና ምሕረት የሚደረግላቸው ሰዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ የሚያሳዩት ፍላጎት ምህረት ለመስጠት እንደ መሥፈርት ተቀምጠዋል።

ቦርዱ ተስማምቶበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበውን የምሕረት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተስማሙበት፣ የሕግ አወጣጥ ሒደትን ተከትሎ የምሕረት ጥያቄው የምሕረት አዋጅ እንደሚዘጋጅለትና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላማ እንደሚላክ፣ ፓርላማው የምሕረት አዋጁን ሲያፀድቀው ተግባራዊ እንደሚደረግ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡

ምሕረት የሚያስከትለው ውጤት በተመለከተ በሚዘረዝረው አንቀጽ ሥርም ቅጣት ተወስኖ ከሆነ ቅጣቱ የሚያስከትለውን ማናቸውም የወንጀል ውጤቶች የሚያስቀር፣ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳልነበር ተቆጥሮ ከወንጀለኛው መዝገብ ላይ የመሰረዝ፣ የወንጀል ምርመራም ሆነ ክስ እንዳይጀመር ወይም እንዳይቀጥል እንደሚያደርግ ተዘርዝሯል፡፡

ይህ የምሕረት አሰጣጥና አፈጻጸም ከይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ የምሕረት አሰጣጥ አዋጅ ረቂቅ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28(1) መሠረት፣ እንዲሁም በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 30 መሠረት የሚፈቀደውን ምሕረት ለመስጠት ነው የተዘጋጀው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...