Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የመጣን መቀበል የሄደን መሸኘት!

‹‹አራት ኪሎ ፒያሳ›› የሚለውን የወያላ ድምፅ ከመስማታችን ተንጋግተን የቆመው ታክሲ ውስጥ ገባን፡፡ ዳሩ ግን ገና ተጨማሪ ለአምስት ሰዎች የሚሆን ቦታ ነበር፡፡ ወያላውም እኛ ከገባን በኋላም ‹‹አራት ኪሎ ፒያሳ›› እያለ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ መነሻችን መገናኛ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሰው ላይ ተረማምዶ ቦታ መያዝዎን ካረጋገጡ በኋላ ትርፍ ቦታ እንዳለ ሲገነዘቡ ያን ጊዜ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ መገናኛ ከወዲህ ወዲያ ሰው ይተራመሳል፡፡ አንድ ተሳፋሪ የሰውን ግርግር በግርምት እያስተዋለ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ መቶ ሚሊዮን ከሆነ ዘጠና ሚሊዮኑ ያለው መገናኛ ነው…›› በማለት የራሱን የተጋነነ አስተያየት ሰጠ፡፡

ይህንን አስተያየት የሰማው አንድ ወጣት፣ ‹‹ብራዘር ከቁጥር ጋር ያለህ ኅብረት እንዴት ነው?›› በማለት አሽሙር አዘል ጥያቄ አቀረበለት፡፡ የመጀመርያው ሰውዬ እንደ መቀለድ እያለ የሰጠው አስተያየት ተቃውሞ ማስነሳቱ ያስገረመው ይመስላል፡፡ ዳሩ ግን በዚያው ሐሳብ ለመከራከር ወስኖ በሌላ አዝናኝ ሐሳብ መጣ፣ ‹‹እርግጠኛ ነኝ የሰጠሁት ግምት እውነትነት አለው፡፡ ከፈለግክ ይቆጠር…›› በማለት ሐሳቡን አጠናከረ፡፡ ይኼን ጊዜ ጥያቄውን ያቀረበው ወጣት ድምፀ ተዓቅቦ አደረገ፡፡

ታክሲያችን ሁለት አዳዲስ ተሳፋሪዎችን አስተናገደች፡፡ የጦፈ ወሬ ይዘው ነበር የተቀላቀሉን፡፡ ወሬያቸው የሚያጠነጥነው ስለኢትዮ-ኤርትራ እንደነበር ወዲያው አፍታም ሳይቆይ ተገለጠልን፡፡ ታክሲ ውስጥ መኖራችንን ያስተዋሉም አይመስሉም፡፡ አንደኛው፣ ‹‹የኤርትራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውሳኔ የተደሰተው ባድመ የዚያን ያህል አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖበት አይደለም፤›› በማለት ለጀመረው ሐሳብ አብሮት ያለው ወጣት የተስማማበት አይመስልም፡፡ እንዲህ በማለት ሙግት ውስጥ ገባ፣ ‹‹ታዲያ ለምንድነው በመላው ዓለም የሚገኙ ትውልደ ኤርትራውያን በደስታ የፈነጠዙት?›› ሲል ወሳኝ ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ወጣቱም በደስታ ወደ መልሱ ተንደረደረ፡፡ ‹‹አየህ በኤርትራም ሆነ በመላው ዓለም ተበትኖ ያለው የኤርትራ ሕዝብ ባድመ ላይ የመስፈር ዓላማ ስለሰነቀ አይደለም፤›› በማለት ማብራሪያውን ቀጠለ፡፡

ሌላ አዲስ ሰው አስተናግደናል፡፡ በጣም ቆንጆ ናት፡፡ ታክሲ ውስጥ እንደገባች  ለአፍታም ቢሆን ትኩረታችንን ወሰደችው፡፡ ሁለቱ ወጣቶች ግን ሙግታቸውን ገፍተውበታል፡፡ የመጀመርያው ወጣት፣ ‹‹እንኳንስ ባድመ ይቅርና መሀል አስመራ ላይ እንኳን ወጣት የሚባል ነገር እኮ አይታይም?›› በማለት ብርቱ ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ይበልጥ ተመስጦ፣ ‹‹እና ለምንድነው ደስ ያላቸው?›› በማለት ጥያቄ አቀረበለት፡፡

በነገራችን ላይ ቆንጂት መስታወቷን አውጥታ በውበቷ ላይ ውበትን ለመጨመር እየተፍጨረጨረች ነበር፡፡ ይህንን በትኩረት ሲከታተል የነበረ አንድ ጎረምሳ፣ ‹‹ኧረ እዚህ ውበት ላይ ምንም ባትጨምሪበት ነው የሚሻለው፤›› በማለት የጎረምሳ አስተያየት ሰጣት፡፡ ይኼን ጊዜ ቆንጂት ከመኳኳያዋ ጊዜ ሳትቀንስ መኳኳሏን እንደ ቀጠለች፣ ‹‹አየህ የተሰጠህን ነገር በአግባቡ መጠበቅ አለብህ፤›› የሚል አጭር መልስ ሰጠችው፡፡ ወጣቱም፣ ‹‹ምናለበት እንዲያው እግዜሩ አንቺን ሰጥቶኝ ዕድሜ ልኬን ስጠብቅሽ በኖርኩኝ?›› አላት፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ዓይኗን ከያዘችው መስታወት ላይ ቀና አድርጋ ዞር ብላ ተመለከተችው፡፡

ወጣቱም፣ ‹‹በሙሉ ዓይንሽ ስለተመለከትሽኝ እጅግ አብዝቼ አመሰግናለሁ፡፡ የሚያየን አጥተን እንጂ የሚታይ ነገር ጠፍቶብን አልነበረም፤›› በማለት አሰብ አድርጎ፣ ‹‹እንዲህ ባሉ ውብ ዓይኖች መታየትን የሚያክል ታላቅ መታደል ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ገና የዓይኖችሽ ሽፋሽፍቶች ተከፍተው ዕይታሽን ወደ እኔ ስታደርጊ ለዘመናት ተጫጭኖኝ የነበረው የብቸኝነት ጋኔል እንደ ጉም ከላዬ ላይ ሲተን ታወቀኝ፤›› አለ፡፡ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ንግግሩን በማስረዘም፣ ‹‹እንዲያው አሁን ላንቺ ኤላንትራ ገዝቶ የሚሰጥ ጠፍቶ ነው በታክሲ የምትጋፊው?›› በማለት ጥያቄ ሰነዘረላት፡፡ ቆንጂትዬ ምን ብትል ጥሩ ነው? ‹‹ጥሩ ትጫወታለህ፡፡ ለምን በመጽሐፍ መልክ አታሳትመውም? ምናልባት ብዙ አንባቢ ታገኝ ይሆናል…›› ብላ በነገር ኮረኮመችው፡፡ በዚህ ብታበቃ እንኳን ለወጣቱ የእግር እሳት እንደሆነችበት መገመት አያዳግትም፡፡ ዳሩ ግን ቀጠለች፡፡ ‹‹ደግሞ እኛ ሴቶች ተቀባዮችና ተመፅዋቾች ናቸው ብለህ ማሰብህ ቀሽምነትህን ያሳያል፡፡ ለዛሬ ነጥብ ጥለሃል…›› ብላ ወረፈችው፡፡ ወቸ ጉድ?

‹‹የማንንም ዕርዳታ የማልፈልግ የራሴ ሥራ ያለኝ ሙሉ ሰው ነኝ፡፡ ራሴን ችዬ ራሴን ሆኜ የምኖር ምሉዕ ሰው ነኝ፤›› እያለች፡፡ ወጣቱ የሚለውን አሳጣችው፡፡ እሱ ደንግጦ፣ ‹‹ኧረ በፈጠረሽ ወንድም የለሽም? ወይም አባት የለሽም…›› እያለ በወንድ ፆታ የሚወከሉ የቤተሰብ አካላትን በመጥራት ተማፀናት፡፡ ‹‹በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ›› ይባል የለ? እንደ ቀላል ዘው ብሎ የገባበት ነገር መማፀን ውስጥ ከከተው ምን ይደረግ ታዲያ?

ይህ ሁሉ ታሪክ ሲፈጸም ሁለቱ ሰዎች በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ላይ እንደተጠመዱ ነበር የቆዩት፡፡ ወጣቱ የኤርትራ ሕዝብ እንኳንስ ባድመ ሊሄድ ‹‹መሀል አስመራ ላይ ወጣት የሚባል የለም፤›› የሚለው ሐሳብ ኮርኩሮታል፡፡ ጥያቄውንም በማጠናከር፣ ‹‹መልስልኛ ለምንድነው የኤርትራ ሕዝብ በደስታ የፈነጠዘው?›› በማለት ጥያቄውን መልሶ አቀረበለት፡፡

ጓደኛውም ሲመልስ፣ ‹‹አየህ የኤርትራ መንግሥት ለብዙ ዘመናት ሕዝቡን ሲዋሸው ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያጠፋህ ተነስቷል፡፡ ሊገድልህና አገርህን ሊወርስብህ ነው እያለ በርካታ የጥላቻ ሐሳቦችን በሕዝቡ ላይ ሲነዛ ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ ወሬ ውሸት እንደሆነ ሕዝቡ በአንድም በሌላም አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ መሬትህን ወስደውብሃል፣ ታጠቅና ለአገርህ ዘብ ቁም እያለ ሲያውጅ የነበረው የኤርትራ መንግሥት ነው፡፡ አሁን መሬትህ ተመልሶልሃል፣ ጠላት ያልካቸውም ኢትዮጵያውያን ከዚህ በኋላ ሰላምና ዕርቅ ነው የምንፈልገው በማለታቸው የኢሳያስን መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ የጣለ ጉዳይ ነው፤›› በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጠ፡፡

ይህን ጊዜ በስንት መከራ ታክሲያችን ሞልታ የመገናኛን አደባባይን ዞረን ሽቅብ ተመልሰን ወደ አራት ኪሎ በሚወስደን ዋና መንገድ ውስጥ እየገባን ነበር፡፡ ተሳፋሪ አልሞላ ብሎት ሲያንጎራጉር የነበረውም ወያላ አሁን ተቀላቅሎን ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል፡፡ ‹‹ኢሳያስ አፈወርቂ አሁን ደግሞ ምን ይል ይሆን የሚለው የኤርትራውያን ሐሳብ በመላው ዓለም እየተጠናከረ ነው፤›› የሚል ሐሳብ የሰነዘረው ስለኤርትራ ብዙ ጥናት ያደረገ የሚመስለው ወጣት ነው፡፡

ቀጥሎም በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥትን ጥገኝነት ጠይቆ ተቀባይነት በማጣቱ ወደ ኤርትራ ሲመለስ ግብፅ ውስጥ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ገብቶ ራሱን ላጠፋው ወጣት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጹ፡፡ ሟቹ ወደ ኤርትራ ከምመለስ በማለት የወሰደው ዕርምጃ ነበር የሐዘኑ መነሻ፡፡ ‹‹ከዚህ ሁሉ በላይ የሚያሳዝነው አለ፡፡ ቤተሰቦቹ ልጃችን ይመጣልናል በማለት አስመራ አውሮፕላን ማረፊያ እየጠበቁት ባሉበት ወቅት ነው መታጠቢያ ቤት ውስጥ ራሱን አንጠልጥሎ የተገኘው…›› በማለት ሁላችንንም ሐዘን ውስጥ ጣለን፡፡

‹‹እኛም ከመዲናችን አዲስ አበባ ሆነን በግብፅ ለሞተው ኤርትራዊ ወንድማችን ነፍስ ይማር እያልን፣ ከግብፅ ለመጡት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ደግሞ እንኳን ደህና መጣችሁ ብንላቸውስ? ያለን ዘግይቶ ወሬውን የተቀላቀለው ወያላው ነበር፡፡ ‹‹የመጣውን በፍቅር ተቀብሎ ማስተናገድ ልማዱ የሆነው ሕዝባችን የሚሄደውንም በአክብሮት መሸኘቱ ልብ ይባልልን፤›› ሲል አንድ ወጣት፣ ጉዟችን እየተገባደደ ነበር፡፡ የመጣን መቀበል የሄደን መሸኘት ተገቢ አይደል? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት