Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​የጃፓን ቡና ኩባንያ ከቀናት በኋላ በኢትዮጵያ የቡና ጥራት ውድድር ያካሂዳል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም ግዙፉ የቡና ኩባንያ የሆነው ዩሺማ ኮፊ ካምፓኒ ሆልዲንግ ግሩፕ (ዩሲሲ) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡና ጥራት ላይ ያተኮረ ውድድር ሊያካሂድ መሆኑን ይፋ ካደረገ ከወራት በኋላ በመጪው ዓርብ፣ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. Anchorውድድሩን እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከጃፓን ኤምባሲ በተገኘው መረጃ መሠረት ኩባንያው የጅማ ጫካ ቡናን በመግዛት ወደ ጃፓን ኤክስፖርት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ለሚያመርቱ ገበሬዎች ማበረታቻ ይሆን ዘንድ በታሰበው የጥራት ውድድር ላይ ኩባንያው በጅማ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት በለጠና ጌራ አካባቢዎች የሚገኘውን የጫካ ቡና ሲገዛ መቆየቱም ይታወቃል፡፡ ኩባንያው በተደጋጋሚ በቡና ጥራት ላይ ከፍተኛ ጃፓናዊ ባለሙያ እያስመጣ ለአካባቢው አርሶ አደሮችና ቡና ላኪዎች ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የኩባንያውን ማኅበራዊ ኃላፊነት የመወጣት ስትራቴጂ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ እንቅስቃሴም፣ ወደፊት በቋሚነት ሊካሄድ ይችላል የተባለውን የቡና የጥራት ውድድር ለማካሄድ ከአገር በቀሉ መታድ የግብርና ልማት ኩባንያ (ካቡ ኮፊ በተባለው ምርቱ ይታወቃል) ጋር የጥራት ውድድር ለማካሄድ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በመጋቢት እንደሚካሄድ ይጠበቅ የነበረው ውድድር 24 ሺሕ አምራቾችን የሚያሳትፍ ሲሆን፣ አሸናፊ የሚሆኑት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ተወዳዳሪዎች ከመደበኛው የቡና ዋጋ ከአሥር እስከ 30 ከመቶ ጭማሪ የሚደረግበት የስድስት ሺሕ ኩንታል ቡና ግዥ እንደሚፈጸምላቸው ኩባንያው ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡ የጥራት ተወዳዳሪዎች ቡናዎቻቸውን ለውድድር ሲያቀርቡ አብረው የሚከተሏቸው የመወዳደሪያ መስፈርቶችም እንደሚሠራጩ ከዚህ በፊት የዩሲሲ ኩባንያ ኃላፊዎች አስታውቀው ነበር፡፡

ጃፓን ከአሜሪካና ከጀርመን ቀጥላ በዓለም ሦስተኛ ቡና የምትገዛ አገር ስትሆን፣ ከጣልያን፣ ከፈረንሳይና ከዩናይትድ ኪንግደም በመቅደም በቡና ጠጪነት ከሚታወቁት አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ዩሲሲ ኩባንያ በበኩሉ በጃፓንና በእስያ ቡና ቆልቶ በማዘጋጀት ግንባር ቀደምነቱ ተቆናጧል፡፡ በዓለም ሰባተኛ ደረጃ መያዙን የኩባንያው ወኪሎች ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ ዘዴዎች ቡና አዘጋጅቶ ለጃፓናውያን፣ ለእስያውያንና ለአውሮፓውያን የሚያቀርበው ይህ ኩባንያ፣ ቡናን በዱቄትና በፈሳሽ መልክ እንደለስላሳ አሽጎ በማቅረብም ስሙ የሚጠራ ተቋም ነው፡፡ በጃፓን የቡና ማሠልጠኛዎችንና የቡና ሙዚየም ያለው ዩሲሲ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በስፔን፣ በኔዘርላንድስ፣ በስዊዘርላንድና በፈረንሳይ አምስት የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች አሉት፡፡ ከተመሠረተ ሰማንያኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ይህ ኩባንያ በሥሩ 62 ኩባንያዎችን በማቀፍ በዓመት 185 ሺሕ ቶን ቡና በማገበያየት የ2.8 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ያከናውናል፡፡

ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ጃፓን በተላከ ቡና ጆንያ ላይ በተገኘው የኬሚካል ቅሪት ሳቢያ ጃፓን ከኢትዮጵያ የሚላከውን ቡና አግዳ ብትቆይም፣ አሁንም የጥራት ጉድለት በሚላክላት ቡና ላይ እየታየ በመሆኑ የቀድሞውን ያህል እየገዛች አለመሆኗን ማስታወቋን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ተጠይቀው እንደገለጹት፣ ከስድስት ዓመት በፊት በፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ሳቢያ ጃፓን ትገዛ የነበረው ቡና ለተወሰነ ጊዜ ከተቋረጠ በኋላ መልሶ ማገገም ቢጀምርም ከስድስት ዓመት ወደነበረበት ደረጃ ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ጥራት ያለውና ከፍተኛ ደረጃ የተሰጠው ቡና ተብሎ የሚላከው ጥራቱም ደረጃውም ዝቅተኛ ከሆነው ጋር እየተደባለቀ እንደሚገኝ አምባሳደር ሱዙኪ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም የሚፈለገውን ያህል ቡና ወደ ጃፓን መላክ ባይቻልችም በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ተነግሯል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በዓመት ከ170 እስከ 190 ሺሕ ቶን ቡና ለዓለም ይቀርባል፡፡ ከዚህ መጠን ውስጥ የጃፓን ድርሻ ግን ከ10 ከመቶ እንደማይበልጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአንፃሩ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ጃፓን ይላክ የነበረው የቡና መጠን ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት እስከ 25 ከመቶ ይደርስ ነበር፡፡

የኬሚካል ንክኪውን ለማስቀረት የጃፓን ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በጃፓን መንግሥት ድጋፍ የላቦራቶሪ ማዕከል ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ከመደበኛው ቡና ጋር ተቀላቅሎ እየተላከ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ቡና የጃፓንን የጥራት ደረጃዎች ማሟላት ተስኖት እንደሚገኝ አምባሳደሩ ይናገራሉ፡፡ ይህ ቢስተካከል ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ጥራት ያላቸው ልዩ ቡናዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ አምባሳደር ሱዙኪ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥሬ ቡና ባሻገር አገር ውስጥ የተቀነባበረ ቡና የመላክ ሐሳብ እንዳላት ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ይህንን ለማድረግ ግን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪው መዳበር እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

                                                                                 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች