Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለሁሉም ጊዜ አለው!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ቆያችሁልኝ የተወደዳችሁ? እኔማ ናፍቆት እያብሰከሰከኝ ከረምኩ፡፡ መቼም ደላላ ፍቅር አያውቅም የሚል ስንት አለ መሰላችሁ? ፍቅር ለመስጠት ምን ያንሰንና ነው? ወዳጆቼ ዘመን ተቀይሯል፡፡ ፍቅራችንንም ለመግለጽ መሬትና መኪና ካጋዛችኋቸው ሰዎች ጋር ‘ሰልፊ’ ተነስቶ መልቀቅ የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ መኪናውን ወይም ቤቱን ከኋላችን አድርገን፣ በግራ እጄ ሰውዬውን አቅፌ በቀኝ አውራ ጣቴ ደግሞ ወደኋላ እያመለከትኩ የተነሳኋቸውን ፎቶዎች ተመልክታችሁ ‘ላይክ፣ ሼር’ ያደረጋችሁትን ሁሉ ሳላመሠግን አላልፍም፡፡

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ጠቅላዩ ፎቶ ያልተነሱት ከባድመ ጋር ብቻ ነው. . . ›› እያለ ሲሳለቅ ነበር፡፡ ባሻዬ በሐሳቡ ባይስቁለትም፣ በልጃቸው ቀልድ ተማረው፣ ‹‹የሌላው ይገርምሃል? ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ፎቶ ተነስቶ ሲለጥፍ ታየዋለህ፤›› በማለት ይመልሱለታል፡፡ ይኼን ጊዜ ልጃቸው፣ ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ እንዲሁም ባድመ ነሽ›› በማለት ሳቀ፡፡ የባሻዬ ልጅ ያለወትሮው እየቀለደ፣ ‹‹ዋናው ሰላም ነው፡፡ ሰላም ይምጣ እንጂ እንኳን ባድመንና ሽራሮን ትግራይንም ጨምረን እንሰጣለን፡፡ ብቻ ሰላም ይውረድልን. . . ›› እያለ ባሻዬን እያየ ይስቃል፡፡ ወዳጆቼ ዘመኑ ልጅ አባቱ ላይ የሚቀልድበት ነው፡፡ ባሻዬም የልጃቸው አሽሙር ገብቷቸው፣ ‹‹እንዲህ የሚባል ቀልድ የለም፡፡ የእኛ የሆነው የእኛ ነው፡፡ እስከ ዛሬም ስንዋደቅለት ኖረናል፡፡ የእኛ ያልሆነው ደግሞ የእኛ አይደለም፡፡ በግድ የእኛ ልናደርገው መሞከር ራስ ወዳድነት ነው፤›› በማለት መልስ ሰጡት፡፡

ልጃቸው ዛሬ ሊፋታቸው የወደደ አይመስልም፡፡ ‹‹እኔ የምለው ዘንድሮ ግን ወዴት ወዴት እያልን ነው?›› በማለት ጥያቄ ሲያቀርብ ባሻዬ ተቀብለው፣ ‹‹ወደ ሰላም፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ አገራዊ መግባባት. . . ›› በማለት ምጥን ያለች መልስ ሰጡት፡፡ ይህን ጊዜ ልጃቸው፣ ‹‹መሬት በኢንቨስትመንት ሰበብ ለውጭ ባለሀብቶች ተሰጥቶ፣ መመኪያችን የነበረው አየር መንገዳችን በከፊል ተሸጦ፣ እነ ቴሌ፣ የኃይል ማመንጫዎቻችን ሳይቀሩ ተቸብችበው ምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ነው እየገባን ያለነው?›› በማለት አባቱን ሆን ብሎ በጥያቄ ያሰቃያቸዋል፡፡

ባሻዬ በልጃቸው ሐሳብ ቢናደዱም፣ ‹‹ምን ይላል ይኼ? እንዲያውም እንደ እናንተ ዓይነቱን ገልቱ አስተሳሰብ ያለውን ነበር ወስዶ መቸብቸብ፤›› በማለት ሲቆጡት መቼም አባት ናቸውና እርሱም እንደ ልጅ፣ ‹‹አይቀርልንም ቢመቻቸው ያስማሙናል፤ ያንእያለ ሌላ የሚያናድድ መልስ መለሰላቸው፡፡ ይኼን ጊዜ ባሻዬ በተቀመጥንበት ጥለውን ሄዱ፡፡ አሁንም ሊፋታቸው አልፈለገም፣ ‹‹እንዴ አባዬ ተሸነፍክ ማለት ነው? ገና ለገና ይህችን ተናገረኝ ብለህ የተቀመጥክበትን ጥለህ መሄድህ አግባብ አይደለም፡፡ ላመንክበት ነገር መዋደቅ አለብህ. . . ›› እያለ ከአጠገቡ እስኪርቁ ድረስ በነገር ተገተጋቸው፡፡

ወዳጆቼ በናፍቆት ስንጠብቀው የነበረው የዓለም ዋንጫ እነሆ እሱ ዘንድ ባንሄድ እሱ እዚህ ደርሶልናል፡፡ ሰብሰብ ብለን በሞቅታ ውስጥ ሆነን ጀምረነዋል፡፡ የባሻዬ ልጅ ገና አንድም ጨዋታ ከማድረጓ በፊት ዋንጫውን አንስቶ ለፈረንሣይ ችሯታል፡፡ እኔ ደግሞ ‘ብራዚል ብራዚል’ እያልኩ ነው፡፡ ባሻዬ የናይጄሪያ ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው፡፡ እምነታቸውም ቢሆን እንደኛው ነው፡፡ ‹‹ቡድኔ ናይጄሪያ ዋንጫ ይዞ ይመለስልኛል፤›› ብለው ይመኛሉ፡፡ ምነው ያንን ኦክቶፐስ አግኝቼ በጠየቅሁትና ውጤቱን አውቄ ለማንጠግቦሽ ሳልናገር ትንሽ ብር ብመድብ ብዬም ተመኘሁ፡፡ ታዲያ ያለምንም ላብ የመጣ ገንዘብ ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ድሮውንም አንዳንድ ሰዎች ደላሎች ያልደከሙበትን ገንዘብ ነው የሚያፍሱት ብለው ስማችንን ማጥፋታቸው ስላልቀረ በደንብ እንፈሰዋ፡፡ ስለዚህ ብራዚል ዋንጫውን ይበላል፡፡ ይህንን የሚጠረጥር ካለ ይመድብ፡፡

እኔ ቁማር አልወድም፡፡ ደላሎችማ እስከ ዋንጫው ድረስ መታገሻ የላቸውም፡፡ ገና በመክፈቻው ጨዋታ ላይ ነው ማስያዝ የጀመሩት፡፡ ሙሉ ጨዋታውን ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ የዚያን ያህል ማን ይታገሳል? ታዲያስ ካሉማ የመጀመርያውን ጎል ማን ያገባል ተባብለው ረብጣ ብር ይመድባሉ ኧረ ብለው ተገርመው ሳያበቁ የሚያገባውን ሰው ስም ይመርጡና ደግሞ በእሱ እንደገና ሌላ ይመድባሉ በዚህ ቢያበቁ መልካም የመጀመርያው 45 ደቂቃ የኳስ ቁጥጥር ማን ዘንድ ይሆናል በማለት ሌላ ይመድባሉ፡፡ በመጀመርያ ኮርና፣ በመጀመርያ የእጅ. . .  እያሉ በእያንዳንዷ ደቂቃ ውስጥ በምትፈጠረው ቅፅበት ያስይዛሉ፡፡ በዚህ መሀል ስንቶች ቤታቸውን ሳይቀር ይሸጣሉ፡፡ ታዲያ እኔ አንድ ብራዚልን ብዬ ከ64 ጨዋታዎቹ ብመድብ ምን ይለኛል? ሁሉም ነገር ቁማር ነው ብዬ ላነሳሁት ሐሳብ የባሻዬ ልጅ ሲመልስ፣ ‹‹በተለይ ፖለቲካው!›› በማለት አስፈግጎኛል፡፡ በተለይ ሰሞኑን ሕወሓት ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ላይ ሲሳለቅ ነበር የከረመው፡፡

እንዲህ በማለት የቀለደው እኔን አስፈግጎኛል፡፡ ‹‹ሰውዬው ወደ አንድ ሆቴል ይገባና ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ አስተናጋጁን ይጠራዋል፡፡ አስተናጋጁም በፍፁም ትህትና ወደ ሰውዬው ይቀርብና ምን መታዘዝ እንደፈለገ ይጠይቀዋል፡፡ ሰውዬውም ትንሽ አሰብ አደረገና አሩስቶዋችሁ እንዴት ነው? በማለት ይጠይቀዋል፡፡ አስተናጋጁም ማን አቅምሶኝ? ማን አድርሶኝ? በማለት መለሰለት፤›› ቢለኝ ፈገግ አልኩ፡፡ ማን አቅምሶኝ? ማን አድርሶኝ?

የኢትዮጵያ ሕዝብ መጠየቅ ነበረበት በተባሉት ጉዳዮች ላይ ሲያብራራ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ማማከር መጀመር ያሰቡት ከዓብይ መመረጥ በኋላ ነው እንዴ?›› በማለት ላቀረበልኝ ጥያቄ፣ ‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ ኢሕአዴግ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ. . .  ሕዝብን የሚያሳትፍ. . . ›› እያልኩ ሳብራራ ከአፌ ላይ መንጭቆ፣ ‹‹ሕዝብ? ማማከር? ማ? የኢትዮጵያ ሕዝብ? አማክሮት? በምን ጉዳይ ላይ? መቼ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ማን አድርሶት? ማን ጠርቶት?›› እያለ በምሬት ተንጣጣብኝ፡፡

ባለፉት ሰባ ቀናት ውስጥ እንዲህ ያለ ቁጣ አይቼበት አላውቅም፡፡ ባሻዬም ሁኔታውና የልጃቸው ጉዳይ አስጨንቋቸው ጠቅላይ ከተመረጡ ጀምሮ ሥርዓቱን ይዞ የነበረው የደም ግፊታቸው ጨምሮ ራስ ምታቱ ቢያንገላታቸው አናታቸውን ጋቢ በሚያህል ፎጣ ጠፍንገው ሐኪም ካዘዘላቸው መድኃኒት በላይ እጥፍ ወስደው ነው የዋሉት፡፡

በተለይ ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢ የተነሱትን አለመግባባቶች ተመልክተው፣ ‹‹ገና እንዲህ ያሉ የምናጭዳቸው በርካታ ፍሬዎች አሉን፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ዘመን የተዘሩ ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን አራሙቻውን እያጨድን መልካሙን ዘር በመዝራት የሚመጣው ትውልድ የሚያጭደውን መልካም ዘር መዝራት አለብን፤›› አሉ ልክ ናቸው፡፡ አራሙቻውን ማጨድ ተገቢ ነው፡፡ መልካም ዘር የሚዘራው አራሙቻው ሲጠፋ ነው፡፡ አራሙቻውን ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጊዜ አለው! መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት