ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አልጋወራሽን ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከተቀበሉ በኃላ ራሳቸው በሚያሽከረክሩት አውቶሞቢል እንግዳውን አሳፍረው ወደ ጉብኝት መዳረሻቸው ማቅናታቸው ታወቀ።
ጠቅላይ ሚትሩ ይህንን ያልተለመደ ተግባር የፈጸሙት ዛሬ ሰኔ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲሆን ለሥራ ጉብኝት ከቀትር በኋላ አዲስ አበባ የደረሱትን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አልጋወራሽ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አቀባበል ካደረጉላቸው በኃላ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቢሮ ለሪፖርተር ገልጿል።
አልጋ ወራሹ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡ፣ በቅርቡ የተሾሙት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን በአቀባበል ሥነ ስርዓቱ ተገኝተዋል፡፡ ለእንግዳው ክብር ሲባልም ሃያ አንድ ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተጋበዙት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ይወያያሉ።