Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኢትዮጵያ ችግሮች ኢትዮጵያዊ መፍትሔዎች ይፈለጉ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተወሰዱ ያሉ የተለያዩ ዕርምጃዎች፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን እያሳዩ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች እስር ላይ የነበሩ ወገኖችን በብዛት መፍታት፣ ክሶችን ማቋረጥ፣ አገራቸውን አገልግለው እንደ አልባሌ ዕቃ የተጣሉ ሰዎችን ማስታወስና መደገፍ፣ በጡረታ የሚገለሉትን በክብር መሸኘት፣ ማዕረጋቸው የተገፈፈን መልሶ መስጠትና የጡረታ መብት ማስከበር፣ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ሊያቆሙ የሚችሉ ጥዑም መልክቶችን ማስተላለፍ፣ አገርን ከሌብነትና ከዘረፋ ለመታደግ ቁርጠኛ አቋም ማሳየትና የመሳሰሉ ዕርምጃዎችን ሕዝብ በአንክሮ እየተከታተለ ነው፡፡ ይህች ታላቅ አገርና ይህ የተከበረ ሕዝብ በዚህ ዓይነቱ ቀና ጎዳና መራመድ ከቻሉ፣ መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡ ይህ ተስፋ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ በአገራዊ ዙሪያ መለስ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ላጋጠሙዋት ችግሮች ኢትዮጵያውያን በነፃነት ሐሳብ ማዋጣት ከቻሉ መፍትሔው ቅርብ ነው፡፡ የሉዓላዊነት መገለጫም ነው፡፡ ለዚህም ሲባል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ፣ በሁለት ታላላቅ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች ገዥው ፓርቲ በሚመራው መንግሥት ተግባራዊ መሆን ከመጀመራቸው በፊት ጠቃሚ ነጥቦች መነሳት አለባቸው፡፡ የኢኮኖሚ ሪፎርምን በሚመለከት የተላለፈው ውሳኔ፣ የአገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ ዕድገቱ ዜጎችን አካታች ሆኖ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሚፈለገው ኢኮኖሚ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖራቸው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) እና የውጭ ባለሀብቶችን ይጋብዛል፡፡ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ ኩባንያዎችን ሙሉ በሙሉና በከፊል በአክሲዮን ለማስተላለፍ ተወስኗል፡፡ አፈጻጸሙም የልማታዊ መንግሥት ባህሪያትን፣ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ማስቀጠልን፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በማረጋገጥ እንዲመራ ማድረግና ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲሲፕሊን ተግባራዊ እንሚደረግ ተገልጿል፡፡ ቃልና ተግባር ከተጣጣሙ ጥሩ ነው፡፡

ነገር ግን ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በነፃ ገበያ ትመራለች በተባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ጉራማይሌዎች ታይተዋል፡፡ በአንድ በኩል የአገሪቱ የዕድገት ሞተር ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የግል ሴክተር ማቆጥቆጡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥትን ጡንቻ ያፈረጠሙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንደ እንጉዳይ መፍላታቸው ነው፡፡ በምዕራባውያን የሚታዘዙ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንክብሎችም ከዕዝ ወደ ነፃ ገበያ ሥርዓት የተደረገውን ሽግግር አወዛጋቢ እንዳደረጉትም ይታወሳል፡፡ የእነሱን ተፅዕኖ በመጋፋት ወደ ልማታዊ መንግሥት የተደረገው ጉዞም እንዲሁ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል በርካታ ውጣ ውረዶች ቢታለፉም፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በብዛት እየታዩ ነው፡፡ ችግር ያለባቸውን ንፋስ አመጣሾቹን ትተን፣ በትክክል ሠርተው ለአገር ኢኮኖሚና ለሥራ ፈጠራ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን የግል ባለሀብቶችን ተወዳዳሪነትና የዕድገት ተስፋ የሚያቀጭጩ ድንበር ዘለል ኮርፖሬሽኖች እንዲፈነጩ የሚያደርግ ስህተት ላለመሥራት መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም ግፊቶችና እጅ ጥምዘዛዎች የረቀቁ በመሆናቸው ከጎረቤት ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ፣ ከሩቅ ደግሞ የደቡብ አሜሪካ አገሮች በምዕራባውያንና በሸሪኮቻቸው መዋጥን መማር ይገባል፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ መፍትሔዎችን እንዳለ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ መፍትሔዎች ስላሉ እነሱን መጠቀም ይሻላል፡፡

እርግጥ ነው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማፍራት ቢቻልም፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገልና ሥር የሰደደ ሌብነት ምክንያት ጤናማ ተወዳዳሪነት እየጠፋ አገሪቱ ችግር ውስጥ መግባቷ ግልጽ ነው፡፡ የአገር ሀብትን በውጭ ምንዛሪ ማሸሽ፣ ገቢን በተገቢው መንገድ መሰብሰብ አለመቻል፣ ቢሮክራሲው ማሠራት አለመቻሉና የመሳሰሉት በርካታ ችግሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ሳንካ ፈጥረዋል፡፡ በሕዝብ ላይ እንደ መርግ የከበደ የኑሮ ውድነት አምጥተዋል፡፡ ነገር ግን በሕግ ማዕቀፍ የሚመራ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር አገርን መለወጥ ከሚችል የአገር ውስጥ ባለሀብት ጋር ተዓምር መፍጠር ይቻላል፡፡ አዲሱ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሲከናወን ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎችና ሠርተው ማሠራት የሚችሉ ባለሀብቶችን ዕምቅ አቅም መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትና የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማስቀጠል ሲታሰብ፣ ጊዜያዊ ችግሮች ዘላቂውን የአገር ጥቅም እንዳይጋርዱ መጨነቅና መጠበብ ያስፈልጋል፡፡ መጀመርያ ለኢትዮጵያዊ መፍትሔዎች ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

ጠንካራና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያግዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በባለሙያዎች ድጋፍ መቀየስ፣ የውጭ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለመማረክ በሚደረግ ጥረት በርካታ አማራጮችን ማየት፣ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል የሚተላለፉ ድርጅቶችን አክሲዮኖች ለመሸጥ መሟላት ካለባቸው መካከል ሕጋዊ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀት፣ ፍትሐዊነትና የመሳሰሉትን በትኩረት ማሰብ፣ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ በተለያዩ መንገዶች እንዳይኖሩ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ፣ የኢትዮጵያውያንን ሥጋቶች መገንዘብና የአገርን ዘላቂ ጥቅም ከግምት ማስገባት መቼም ቢሆን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ የካፒታል ዕድገት ሲኖር፣ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የሆነ የግል ዘርፍ በአምራችነት ሲሰማራና የአገሪቱ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርትና የነፍስ ወከፍ ገቢ ሲጨምር፣ በእርግጥም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ለሕዝቡ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር መለካት ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን እንደሚታየው የሕዝቡን የባለቤትነት ስሜት የማያመላክት ዓይነት ሁነት ውስጥ ከተገባ ችግር ይፈጠራል፡፡ የአክሲዮን ሽያጫቸው ለገበያ የሚቀርቡ ኩባንያዎች ወይም ፕሮጀክቶች እንደተባለው አፈጻጸማቸው በጥቅብ ዲሲፕሊን የማይመራ ከሆነ፣ የተወሰኑ ቡድኖችና የውጭ ኮርፖሬሽኖች መቀለጃ ይሆናሉ፡፡ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደ ጥሩ ዕርምጃ የታየው ውሳኔ፣ በብልጣ ብልጦች የሚጠለፍ ከሆነ አደጋውን ለመቀልበስ አዳጋች ነው፡፡

      የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማሟላትና ኢኮኖሚውን አስተማማኝ ለማድረግ በየሙያ መስኩ አሉ የተባሉ ባለሙያዎችን መጠቀም ይገባል፡፡ በዚህ መሀልም የትኞቹ ኩባንያዎች አክሲዮኖቻቸው ለገበያ መቅረብ ይኖርባቸዋል፣ የትኞቹ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ሆነው መቀጠል አለባቸው ለሚባለውም ብርቱ ምክክር ያስፈልጋል፡፡ አትራፊን ከአክሳሪው፣ ተወዳዳሪውን መወዳደር ከማይችለው፣ ወዘተ. የመቀላቀል ጉዳይም ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ነው፡፡ ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መዳረስ የሚችለው፣ ኢኮኖሚው ከተለያዩ መሰናክሎች ነፃ ሆኖ የሚመራባቸው ዘመናዊና አሳታፊ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ሲኖሩ ነው፡፡ አክሲዮኖች ሲሸጡ በዘፈቀደ ሳይሆን የአክሲዮን ገበያ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህንን ገበያ የሚቆጣጠር ብርቱና ዘመናዊ ተቋም መመሥረት አለበት፡፡ ይህን ዓይነቱ ተቋም ደግሞ በመስኩ አንቱ በተባሉ ባለሙያዎች መመራት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ደላሎች ይጠልፉትና የበለጠ ጥፋት ይመጣል፡፡ ውሳኔዎች በፍጥነት ሲተላለፉ ባለማስተዋል የሚያጋጥሙ አደጋዎች ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ የምዕራባውያን የኢኮኖሚ ሞዴል ብቻ ሳይሆን ሌሎች አማራጮችን በመቃኘት ኢትዮጵያዊ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...