Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋጋሪ ማብራሪያ በፓርላማ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋጋሪ ማብራሪያ በፓርላማ

ቀን:

ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በፓርላማ ለምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከፓርላማ አባላት በተጨማሪ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ስሜት የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ ከበዓለ ሲመታቸው ወዲህ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ነው፡፡ በሩሲያ እየተካሄደ ባለው የዓለም ዋንጫ የስዊድንና የደቡብ ኮሪያን የምድብ ጨዋታ ቀጥታ ሥርጭት እየተከታተሉ የነበሩ የኳስ አፍቃሪያን ሳይቀሩ፣ ትኩረታቸውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ቀይረው ነበር፡፡ ይህም በተለያዩ ሥፍራዎች ተስተውሏል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎችም በቀጥታ ሲከታተሉ የነበሩ ወገኖችም ከሰጡዋቸው አስተያየቶች ለመገንዘብ እንደተቻለው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ጠንከር ብለው በልበ ሙሉነት ምላሾች የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሙገሳዎች ሲቀርቡላቸው ተሰምቷል፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎና የፈጠረው ስሜት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ የሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን አራተኛ ልዩ ስብሰባ በመሰየም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሪፖርት እንዲያቀርቡና ከምክር ቤቱ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዴትና ለምን ተጠሩ?

በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመንግሥትን ሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ በዓመት ሁለት ጊዜ ሪፖርት እንዲያቀርብ ይደነጋግል፡፡ ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ መቅረብ የሚገባው ጉዳይ አለ ብሎ ካመነ በማንኛውም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመጥራት ሪፖርት እንዲያቀርብ ሊያደርግ እንደሚችል፣ በአሠራርና አባላት ሥነ ምግባር ደንቡ አንቀጽ 81(3) ሥር ደንግጓል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ ‹‹መቅረብ የሚገባው ጉዳይ አለ ብሎ ካመነ›› የሚለውን የድንጋጌውን አካል፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5(ሀ) ሥር ‹‹አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ››፣ እንዲሁም በንዑስ አንቀጽ 5(ሐ) ላይ በመንግሥታዊ አካሉ ላይ እንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ከሕዝብ የሚነሱ እንደሆነ፣ በማንኛውም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ሌሎች የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት አመራሮች ሊጠሩ እንደሚችሉ በማብራራት ይደነግጋል፡፡

 ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጠራው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና የአሠራር ድንጋጌዎች መሠረት ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡትም በምክር ቤቱ ልዩ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት ከተጠሩበት ምክንያት ወቅታዊነትና አንገብጋቢነት ጋር የተገናኘ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ‹‹የሥራ መደራረብ ወይም አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ሲጋጥም ከመደበኛው የስብሰባ ጊዜ (ከማክሰኞና ከሐሙስ) ውጪ ባሉት ቀናት ልዩ ስብሰባ ሊያካሄድ ይችላል፤›› ሲል የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ስለልዩ ስብሰባ በሚገልጸው አንቀጽ 16 ይደነግጋል፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሰበሰበው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካሳለፋቸውን ሁለት ውሳኔዎች በኋላ በማኅበረሰቡ ዘንድ ግራ መጋባት በመፈጠሩ፣ ከገዥው ፓርቲ መሥራች ድርጅቶች ግንባር ቀደም በሆነው ሕወሓት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን ውሳኔ በመተቸት መግለጫ ማውጣቱ ግራ መጋባቱን ያባባሰው በመሆኑ፣ ፓርላማው የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማብራሪያ እንደጠራ የፓርላማው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግ በራሱ ድርጅታዊ አሠራር አለመግባባቶቹን መፍታት እንዳለበት፣ ፓርላማው ግን መንግሥትን እንደሚከታተል አካል እየሆነ ያለውን መረዳት ስላለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲጠሩ ባለፈው ሐሙስ ተግባብቷል ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፓርላማው ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአስቸኳይ ስብሰባ የተገናኘው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአገሪቱን አኮኖሚ ቀጣይነት ለማረጋገጥና ከዕዳ ጫና ለመውጣት ሲል፣ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙትን ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ማለትም ኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ በሙሉና በከፊል ለመሸጥ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ18 ዓመታት ያልተፈታውን የድንበር ውዝግብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት በማቀድ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ለመተግበር መወሰኑ ይታወቃል፡፡

እነዚህን ሁለት ውሳኔዎች ሕወሓት የሚቀበላቸው ቢሆንም፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎቹን ያሳለፈበት መንገድ ላይ ቅሬታዎቹን አቅርቧል፡፡

በዚህና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በፓርላማው ተገኝተዋል፡፡ ከፓርላማው 547 አባላት መካከል 325 አባላት የተገኙ ሲሆን፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ላይ ቅሬታውን የገለጸው የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮች ማለትም አቶ ዓባይ ፀሐዬና አቶ ጌታቸው ረዳ በፓርላማ አልተገኙም፡፡ ከደኢሕዴን አመራሮች መካከል ደግሞ የፓርቲው ሊመቀንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤና አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ፓርላማው አልተገኙም፡፡

በአራት ሙሉ ገጾች የተዘጋጀ ወቅታዊ ሁኔታዎችን፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሪፖርታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቡ በኋላ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የፓርላማ አባላቱ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ዋናዎቹ ሕወሓት በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ላይ ካቀረበው ቅሬታና ትችት አዘል መግለጫ ጋር ዝምድና ያለው በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የጥያቄዎቹን ዝምድና ባገናዘበ መንገድ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ለቀረቡት ዋና ዋና ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሽያጭን በተመለከተ

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በከፊልና ሙሉ በሙሉ እንዲሸጡ በተወሰኑ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ጉዳይ በተመለከተ የሚቀበለው ቢሆንም፣ አሁን ለገጠመው መሠረታዊ የኢኮኖሚ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየት ሲገባው ችግሩ ባስከተላቸው ውጤቶችና ጊዜያዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ መስጠቱ ጉድለት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ሽያጩም ጥንቃቄ እንዲደረግበት ያሳስባል፡፡ የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ ታደለች ከበደ ባቀረቡት ጥያቄም አየር መንገድና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ወደ ግል ሲዘዋወሩ ለሕዝብ ከሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት ጋር እንዴት ሊሆን ይችላል? በተለይ መብራትን በተመለከተ ከአገልግሎት ጥራት ጋር እንዴት ሊሆን ነው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በዚህ ጉዳይ ረዥም ማብራሪያና ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውሳኔው ለአገሪቱ እጅግ እንደሚያስፈልግና በየወቅቱ ተመሳሳይ ማሻሻያዎችን መውሰድ ካልተቻለ፣ ኢኮኖሚው ወደ ኋላ የሚመለስና አገራዊ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አገሪቱ ላለፉት ዓመታት ስትበደር ቆይታ አሁን መክፈያው ጊዜው ሲደርስ ለመክፈል ከፍተኛ ችግር መፈጠሩ፣ ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ተበድሮ መክፈል የማይችል አገር የማይታመን፣ ወደፊትም ለመበደር የሚቸገር በመሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻዎች እያደረጉ ይህንን ችግር መፍታት የሚያስፈልግ በመሆኑ ነው፤›› ሲሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ፕሮጀክቶችን መጀመር እንጂ መጨረስ ስላልተቻለ የተፈጠረውን ችግርና የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ መሆኑን አክለዋል፡፡ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ሌሎቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ሥራውን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ወጪ ወይም የሀብት አጠቃቀምንና ብክነትን ለመከላከል ከተፈለገ፣ እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ማተኮር የሚያስፈልግ በመሆኑ ወደ ግል መዘዋወራቸው መመረጡን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የሚገኘው ጥቅም ደግሞ አዲስ ሀብት በሽያጭ በማመንጨት ኢኮኖሚውን ለማስቀጠል የሚጠቅም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ እየተነሳ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ልማታዊ መንግሥት ወደ ካፒታሊስት ሥርዓት የሚያደርስ ድልድይ እንጂ በራሱ ግብ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በኒዮ ሊበራሊዝምና በልማታዊ መንግሥት መካከል ካፒታሊዝም ሥርዓትን በመገንባት ረገድ ልዩነት አለመኖሩን፣ ልዩነቱ የካፒታሊዝም ሥርዓት በምን አግባብ ቢገነባ ጥሩ ነው በሚል ላይ ብቻ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

‹‹እዚህ ላይ ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ የምንፈልጋቸውን ኩባንያዎች ከመንግሥት ሞኖፖሊ ወደ ግል ሞኖፖሊ እንዲዘዋወሩ ማድረግ የሚፈለገውን ሐሳብ የሚያሳካ አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ወደ ግል ይዞታ የተዘዋወሩ ኩባንያዎች በጥቂት ግለሰቦች የተገዙ በመሆናቸው፣ ከመንግሥት ያልተሻለ ውጤታማነት ማስመዝገብ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ይህ ዓይነት ስህተት እንደማይደገም፣ በአፍሪካ አገሮች የተስተዋሉ ስህተቶችም በኢትዮጵያ እንዳይደገሙ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ዋና ዋናዎቹ ኩባንያዎች አብላጫ አክሲዮን በመንግሥት ዞታ የሚቀጥል እንደሆነ፣ ለሽያጭ ከሚቀርበው የአክሲዮን ድርሻ ውስጥ አምስት በመቶ የሚሆነው ውጭና አገር ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውን እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው በሚሹት የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ብቻ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሸጠው የአክሲዮን ድርሻ ገንዘብ ያላቸው ብቻ እንዳይጠቀልሉ ጥንቃቄ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አሁን እንዲዘዋወሩ የሚፈለጉ ኩባንያዎች ገበያውን በሞኖፖሊ ጭምር ይዘው ያለ ውድድር በበቂ ደረጃ ማደግ ያልቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ለምሳሌ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል የአገር ውስጥ የስልክ ጥሪ የሚገኝ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምር፣ ከውጭ ጥሪ የሚገኝ ገቢ ከዓመት ዓመት በእጅጉ እየቀነሰ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በውስጥም በውጭም የቴሌኮም ማጭበርበር በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡  

‹‹የቴሌኮም ማጭበርበር የትም ቦታ አለ፣ የእኛ ግን የከፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሌላው የሀብት ብክነት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቴሌኮም እየገዛ በየመጋዘኑ ያከማቸው ሀብትና ንብረት የትየለሌ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

‹‹የመንግሥት ስለሆነ እንጂ በግል ሴክተር ቢሆን አይታሰብም፡፡ በመግዛት የሚያድግ እየመሰለው ስለሆነ ነው፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ የኢትዮጵያን የቴሌኮም አገልግሎት ጥራት የሚያማርር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ በሶማሊያ 12 ሚሊዮን ሕዝብን ለማገልገል አራት ኩባንያዎች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመቶ ሚሊዮን ለሚቆጠረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አገልግሎት ከሚሰጠው አንድ የመንግሥት ኩባንያ የሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት በብዙ እጥፍ ይሻላል ብለዋል፡፡ ይህም የተፈጠረው በሶማሊያ ውድድር በመኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውድድር ባለመኖሩ የአገር ሀብት እንዲባክንና የአገልግሎት ጥራት እንዳይኖር ማድረጉ ሊሰመርበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡፡

ከኢነርጂ አንፃር በተደጋጋሚ መንግሥት የሚተቸው በየገጠሩ የኤሌክትሪክ ፖል ቆሞ መብራት ማድረስ አልተቻለም በማለት እንደሆነ አስታውሰው፣ ኤሌክትሪክ አምርቶ እንደገና ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትር መስመር ዘርግቶ ማቅረብ ለመንግሥት የሚያዳግት እንደሆነ አውስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል 35 በመቶ በሥርጭት ወቅት እንደሚባክን ገልጸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር የሚያዋጣው ከብሔራዊ የሥርጭት ቋት ይልቅ አካባቢያዊ የሥርጭት ቋት (ሎካል ግሪድ) መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ አንድ የግል ባለሀብት ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚወጣውን ቆሻሻ ተጠቅሜ ኤሌክትሪክ አምርቼ ለፓርኩ እሸጣለሁ ቢል ለአገር፣ ለራሱ ለኢንዱስትሪ ፓርኩም በጣም ጠቃሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ትልቅ ስምና ክብር ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀላሉ ለግል ባለሀብት ቢዞር አደጋ ያስከትልብናል የሚል ሥጋት ኢትዮጵያ ሕዝብና የምክር ቤት አባላት ቢያነሱ ተገቢ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀብለዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የሚጠይቀውን ኢንቨስትመንት በማለፍ፣ ይህንን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዝናና ክብር ማስጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ መሪዎች በቅርቡ በአፍሪካ ደረጃ አንድ አየር መንገድ ይኑር የሚል ስምምነት ተፈራርመዋል ኢትዮጵያን ጨምሮ፡፡ ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማላዊን አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ ገዝቷል፡፡ የማላዊ አየር መንገድ ሀብት ግማሹ የእኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በዛምቢያ አየር መንገድ 45 በመቶ፣ በቻድ 49 በመቶ፣ በጊኒ 49 በመቶ ገዝቷል፡፡ በቶጎ 49 በመቶ ገዝቷል፡፡ በሌሎች አገሮች ላይም በመግዛት ሒደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

‹‹እያልን ያለነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጤታማ ስለሆነ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለዓለም ያስተዋውቃል ነው፡፡ አሁን ደግሞ እየተባለ ያለው አዎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ይሆናል፡፡ በአፍሪካ ደረጃም የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውለበልባል ነው፡፡ ምርጫው ለእናንተ የሚተው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን በተመለከተ ከፍተኛ የውጤታማነት ችግር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በዓለም ካሉ ተመሳሳይ 160 ድርጅቶች 126ኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ብዙዎቹ የሚናገሩት የእናንተ መርከቦች በየአገሩ ይቆማሉ፡፡ ምክንያቱም ማርኬቲንግ ላይ ብዙ አትሠሩም ይሉናል፡፡ ያው የመንግሥት ቅጥረኛ እንደ ግል ስላልሆነ፤›› ብለዋል፡፡  

በተጨማሪም ለሚሰጠው አገልግሎት የሚያስከፍለው ዋጋ ከሌሎች ጋር ሲወዳደር እስከ 400 በመቶ የናረ መሆኑ ተወዳዳሪ እንዳይሆንና የአገሪቱንም የኤክስፖርት ዘርፍ ከመደገፍ ይልቅ እያዳከመ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል መወሰኑን የደገፈ ቢሆንም፣ ውሳኔው በኢሕአዴግ ምክር ቤት ሳይቀርብ አጋር ድርጅቶች ሳይወያዩበት እንደ መጨረሻ ውሳኔ ተደርጎ ለሕዝብ ይፋ መደረጉን መተቸቱ ይታወሳል፡፡ የፓርላማው አባል አቶ መሠረት ጀማነህ በበኩላቸው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን የድንበር ውዝግብ በሰላም ለመፍታት መወሰኑ ተገቢ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የልጆቹን ውድ ሕይወት፣ ደም፣ አካልና ሀብቱን በገበረበት ጉዳይ ላይ የተጣደፈ ውሳኔ መወሰን ተገቢ ሆኖ እንዳላገኙት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ሕዝብ ተወያይቶ እንዲወስንበት ውሳኔው በድጋሚ ቢታይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚነስትሩ በሰጡት ምላሽ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ብዥታ መፈጠሩን እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል፡፡ ብዥታው አንዱ የሚነሳበት ምክንያት በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች መካከል ድንበር አለ ከሚል ዕይታ የሚመነጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ ድንበሩ ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩት አርተፊሻል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ትግራይና ኤርትራ ውስጥ የሚኖረውን የኩናማን ሕዝብ ለሁለት እንደከፈለ፣  በተመሳሳይ የቦረና ኦሮሞ ሕዝብን የኢትዮጵያና የኬንያ ቦረና አድርጎ ለሁለት መክፈሉን፣ ነገር ግን እነዚሁ ሕዝቦች ሁለት ፕሬዚዳንት ያሏቸው በአንድ አባ ገዳ የሚተዳደሩ ሕዝቦች መሆናቸውን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

‹‹ስለዚህ እነዚህን ድንበሮች መጀመርያ ድንበር አይደሉም ብሎ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቦችን ከፍለዋል፡፡ አልጠቀመም፣›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ችግርም ለመቅረፍ የአፍሪካ መሪዎች ውህደት ብለው ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ጥረት ውስጥ የተሻለ ቅርበት አላቸው የሚባሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ እንዲሁም ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በመለያየት ከሌሎቹ ብሰው እንደተገኙ ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ችግር እንዴት ከመሠረቱ ይፈታ የሚለው ጥያቄ አሁን ላለው አመራር የቤት ሥራ መሆን እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

ሰሞኑን በሶማሊያ ባደረጉት ጉብኝት በፍጥነት የኢኮኖሚ ውህደት እንዲደረግ፣ በኋላም አንድ አገር ለመሆን መስማማታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ብንደመር ትልቅ አገርና ሀብታም መሆን ስንችል ተከፋፍለን አንዱ የሆነ ነገር እያከራየ ለመኖር በሚያደርገው ጥረት ሁላችንም ደሃና ለማኝ ሆነናል፡፡ አይጠቅምም ይቅር ነው ይህ አሁን ያቀረብነው ሐሳብ በመሠረታዊነት የሚያነሳው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይን በተመለከተ ከፓርላማው ጥያቄ ጠብቄ የነበረው  የአልጀርስ ስምምነት ተፈራረሙና ከተፈራረማችሁበት ቀን አንስቶ ስምምነቱ ተፈጻሚ እንደሚሆን፣ በአዋጅ ሕግ አውጥቼ ሳበቃ ለምንድነው ያልተፈጸመው የሚል ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ የፌዴራል ካቢኔ አፅድቆት በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለምክር ቤት አቅርበው ይኼ ምክር ቤትም በመሉ ድምፅ አፅድቆታል ብለዋል፡፡

‹‹የፌዴራል ካቢኔም ውሳኔውን ተቀብሎ ለአፍሪካ ኅብረት አሳውቋል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ በሆነበት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ያሳለፈው አዲስ ሐሳብ የለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የቀረበው የሰላም ጥሪ ለአገሪቱና ለአካባቢ ዘላቂ ጥቅምን እንደሚያስገኝ፣ ይህንን መሠረት በማድረግ የተወሰነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ጦርነት በእያንዳንዱ ቤት ጠባሳ የተወ፣ ሲጀመርም በሁለቱ አገሮች መካከል ሊፈጠር የማይገባው ጦርነት እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

ይህ ሐሳብ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋል እንደሌለበት ለሕዝቦችና ለብሔራዊ ጥቅም መዋል ያለበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ የምናስበው እየተነጋገርን እንተገብረዋለን ብለን ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ ሕዝብ ወንድም ነው፡፡ መሬት ስለሄደና ስለመጣ ወንድምነት አይቀርም፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተወያየው የድንበር መስመር ከማስመር ባለፈ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጨርሶ ስለባድመ ጉዳይ እንዳልተወያየም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተወያየነው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላለው አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ድንበር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን የባድመ ጉዳይ ብቻ ለይቶ ማራገብ ተገቢ አይደለም ብለዋል፣ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የትግራይ ሕዝብ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታለት ለትግራይ ክልል አመራሮች በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳነሳ፣ ለእሳቸውም በድጋሚ ጥያቄውን  እንዳነሳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሚሊሻ ሆነን ለሃያ ዓመታት ያለ ክፍያ ድንበር ጠብቀናል፡፡ እኛም እንደሌላው ሕዝብና አካባቢ መልማት እንፈልጋለን፤›› ሲል የአካባቢው ሕዝብ መጠየቁንም አስረድተዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሲወስን በድጋሚ ሕዝብ ማወያየት አስፈላጊ ስለሆነ አመራሮች ሕዝብ እንዲያወያዩ ጨምሮ የወሰነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ በሚዲያ መገለጹ ሊተች እንደማይገባው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ የድብቅ ፖለቲካ አይሠራም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በመደበቅ፣ በመሸረብና እኛ ብቻ አብስለን  የምናቀርብበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የለም፤›› ብለዋል፡፡

ሕዝብ ሳይወያይበት ተብሎ የተነሳው ሐሳብ መከራከሪያ ሊሆን እንደማይችል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አሰብን ስንሰጥ መቼ ተወያየን? እንደዚህ ዓይነት ምክንያታዊ ያልሆነ ክርክር ለጊዜያዊ ፖለቲካ ትርፍ እንጂ ጠቃሚ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በእስረኞች መለቀቅ ዙሪያ

የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥያቄ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ሕግን በመጣስ የተፈረደባቸውን ግለሰቦች በይቅርታ እየለቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከተጣሱት ሕጎች መካከልም የፋይናንስ አስተዳድር ሕጉ፣ የፀረ ሽብር ሕጉ፣ የፀረ ሙስና ሕጉና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሆናቸውን በመጥቀስ ስለተገቢነቱ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የቀረበው ጥያቄ አሁን ያለውን ሁኔታ የማይገልጽ፣ ብዥታ ያለበትና ማስተካካያ የሚሻ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹መጀመርያ ሽብር ማለት ምንድነው? የሚለውን ጥያቄና እስከ ዛሬ በዚህ መንገድ ያተረፍነው ምንድነው? የሚለውን ሙሉ አድርጎ ማየት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ሽብር ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ኃይል መጠቀምን ጭምር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ደግሞ ለዚህ መዛነፍ ኃላፊነት ሊወስድ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ መከላከያውንና የደኅንነት ተቋሙን ከፖለቲካ ነፃ አድርጎ ማደራጀት እንደሚገባ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተቋቋሙት ግን እንደዚያ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹ሕገ መንግሥት በሕግ መሠረት የተያዘን ግለሰብ ግረፉ፣ ጨለማ ቤት አስቀምጡ ይላል እንዴ?›› በማለት የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹መግረፍ፣ ጨለማ ቤት ማስቀመጥ የእኛ የአሸባሪነት ተግባር ነው፤›› በማለት በጠንካራ ሁኔታ የመንግሥትን ተግባር ኮንነዋል፡፡

ይህ ተግባር በፌዴራል መንግሥት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ቀበሌና ወረዳ ሲፈጸም እንደቆየም ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢሕአዴግ በግልጽ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቁን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጋችሁ ስትመርጡኝ እዚሁ ቆሜ በይፋ ይቅርታ ጠይቄያለሁ፤›› ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

‹‹ይኼ መልካምና ደግ ሕዝብ ይቅር ብሎ ዕድል ሰጥቶናል፡፡ ያንን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ እኛ ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ድርጊት እንዳላደረግን ሳይሆን፣ ዓይተንና ገምግመን ይቅርታ ጠይቀናል፣ ሕዝቡም ይቅርታ አሳይቶናል፤›› ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ይቅርታ ያደረገው አመራሩ እስር ቤት ቢገባ ለአገር አይጠቅምም ብሎ መሆኑን፣ በይቅርታ አንድ ቦታ ይቁም በሚል እሳቤ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹ለእኛ ይቅርታ ያደረገው ሕዝብ ለእነሱም ጭምር ይቅርታ የማድረግ ፍላጎት አለው የሕዝቡን ስሜት ታውቁታላችሁ፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

‹‹ሰው የገደሉ መፈታታቸው እንደተገለጸው ለተጎዱ ቤተሰቦች ሕመም ነው፡፡ ነገር ግን የደርግ ባለሥልጣናትን ፈተን የለም ወይ? ይቅርታ እኮ እንዲህ ነው፣ ይቅርታ ድንበር የለውም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሁሉም በይቅርታ የተፈቱት በሙሉ ሕግን መሠረት አድርገው እንደሆነ፣ እንዲሁም የሕግ መዛነፍ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሳውን ግጭት ከመሠረቱ ለመፍታት ይቻል ዘንድም፣ የፌዴራሊዝም አወቃቀር ላለፉት 27 ዓመታት ያስገኘውን ጥቅምና ጉድለት ለመለየትና መፍትሔ ለማበጀት ኮሚሽን እንደሚቋቋም ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የፈጠረው ስሜት

ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች በፓርላማ የተገኙትን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሾችና ማብራሪያዎች፣ የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታን በማስቀየር በቴሌቪዥን ሲከታተሉ ተስተውሏል፡፡ ምናልባትም የአገሪቱ ፓርላማ የሕዝቡን ትኩከረት የሳበበት ዕለት እንደነበር መግለጽ ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በሕገ መንግሥት ጉዳዮች የሕግ ባለሙያና ጠበቃ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ታምራት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሪፖርትና ማብራሪያ አድንቀዋል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችና የመንግሥት መስተጋብር ጤናማ ሊሆን የሚችለው ሥልጣኑ በእውነትም የተገደበ መንግሥት ሲኖር ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም መንግሥት በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽምና የአገሪቱ ሀብት ሲበዘበዝ፣ የተገደበ የመንግሥት ሥልጣን ባለመኖሩ ዜጎች በሚመለከታቸው ጉዳይ ላይ ትንፍሽ እንዳይሉ በመደረጋቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለትግራይ ሕዝብ በሌሎች አካባቢዎች የተያዘውን ግንዛቤ በመተቸት፣ የትግራይ ልጆች እንኳን ሊጠቀሙ ይቅርና በውኃ ጥቅም ላይ መሆናቸውን፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ያልተሟላ ነው ማለታቸው የተሳሳተ ግንዛቤን የሚያርም ስለመሆኑም አቶ ኤፍሬም እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው እስረኞች በይቅርታ መፈታታቸውን ከሕግ አግባብ ጋር አያይዘው ጥያቄ ያቀረቡት የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው፡፡ ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ አልተደሰትኩም ቅሬታ አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

ለቅሬታቸው እንደ ምክንያት የሚያነሱት ላቀረቡት ጥያቄ በቂ ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተጠምደው ነበር የሚል ነው፡፡

‹‹እኔ የፓርቲ አባል ብሆንም ያቀረቡኩት ጥያቄ ያመንኩበትንና የሕግ ጥሰት ስለመኖሩ ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሙሉ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ቀደም ብሎ የተሠራን ስህተት በመጥቀስ፣ ስህተትን በስህተት እንደማረም የሚመስል ምላሽ ነው የሰጡት፤›› በማለት ተችተዋል፡፡

‹‹ስህተቱ ሲፈጸም የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የካቢኔ አባል አልነበሩም እንዴ?›› በማለት ጥያቄ የሚያነሱት የምክር ቤት አባሏ፣ የተሰጣቸው ምላሽ እንዳላሳመናቸው ተናግረዋል፡፡

በፀረ ሙስና አዋጁ አማካይነት ተይዘው መንግሥት ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ ግለሰቦችን በተመለተ የሰጡትን ማብራሪያ ብቻ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮ ኤርትራን የድንበር ጉዳይ አስመልክቶ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የምክር ቤቱ አባል አቶ መሠረት ጀማነህ በበኩላቸው፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ማብራሪያ ረክቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ጥያቄውን ያቀረብኩት የሕዝብ ውይይት እንዲኖር ከመፈለግ እንጂ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም እንዲወርድ የእኔም ፍላጎት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚሁ አግባብና በዝርዝር በመመለሳቸው ከበቂ በላይ ተደስቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በዚሁ በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ሆርዶፋ በቀለ ናቸው፡፡

አቶ ሆርዶፋ የአልጀርሱ ስምምነት ከፀደቀበት ወቅት አንስቶ እስከ አሁኑ ወቅት ድረስ የፓርላማው አባል በመሆን ያገለገሉ አንጋፋ  የሕዝብ ተወካይ ሲሆኑ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ፓርላማው የአልጀርሱን ስምምነት በወቅቱ ማፅደቁን አሁንም ለሁለቱ ሕዝቦች፣ እንዲሁም በአካባቢው በልጦ ለመገኘት የተወሰደውን ዕርምጃ እደግፋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከይቅርታ ጋር በተገናኘ የሰጡት ማብራሪያና በግንባርም እየፈጸሙት የሚገኘው ተግባር አገሪቱን መልሶ የሚያድስ ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ በተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ማዕረጋቸው ተገፎ ከመከላከያ ሠራዊት የተሰናበቱ ጄኔራሎችን ክብርና ማዕረግ እንዲመለስ ማድረጋቸው እጅግ አስደሳች እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አገራቸውን ለስድስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት የነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) የቀድሞ ፕሬዚዳንት የሚል የማዕረግ ክብር ከእነጥቅማ ጥቅሙ ሊመለስም ይገባልም ብለዋል፡፡

ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት የዶ/ር ነጋሶ ሕገ መንግሥታዊ መብትና ጥቅማ ጥቅም የተነጠቀው በፖለቲካ ምክንያት እንደሆነ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...