Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​‹‹በድርቁ ላይ በቅርበት ክትትል እየተደረገ መሆኑን አይተናል››

ማርክ ጎልድሪንግ፣ የታላቋ ብሪታንያ ኦክስፋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ማርክ ጎልድሪንግ የታላቋ ብሪታንያ ኦክስፋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ከዓለም አቀፍ የልማት ሥራ ጋር በተገናኘ ከአሥር ዓመታት በላይ የሠሩት ጎልድሪንግ ኦክስፋምን ከመቀላቀላቸው በፊት የሜንካፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ ጎልድሪንግ የቪኤስኦ ዋና ሥራ አስፈጻሚም የነበሩ ሲሆን፣ በተመድ የልማት ፕሮግራም በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማት ተቋም ውስጥም አገልግለዋል፡፡ ጎልድሪንግ ከኦክስፎርደ ዩኒቨርሲቲ ሕግ እንዲሁም ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ሶሻል ፕላኒንግ አጥንተዋል፡፡ ጎልድሪንግ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ በማለት የኦክስፋም ኢትዮጵያ ሥራዎችንና በድርቁ የተጎዱ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል፡፡ አስራት ሥዩም ጉብኝታቸውን በተመለከተ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኦክስፋም ሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ የሚሠራ እንደመሆኑ የጉብኝትዎ አንዱ አጀንዳ ድርቁ መሆኑን አልጠራጠርም፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የድርቅ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል? ሁኔታውስ በዚህ ከቀጠለ ምን ዓይነት ቀውስ ይኖራል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግልጽ የሆነ አጠቃላይ ግምገማ ከወር በፊት አድርገው ነበር፡፡ በውጤቱ ለአሥር ሚሊዮን ዜጎች ተጨማሪ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግና አምስት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የውኃ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ተመልክቷል፡፡ ይኼ መጠነ ሰፊ ችግር የተከሰተው ለሦስት ዙሮች ያህል ዝናብ ባለመዝነቡና የአካባቢ ለውጥ ባመጣው ተፅዕኖ ሳቢያ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- መንግሥት የሚችለውን ሁሉ በመጠቀም በድርቁ የአንድም ሰው ሕይወት እንዳያልፍ ለማድረግ እየተረባረበ እንደሆነ እየገለጸ ነው፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚጠበቀው ዕርዳታ በጣም የዘገየ በመሆኑ፣ የአገሪቱ ሀብት እየተሟጠጠ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ የዘገየው ለምን ይመስልዎታል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- በቅርቡ በተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. 2015 የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ በእርግጥም የዘገየ ነው፡፡ አዲስ ገንዘብ ማሰባሰብ ቀላል ባለመሆኑ መዘግየቱ እንደተከሰተ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ከልማት ፕሮግራሞች ገንዘቡን ወደ ዕርዳታ ለመቀየር የመጨረሻ አማራጭ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን የሚሻላት የተሻለ የጤና አገልግሎት፣ ተጨማሪ የትምህርትና የኢኮኖሚ ዕድሎችን ማግኘት ነው፡፡ እነዚህ የልማት እንቅስቃሴዎች ለአገሪቱ በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርቁ የሰጠው ምላሽ በጣም ጠንካራ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ባደረግኩት ጉብኝት እንደታዘብኩት አሁን ዓለም አቀፍ ለጋሾችም ድጋፍ እየሰጡት ነው፡፡ ለአብነት ያህል በጣም ሩቅና በድርቁ በጣም የተጎዱ በኢትዮ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ የሚገኙ አካባቢዎች ዕርዳታ ሲደርስላቸው አይቻለሁ፡፡ የተሻለ የውኃ አቅርቦት ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቶቻቸው ሳይቀር በተወሰነ መንገድ ምግብ ሲቀርብላቸውም ተመልክቻለሁ፡፡ በድርቁ ላይ በቅርበት ክትትል እየተደረገ መሆኑን አይተናል፡፡

ነገር ግን ይህን እያደረጉ ለረጅም ጊዜ መቀጠል ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ዝናብ በመጋቢት ወር መጣል ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ማለት ግን ዜጎች ወዲያውኑ በቂ ምግብ ያገኛሉ ማለት አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በዝቅተኛ እርከን የሚገኙ የአካባቢያዊ መስተዳድሮች መሪዎች እንደገለጹልን ሁኔታው ከወር በፊት ከነበረው የተሻለ ነው፡፡ ይሁንና ሁኔታው ስለሚፈጥረው ተፅዕኖና ስለ ዕጣ ፈንታው እንደተጨነቁ ነግረውናል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከመንግሥት ባሥልጣናት ጋር ካደረግኩት ውይይት የተረዳሁት መንግሥት ለድርቁ ምላሽ እየሰጠና ለሕዝቦቹ ተደራሽ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ጥረት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እየተከናወነ እንደሆነም ተረድቻለሁ፡፡ ወደ ብሪታንያ ስመለስ አንዱ የማደርገው ነገር ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ ድጋፍ ማሰባሰብ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጠው ድጋፍ ለውጥ ሳያሳይ ቢቀር የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻውን ከዚህ ችግር መውጣት ይችላል ብለው ያስባሉ?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ይኼንን መመለስ አልችልም፡፡ ነገር ግን እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው ምላሽ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1985 በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ድርቅ ከአሁኑ የባሰ አልነበረም፡፡ ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር ትልቁ ለውጥ የመንግሥት ምላሽ የመስጠት አቅም የጨመረ መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የገንዘብ አቅም ምን ያህል እንደሆነ መናገር አልችልም፡፡ ይሁንና ችግሩ ባለበት ከቆየ በሌሎች የመንግሥትና የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነገሩኝ ከሆነ መንግሥት ድርቁ በአገሪቱ ዘላቂ ልማት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ቢፈልግም ለሰብዓዊ ቀውሱ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ለተከሰተው የቅርብ ጊዜ ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ከመስጠት አንፃር የኦክስፋም ሚና ምን ነበር?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ኦክስፋም ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በሥራ ላይ ቆይቷል፡፡ በዋነኛነት ትኩረቱ እንደ ውኃ፣ ፅዳትና የዜጎች ኑሮ መሻሻል ላይ ባሉ ዘላቂ የልማት ፕሮግራሞች ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡ እነዚህን የኦክስፋም ፕሮግራሞች በድርቁ ባልተጎዱ አካባቢዎች ዞሬ አይቻለሁ፡፡ በተለይ በውኃ ላይ የምንሠራቸውን ፕሮግራሞች አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በኢትዮ ሶማሊ ብሔራዊ ክልል የውኃ አቅርቦት ለመጨመር እየሠራን ነው፡፡ የእንስሳት የምግብ አቅርቦትን ለመጨመርም እንዲሁ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ ከነዋሪዎች የተዳከሙ እንስሳትን በመግዛት ከመሞታቸው በፊት ዋጋ እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ እነዚህን እንስሳት ሌሎች ተጋላጭ ዜጎችን ለመመገብ እየተጠቀምንባቸው ነው፡፡ ለዜጎች የተወሰነ ገንዘብ በመስጠት እንደ ምግብ ዘይትና ጨው የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦችን እንዲገዙ እያስቻልን ነው፡፡ ነገር ግን ኦክስፋም ችግሩን ለመቅረፍ በቂ ሥራ ሠርቷል ብዬ አላምንም፡፡ ስመለስ እነዚህ ዕርዳታዎች እንዲጠናከሩ የሚያስችል ሕዝባዊ ድጋፍ ለማግኘት ሐሳቡ አለኝ፡፡ በአጠቃላይ ግን ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር እየሠራን ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥትና እንደ ኦክስፋም ባሉ ድርጅቶች የሚከናወኑ የልማት ፕሮግራሞች ድርቅ የመቋቋም አቅምን ለመገንባት ያለሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ኤልኒኖ ሲከሰት ድርቁን መቋቋም አልተቻለም፡፡ ይኼን ተቃርኖ እንዴት ይገልጹታል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የስኬት ታሪክ ነው ያላት፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1985 በተቃራኒ እስካሁን አንድም ሰው አልሞተም፡፡ ይኼ የመቋቋም አቅም መዳበሩን የሚያሳይ ነው፡፡ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ጭምር በመስኖ፣ በጉድጓድ ውኃና በግብርና ሥልቶች እየታገዙ ዜጎች ክብር ያለው ኑሮ ሲኖሩና ተገቢ የሆነ የምግብ መጠን ሲያገኙ አይቻለሁ፡፡ የገቢ መጠናቸውም ከዓመት በፊት ከሚያገኙት የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን የደረሰው ጉዳት የከፋ ከሆነ የመቋቋም አቅምህ ሊሰበር ይችላል፡፡ የውኃ እጥረቱ የቀጠለው ረዘም ላለ ጊዜ ነው፡፡ ዝግጅቱና የመቋቋም አቅሙ ለውጥ አምጥቷል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኦክስፋም በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ፕሮግራሞች መካከል በፆታ እኩልነትና በሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ ላይ የሚሠራቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የእነዚህ ፕሮግራሞች ትኩረት ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡ ውጤቱን ለመለካት አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር ኦክስፋም የስኬት መጠኑን እንዴት ነው የሚለካው?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ገንዘብ የት እንደምናወጣ በጥብቅ ነው የሚቆጣጠረው፡፡ ለእያንዳንዱ ፕሮግራምና ፕሮጀክት ተጠያቂ ነን፡፡ ከመፈጸሙ በፊትም ሆነ ከተፈጸመ በኋላ ሪፖርት እናቀርባለን፡፡ ባህር ዳር ያየሁትን ልንገርህ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በአካባቢው ማር የሚያመርቱ 1,000 ገበሬዎች ነበሩ፡፡ አብዛኛዎቹ ወንዶች ሲሆኑ የሚያገኙት ምርት በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ አሁን በኦክስፋም ዕርዳታ 5,000 ሰዎች ማር በማምረት ሥራ የተሰማሩ ሲሆን፣ የሚያገኙት ምርትም በእጥፍ ጨምሯል፡፡ አብዛኛዎቹም አዲስ አምራቾች ሴቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሥራዎችን የምንለካባቸው የተለያዩ መሥፈርቶች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- ኦክስፋም ሌላው የሚያከናውነው ፕሮግራም ልማትን ከመብትና ከፖለቲካ ውትወታ ጋር ማቀናጀት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ለዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ምን አነሳሳችሁ? ከመንግሥትስ ጋር በቀጥታ አያጋጫችሁም?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ኦክስፋም ሁሌም የሚሠራባቸውን አገሮች ሕግ ያከብራል፡፡ ከመንግሥት ጋር አንጋጭም፡፡ ነገር ግን በውትወታና በፖለቲካ ዘመቻ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ለአብነት ያህል የአቅርቦት ሰንሰለቱን ሳታሻሽል የማር ምርትን መጨመር አይሻልም ማለት ውትወታ ነው፡፡ ኦክስፋም እንዲህ ዓይነት ውትወታዎችን አይሠራም፡፡ የእኛ ትኩረት ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ የሆኑት እንደ አካባቢ ለውጥ ያሉ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ መነሻው ዓለም አቀፋዊ ገጽታ አለው፡፡ ዘመቻ ስናደርግ ከትልልቅ የኢኮኖሚ ኃይሎችና ከበለፀጉ አገሮች መሪዎች ጋር ስለዚህ ፍትሐዊ ያልሆነ ጉዳይ እንነጋገራለን፡፡ አንድ በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የሚያመርቱት ካርበን የተቀረውን 99 በመቶ ሕዝብ እንዴት እየጎዳው እንደሆነ እንናገራለን፡፡ ስለዚህ ኦክስፋም ስለ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ እንጂ ስለ አገሪቱ ፖለቲካ የውትወታ ሥራ አይሠራም፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ ይህ ግን ከፖለቲካ ውትወታ የተለየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገር በቀል ሲቪል ማኅበራት ሊኖራቸው የሚገባው ምኅዳር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች አስፈላጊ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበራትን ሚና ለመጨመር እየተሠራ ጉዳዩ ፖለቲካ እንዳይሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ዜጎች የተደራጀ ድምፅ ሲኖራቸው ኅብረተሰቡ የተሻለ ጠንካራ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ አንዱ የዚህ መገለጫ ፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት ቢሆንም፣ የብድርና ቁጠባ ማኅበር በመመሥረትም ይህን ልታሳካ ትችላለህ፡፡ እነዚህ ማኅበራት እንዲደራጁና ድምፃቸውን እንዲያሰሙ እንረዳቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኦክስፋም በኢትዮጵያ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ እነዚህን ማኅበረሰቦች ከማገዝ አኳያ በመንግሥትና በዕርዳታ ድርጅቶች መካከል የአቀራረብ ልዩነት ያለ ይመስላል፡፡ መንግሥት እነዚህ ማኅበረሰቦች አንድ ቦታ ላይ እንዲሰፍሩና በቀላሉ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአርብቶ አደሮቹ የአኗኗር ዘይቤ እንዲቀየር አይፈልጉም፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- በሁለቱ አቀራረቦች መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለ ብዬ አላስብም፡፡ የመጠን ጉዳይ ነው፡፡ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩትንም ሆነ ባሉበት መርጋት የሚፈልጉትን ለማገዝ እንሞክራለን፡፡ ዜጎች ተገደው አንዱን እንዲመርጡ መደረግ የለበትም ብለን እናምናለን፡፡ በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጡ ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወሩ እንደሚያስገድድ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍሪካ የሚሰጡ የልማት ድጋፎች ከፖሊሲ ቅድመ ሁኔታ ጋር እንዲያያዙ መደረጋቸው ችግር ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ እንደ ልማት ባለሙያ ይህንን እንዴት ያዩታል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ኦክስፋም በቅድመ ሁኔታ አያምንም፡፡ እኛ ዕርዳታ ለመስጠት ሕግ መሻሻል አለበት የሚል አቀራረብ የለንም፡፡ እኛ የምንፈልገው ለሁሉም ሰው የኢኮኖሚ ዕድል እንዲፈጠር ነው፡፡ የተገለሉ ሰዎችን ለመርዳት እንሞክራለን፡፡ ለእኛ ችግር የሚሆነው መንግሥት ለምሳሌ ሴቶች የሚሳተፉበትን ፕሮጀክት መደገፍ አትችሉም ሲለን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ከኦክስፋም አንፃር ነው፡፡ በአጠቃላይ የዕርዳታና የቅድመ ሁኔታን ግንኙነት እንዴት ያዩታል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ዕርዳታ የሚለግሱ ሰዎች አሳሳቢ ናቸው በሚሉዋቸው ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው ምክንያታዊ ነው፡፡ ለአብነት ያህል መድልኦ ይፈጸማል የሚል መረጃ ካለ ውይይት ማድረጉ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይሁንና በጉዳዩ ላይ መነጋገር ቅድመ ሁኔታ ከማቅረብ ይለያል፡፡ ቅድመ ሁኔታ ማቅረብ የፋይናንስ ፈላጭ ቆራጭነትን ያስከትላል፡፡ ለእኔ ዋናው ጉዳይ መነጋገርና መደራደር ነው፡፡ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጋራ አስተሳሰብ ለመፍጠር መሥራት ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኦክስፋም በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ የሚሰጠው ዕርዳታ ስላስገኘው ውጤት ምን ይሰማዋል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- ከምንም ነገር በላይ ውጤታማ እንዲሆንና ጥራት ያለው ሥራ በዕርዳታው እንዲከናወን እንጥራለን፡፡ ውጤታማ ለመሆን ትክክለኛውን ዘርፍ ከመምረጥ እንጀምራለን፡፡ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበትን መንገድ መምረጥ ሌላኛው ሥራችን ነው፡፡ የሥራው ጥራት ከሚወጣበት ወጪ አንፃር ሊገመገም ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በእኛ አገር የሚገኙ ለጋሾች በሁለቱ መካከል መመጣጠን እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ ይህን እኛም ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ዕቅድ እንደታሰበው ላይሠራ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኦክስፋም በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ዘመቻ እንደሚያደርግ ነግረውኛል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ ለመካስ እየሞከረ ነው ማለት ይቻላል?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ሀብታም አገሮች ይበክላሉ፣ ደሃ አገሮች ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ የደን ምንጠራ፣ የአካባቢ ሙቀት ለውጥና የዓሳ ምርት ለግማሽ ምዕተ ዓመት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ኦክስፋም በአካባቢ ጥበቃ ላይ አተኩሮ የሚሠራ ተቋም አይደለም፡፡ ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ በደሃ ሕዝቦች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስረዳት እንሞክራለን፡፡ ውሳኔ አሰጣጣቸው ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡ ደሃ ሕዝቦች ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር የአኗኗር ዘዴያቸውን እንዲቀይሩም እንሠራለን፡፡ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ለሚሠሩ ሥራዎች ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ለውጡን ለማሳለጥ ግን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- የዕርዳታ ኤጀንሲዎች ከዘላቂ ልማት ይልቅ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ላይ ያተኩራሉ ተብለው ይተቻሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ማርክ ጎልድሪንግ፡- በኢትዮጵያ ለጋሾችና መንግሥት በዘላቂ የልማት ሥራዎች ላይ ስኬታማ ሥራ እንደሠሩ አስባለሁ፡፡ አሁን በአገሪቱ በፍፁም ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ከአስቸኳይ ዕርዳታ ይልቅ ዜጎች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ፣ ጤናማ ሕይወት እንዲመሩና ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ ይሁንና ቀውስ ሲከሰት ደግሞ ዕርዳታ ማድረግ ግድ ነው፡፡ የኤጀንሲዎቹ ሥራ ሁለቱንም የተመለከተ ነው፡፡ አዝርዕት እያበቀልን ስለሆነ ዛሬ የዕለት ደራሽ ምግብ አንሰጥም አይባልም፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...