Tuesday, February 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገንዘብ እጥረት ቀውስ በኢኮኖሚው ላይ ሥጋት መደቀኑን መንግሥት አመነ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ዘንድሮ መሰብሰብ አልተቻለም

የ2011 ዓ.ም. በጀት 59 ቢሊዮን ብር ጉድለት አለበት

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የገንዘብ እጥረት ቀውስ እንደገጠመው፣ እጥረቱ በፍጥነት መፍትሔ ካልተገኘለት ኢኮኖሚውን በመጉዳት ማኅበራዊ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መንግሥት በይፋ አስታወቀ፡፡

ይህንን የተናገሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ የፌዴራል መንግሥትን የ2011 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት ሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

ክስተቱ መፈጠር ከጀመረ ረዥም ጊዜ ቢሆነውም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ግን የገንዘብ እጥረቱ ጎልቶ በመውጣት ወደ ኢኮኖሚ ቀውስነት የመሸጋገር አዝማሚያ እየታየበት መሆኑን፣ ሚኒስትሩ ካቀረቡት የበጀት መግለጫ ንግግር መረዳት ተችሏል፡፡

‹‹ከኤክስፖርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ደካማ በመሆኑ ለልማት የሚያስፈልጉ የካፒታል ጥሬ ዕቃዎች፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ የማይመረቱ መሠረታዊ ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ፈታኝ ሆኗል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው የውጭ ምንዛሪ ደካማ ስለሆነ፣ የአገሪቱን ልማት ለማስቀጠል የውጭ ፋይናንስ በተለይም የውጭ ብድር ለማግኘት እንቅፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሚኒስትሩ ንግግር የሚያስረዳው አገሪቱ ከኤክስፖርት የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ ስለሆነ፣ የውጭ ዕዳ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ የአገሪቱ የብድር አጋር የነበሩ የውጭ መንግሥታትና ተቋማት ጭምር አዲስ ብድር ከመስጠት መቆጠብ መጀመራቸውን ነው፡፡

ሪፖርተር ያገኘው የሁለት ዓመት ተኩል የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዶክመንት እንደሚያስረዳው፣ መንግሥት በቀጥታ የተበደረው የውጭ ዕዳ ክምችት በዚህ ዓመት 24.75 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ በ2009 ዓ.ም. 13 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ አገሪቱ ስታገኝ የነበረው የውጭ ብድር በኢንቨስትመንትና ለኢንቨስትመንቱ በሚያስፈልገው ቁጠባ መካከል የሚታየውን ልዩነት ለመሸፈን ከፍተኛ ሚና እንደነበረው የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህ የውጭ ብድር ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱና ከኤክስፖርት ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ መጠን መጨመር ይቅርና በነበረበት ማቆየት እንኳን ባለመቻሉ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ከታክስ ይገኝ የነበረው ቢሆንም በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. እንደቅደም ተከተላቸው 15.2 እና 10.3 በመቶ ብቻ ማደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ታቅዶ ከነበረው የታክስ ገቢ 39 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንዳልተቻለ፣ ለዘንድሮው በጀት ዓመት ከታቀደው የታክስ ገቢ ደግሞ 50 ቢሊዮን ብር እንደማይሰበሰብ ከወዲሁ መታወቁን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ወደ በ2011 ዓ.ም. እንዲሸጋገሩ መንግሥት መገደዱን፣ ይህ ሁኔታም በመንግሥት ላይ የበጀት ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የ2011 ዓ.ም. በጀት ሲዘጋጅ ከፍተኛ የበጀት አጠቃቀም ዲሲፕሊን ይኖራል በሚል መርህ የታክስ አሰባሰቡ ላይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ በመገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተለያዩ ዕቃዎችን ከውጭ በሚያስገቡ የመንግሥት ተቋማት ላይ መሰብሰብ የሚገባውን የጉምሩክ ታክስ በማስላት፣ ንብረቶቹ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው እንዲገቡ እንደሚያደርግ በረቂቁ የ2011 ዓ.ም. በጀት ላይ ተገልጿል፡፡ ባለሥልጣኑ ከአስመጪ የመንግሥት ተቋማት የሚጠበቀውን የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ የገንዘብ መጠን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ለተቋማቱ እንደሚያሳውቅ፣ በዚህ መሠረትም ያልተከፈለው የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ የተቋማቱ ዓመታዊ በጀት አካል እንደሚሆን ተወስኗል፡፡ የ2011 ዓ.ም. በጀት 346.9 ቢሊዮን ብር ሆኖ የቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 59.3 ቢሊዮን ብር በአገር ውስጥ (የገንዘብ ኅትመትን ጨምሮ) የሚሸፈን እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከቀረበው የ2011 ዓ.ም. በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 91.7 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 113.6 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ 135.7 ቢሊዮን ብር ሆኖ፣ በዚህ ዘርፍ ውስጥ የሚካተት ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ስድስት ቢሊዮን ብር ሆኖ ቀርቧል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግዙፍ የልማት ድርጅቶችንና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በከፊልና ሙሉ በሙሉ ለግል ባለሀብቶች ለማዘዋወር ሰሞኑን የወሰነ ቢሆንም፣ የ2011 ዓ.ም. በጀት ግን ከእነዚህ ተቋማት የአክሲዮን ድርሻ የሚገኝ ገቢን አላካተተም፡፡ ረቂቅ በጀቱ ለተጨማሪ ዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች